“እንፈላለጋለን!”- ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ
(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና
የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)
የሀገራችንን ነባራዊ ወቅታዊ ኹኔታ መኾን ካለበትና ሊኾን ከሚገባው ይልቅ እየኾነ ካለው ኹለንተናዊ
እንቅስቃሴ አንጻር ስንመለከት እጅግ በጣም የተለያየ፣ ፈጽሞ ሊቀራረብ የማይችል፣ አብሮ ሊያሰራ የማይችል፣
ፍጹም ተቃራኒ ሀሳብና አቋም ያላቸው ኃይሎችና አካላቶች ሕብረት ፈጥረውና ሕብረት ፈጥረናል ብሎም
ተስማምተናል ሲሉ መስማት የተለመደ ኾኗል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ አመራሮች ስለሕዝብ በተለያዩ መድረኮች “እንትን ሕዝብ እንዲህ ነው – እንዲያ ነው
– እንዲህ ይመስላል – እንዲህ ይኾናል” – – – ወዘተ እያሉ የሚናገሩትና በብዙዎች ጭብጨባ የሚደምቀውን
ነገር እንደቁም ነገር ወስዶ እዚህ ላይ መድገም በስህተት ላይ ስህተት መስራት ነውና ከቁም ነገር ሳይወስዱ ማለፉ
ተገቢ ይኾናል፡፡
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ገና ከበሬ ማረስ ላልወጣን፤ በገጠር የሚኖር ሕዝብ ብዛት ከከተማው አንጻር ፈጽሞ
የማይወዳደርባት፤ መሠረታዊ ፍላጎታችንን ማሟላት ያቃተን – ገና ምግብ፣ መጠለያ፣ ውሃ፣ – – – ወዘተ ጥያቄ
እያለበት – የመኖርና በሰላም ደሕንነትን የማስጠበቅ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ባለባት ሀገር ውስጥ፤ የትኛውም
– በየትኛውም የሀገራችን ክፍል የሚገኝ ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ በመሠረታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት መለኪዎች
እምብዛም ልዩነት የሌለው ሕዝብ ባለባት፤ ሥራ አጥነት አፍ አውጥቶ በሚናገርባት – ድህነት እጅጉን
በተንሰራፋባት፤ የመንግሥት ተቋማት እንደአቅማችን እንደኾኑ በሚታወቅባት፤ ሰላም – ፍትህ – መልካም
አስተዳደር እጅግ አንገብጋቢ የወቅቱ ጥያቄ በኾነበት እጅግ አስጨናቂ ኹኔታ ውስጥ እንዳለን ለማንም የተሰወረ
አይደለም፡፡
ከላይ የተጠቀሱት እጅግ ጥቂት ማሳያዎች ያሉ ቢኾንም እዛም እዚም ባልታረሙ አንደበቶች የሚነገሩና
የሚደሰኮሩ ነገሮች – ማዕከሉን – ከእንፈላለጋለን ይልቅ አንፈላለግም – ከመቀራረብ ይልቅ መለያየት –
ከመዋደድ ይልቅ በተቃራኒው – ከሕብረት ይልቅ በተቃርኖ ውስጥ መኖራችን ዕውን አንፈላለግምን? የሚል
ትርጉም ያለው ጥያቄን እንድናነሣ ግድ ብሎናል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ምንም ይኹን ምን ያለፍንበት፤ ምንም ይኹን ምን ያለንበት ብሎም ምንም ይኹን ምን
የምንኖርበት ኹለንተናዊ ኹኔታ – እንፈላለጋለን ብቻ ሳይኾን እጅጉን እንፈላለጋለን!!!
እንፈላለጋለን ብቻ ሳይኾን እጅጉን እንፈላለጋለን!! የሚለው ሊሰመርበት ይገባል፡፡

 ለምን?
አንደኛ፡- የጋራ ትላንት ስላለን፤
– ምንም ይኹን ምን፡ የጋራ ኹለንተናዊ ትላንት አለን፡፡ ይህም እኛነታችንን የሚገልጽና ሌላውም እኛን
የሚመለከትበት መንገድ ነው፡፡
ሁለተኛ፡- የጋራ ሀገራዊ ጥላ ባለቤት ነን፤
– እንደአንድ ሀገር የጋራ ሀገራዊ ጥላ በውስጣችን አለ፡፡ ምንም ይኹን ምን ደረጃውና አቅሙ መንግሥት፣
ባንዲራ፣ ብሔራዊ መዝሙር፣ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ድንበር አለን፡፡ ዓለም እኛን የሚገልጽበት –
እኛም ከሌላው አንጻር የምንታይበት ነው፡፡
ሶስተኛ፡- ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ደረጃ አለን፤

2

– እንደሕዝብ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል የሚገኝ ሕዝብ ከሌላኛው በመሠረታዊ መለኪያዎች የተለየ
አኗኗር የለውም፡፡ ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚኾነው ሕዝባችን ከግብርና የተላቀቀና ከአርብቶ አደርነት
የወጣ አይደለም፡፡ እነዚህ ደግሞ ባሕሪያዊና ጠባያዊ መገለጫዎቹ እጅጉን ተመሳሳይ ናቸው፡፡
አራተኛ፡- መፈላለጋችን በጽንሰ ሀሳብና በተግባር ተፈላጊ ነው፤
– በጽንሰ ሀሳብ ከተናጠል ሕብረት፤ ከሕብረት ደግሞ ውህደት እጅግ ኃያል እንደኾነ ይታወቃል፡፡ ምንፈላለገው
ስለምንፈላለግ ብቻ ሳይኾን የጋራ መጠሪያዎችና ትርጓሜዎችም ጭምር ስላሉን ነው፡፡
ለአብነት፡- አብዛኛው ሕዝብ አማኝ አልያም ሃይማኖት ያለው ነው፡፡ ክርስትናና እስልምና ደግሞ
ኢትዮጵያን ከትላንት አንጻር ብቻ ሳይኾን በኹሉም የጊዜ ማዕቀፍ የሚያስቀምጡ ናቸው፡፡
 የጊዜ ማዕቀፍ፡- ትላንት – ዛሬና ነገን ይይዛል፡፡
 የትኛውም ሕዝብ በዛ ማዕቀፍ ውስጥ ያለውን ኹለንተናዊ የይዘት መጠሪያ ማጣት አይፈልግም፡፡
ያን ያጣም ሙሉዕ ይኾን ዘንድ ይቸገራል፡፡

አምስተኛ፡- መፈላለግ ባሕሪዊና ጠባያዊ ማንነት ሲኾን አለመፈላለግ ግን ጠባያዊ ማንነት ብቻ ነው፡፡
– ባሕሪ ተፈጥሯዊ ማንነት – የማይቀየርና የማይለወጥ የሕልውነት ማረጋገጫ ሲኾን ጠባይ ግን ከተፈጥሮ
በኃላ በሂደት የሚለዋወጥና የሚቀያየር ማንነት ነው፡፡
ስድስተኛ፡- የመፈላለግ አመክንዪ ካለመፈላለግ ጋር ፈጽሞ አይወዳደርም፤
– ላለመፈላለግ ምክንያት ተደርገው የሚወሰዱ ኹለንተናዊ ነጥቦች በሙሉ ከመፈላለግ አንጻር ሚዛን ላይ
ቢቀመጥ ፈጽሞ የሚወዳደር አይደለም፡፡
– አለመወዳደር ብቻ ሳይኾን የማወዳደሪያ ሚዛንም ሊኾኑ የማይችሉ ናቸው፡፡
– ከሚያለያዩን ይልቅ የሚያቀራርቡን፤ ከሚያራርቁን ይልቅ የሚያመሳስሉን ነገሮች ቁጥር ስፍር
የላቸውም፡፡
ሰባተኛ፡- በመፈላለግ መወዳደር ባለመፈላለግ ከመወዳደር እጅጉን ይልቃል፤
– ኢትዮጵያ እንደኢትዮጵያ ያላት የሕዝብ ብዛት በብዙ ኹለንተናዊ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ
መለኪያዊች ትልቅ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ሃብት ማንም በመፈላለግ ውስጥ እንጂ ባለመፈላለግ ውስጥ ፈጽሞ
ሊያገኘው አይችልም፡፡
– በተናጠል ተወዳድረን ከምናገኘው ይልቅ በጋራ ተወዳድረን የምናገኘው እንደሚበልጥ አያጠራጥርም፡፡
– ከተናጠል ድምጻችን ይልቅ የጋራ ትንፋሻችን ጎልቶ እንደሚሰማ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ስምንተኛ፡- መነጣጠል ከምንችልባቸው ይልቅ የማንችልባቸው ነጥቦች ይበዛሉ፤
– የግለሰቦች፣ የቡድኖችና የተቋማት መነጣጠል እንጂ ሕዝብ እንደሕዝብ መነጣጠል ኖሮ አያውቅም፡፡
የለምም፡፡ ያለው የግለሰቦችና የቡድኖች መነጣጠል ነው፡፡ የጥቂቶች መነጣጠል እንደምን ወደ ሕዝብ
መነጣጠል፤ ግለሰባዊና ቡድናዊ መነጣጠል ሕዝባዊ መነጣጠል ተደርጎ ይወሰዳል?
ዘጠነኛ፡- የነገ ፍላጎቶቻችን የጋራ ናቸው፤
– እንደሕዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ የነገ ፍላጎቶቻችን ተመሳሳይና ተቀራራቢ ናቸው፡፡
– እነዚህ ተቀራራቢና ተመሳሳይ ፍላጎቶቻችን የሚሳኩት በኹለንተናዊ የተናጠል ኹለንተናዊ ትጋት ብቻ
አለመኾኑ፤
– የጋራ ትላንት – የጋራ ዛሬና የጋራ ነገ ያላቸው እንደምን ላይፈላለጉ ይችላሉ?
አስረኛ፡- መፈላለግ ምርጫ አልባ ነው፤
– በየትኛውም ዕሳቤ፣ አስተምህሮና ዕሳቤ ኹለንተናዊ ግንኙነት የነበረ፣ ያለና የሚኖር ነውና መፈላለግ
ምርጫ አልባ ግዴታ ነው፡፡
– በየትኛውም ዓለም የሚኖር ሕዝብ የኹለንተናዊ ግንኙነቱን መጠን፣ አይነት፣ ይዘት፣ ጊዜና ቦታ ይወስን
ይኾናል እንጂ አልገናኝ እንኳ ቢል ተገናኝቶና የመገናኘትን መንገድ መከተል ይገባዋል፡፡

3
አስረ አንደኛ፡- ያም ኾነ ይህ በዓለም ውስጥ ኗሪ ነን፤
– ዓለም በብዙ መለኪያ ድንበር አልባነትን በኹለንተናዊ መንገድ እየያዘ በመኾኑ ለድንበርተኝነት
የምናደርገው ኹለንተናዊ ትግልና ትጋት በዚህ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ውስጥ የሚወድቅ መኾኑ ሳይታለም
የተፈታ ነው፡፡
እንፈላለጋለን ብቻ ሳይኾን እጅጉን እንፈላለጋለን ሲባል ካለመፈላለግ አንጻር መፈላለግ አስፈላጊና ጠቃሚ ስለኾነ
ብቻ አይደለም፡፡ ከዛ በላይ አለመፈላለግም ስለማይቻል ነው፡፡ አኹን ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን አለመፈላለግ
ቦታ የሌለውና ተጽዕኖ ስለማይፈጥር ብሎም ያለሱ ህልውናን ጭምር ማስጠበቅ ስለማይቻል መኾኑ ሊሰመርበት
ይገባል፡፡
በሥልጣኔና በተወዳዳሪ ዘመን ላይ አለመፈላለግ ምርጫ አይደለም፡፡ ምርጫ ሊኾንም አይችልም፡፡ ስለኾነም
ሊሰመርበት የሚገባው ኹለንተናዊ ግንኙነታችን ምን ይኹን? ምን ይምሰል? እንጂ ከዛ የዘለለ ያለ ግንኙነት መኖር
ፈጽሞ የማይታሰብና ሊታሰብ የማይገባው ኃላቀርነት ነው፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ
ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

Leave a Reply