”እኛ ደቡብ አፍሪካ የሄድነው ወልቃይት ወደ አማራ ይሁን ወደ ትግራይ ይሁን የሚለውን ለመወሰን አይደለም” ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ማክሰኞ ኀዳር 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያ እና ምላሽ በሰጡበት ወቅት ወልቃይትን አስመልክቶ ”እኛ ደቡብ አፍሪካ የሄድነው ወልቃይት ወደ አማራ ይሁን ወደ ትግራይ ይሁን የሚለውን ለመወሰን አይደለም“ ብለዋል።

የፕሪቶሪያው Summit ይሄን ለመወሰን ስልጣን የለውም። ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ”ምን አገባውና ነው የኢትዮጵያን መሬት እዛ ይሂድ እዚህ ይሂድ የሚለው?” ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም፤ እኛ እዛ የሄድነው እንዴት ሰላም አምጥተን ችግሮቻችንን በንግግር እንፍታ ለማለት ነው። ለምን ወልቃይት ተስቦ እዛ ውስጥ እንደሚገባ አላውቅም። ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው “ብዙ አነባለሁ ፤ ብዙ እሰማለሁ ወልቃይትን በሚመለከት የሚነገሩ ሽረባዎች ፣ ሴራዎች … Conspiracy ብዙ እሰማለሁ። የወልቃይት ህዝብ እንዲገነዘብ የምንፈልገው የሚወራው የሚናፈሰው አሉባልታ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት እጁ የለበትም።“ ሲሉም ገልጸዋል።

“ወልቃይት ብቻ አይደለም ሰሜን ሸዋ ላይ ኦሮሚያ እና አማራ ጥያቄ አላቸው፤ እሱም ደቡብ አፍሪካ ይኬድ? ሲዳማ እና ወላይታ ብላቴ ላይ ጥያቄ አላቸው እሱም ደቡብ አፍሪካ ይኬድ? እኛ አሰራር የለንም? ልምምድ የለንም? ቦታው አይደለም።”

የተስማማነው በኢትዮጵያ ህግ እና ስርዓት ይፈፀም ነው። ከህገመንግስት በፊት ነው የተወሰደው ፤ በጉልበት ነው የተወሰደው ላሉት የእኔ ፍላጎት ያ ስህተት እንዳይደገም ነው። ብለዋል

ዛሬን በጉልበት ነገ ታግሰን በጉልበት ከሆነ ዘላቂ ሰላም አያመጣም። ወልቃይት ብንፈልግም ባንፈልግም የተወላገደ አማርኛ፣ የተወላገደ ትግርኛ የሚናገር የኹለቱ ህዝቦች ድልድይ የሆነ ህዝብ ነው።

ኹለቱንም ቋንቋ የሚናገር፣ የተጋባ የተዋለደ ህዝብ ነው። ወልቃይቴነቱን ነው አትንኩብኝ ያለው እንጂ ከእንግዲህ ከትግራይ ጋራ አልገናኝም አልነጋገርም አላለም ፤ አይችልም ቢልም።

ይሄንን በህግ እና ስርዓት ብንፈፅም ለወልቃይትም ይጠቅማል ፣ ለአማራ ይጠቅማል፣ ለትግራይ ይጠቅማል የሚጎዳው ነገር የለም። በህግ እና ስርዓት እንፈፅም የሚለውን ነገር ከብዙ ተንኮል ጋር ማያያዝ አስፈላጊ አይደለም። ሲሉም ተናግረዋል።

አክለውም፤ ”እዛ አካባቢ ጥያቄ ረዘም ላለ ጊዜ ነበረ፤ ለዛ ብለን ነው ኮሚሽን ያቋቋምነው ከዚህ ቀደም ገልጫለሁ ፤ አሁንም ያኔም የነበረን አቋም በህግ አግባብ በምክክር በውይይት ይፈታ የሚል ነው። ይህ ማንም ይጎዳል ብዬ አልገምትም ውጤቱን በጋራ እናየዋለን።“ ብለዋል።

ዋናው ፍላጎት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ንግግር ያስፈልጋል። ይሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “የተሰጣቸውን ስራ በትክክል የማይሰሩ ሰዎች የፌዴራል መንግስት እያሉ ብዙ ሽረባ እንደሚሰሩ እናውቃለን። ሂደቱን ላለማበላሸት ነው ዝም ያልነው። ሂደቱ መስመር ከያዘ በኃላ ለህዝብ ግልፅ እናደርጋለን።” ሲሉም ተናግረዋል።

ስራውን መስራት አለበት እያንዳንዱ ዞን ፣ እያንዳንዱ ወረዳ ተንጠልጥሎ ፌዴራል ምናንም ሳይሆን ስራውን መስራት አለበት መሬት ላይ ያለውን ያን ካደረገ ሌላው ጉዳይ እዳው ገብስ ነው ፤ ብዙም የሚያስቸግር አይደለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለውም፤ ሁለት ነገሮች አሉ ያሉ ሲሆን፤ ”ከአማራ ወገን ላለፉት 30 ዓመታት ብዙ ወልቃይቴዎች ሲፈናቀሉ፣ ሲሰደዱ ኖረዋል እነሱ በሌሉበት ሪፈረንደም ቢባል የተመናመነ ህዝብ ነውና እንጎዳለን፤ በትግራይ በኩል አሁን በተፈጠረው ግጭት ብዙ ሰው ወጥቷል ስለወጣ አሁን ባለው ቢወሰን አማራ ክልል advantage ይወስዳል የሚሉ ስሞታዎች ይሰማሉ።“ ብለዋል

ወይቃይት የወልቃይቴ ነው ይታወቃል። ከአድዋም የሄደ ከደብረ ማርቆስም የሄደ ሰው ሊኖር ይችላል ግን ወልቃይቴ ይታወቃል ፤ አትላንታም ይኑር አውስትራሊያም ይኑር ጅማም ይኑር ስለዛ ቦታ ሃሳብ እንዲሰጥ እድል ካልተሰጠው በስተቀር ዘላቂ ሰላም አያመጣም።ጉዳዩ ወደዛ ስለሄደ ወደዚህ ስለመጣ ሳይሆን ያ ህዝብ የራሱን fate እንዲወስን ዲሞክራሲያዊ እድል እንዲያገኝ ማድረግ ከቻልን ብቻ ነው መፍትሄ የሚመጣው። እና እነዛን ችግሮች በሚቀርፍ መንገድ እንደሚሰራ ተስፋ አደርጋለሁ። ጊዜ የወሰድነው ፣ ጊዜ የጠበቅነው ለዛነውና ብዙ ስጋት ባይኖር በተረጋጋ መንፈስ ቢሰራ ዘላቂ ሰላም ያመጣል ቢባል መልካም ነው።

አለበለዚያ ከህገመንግስት በፊት TPLF በግድ ስለወሰደ አሁን እኛ በግድ ወስደን እዛ ዘመን በሙሉ ወታደር ልናቆም አንችልም። በስምምነት ካልሆነ በወታደር ነው የሚሆነው በወታደር ከሆነ ዘላቂ አይሆንም ጊዜ ይፈታዋል። አሁን ያለን ሰዎች ስናረጅ ስንደክም ልክ አሁን የተፈጠረው ይፈጠራል። ያ አካባቢ ሊለማ ስለሚችል ሰላማዊ በሆነ መንገድ ወደልማት እንዲገባ ቢደረግ ለኹሉም ጠቃሚ ይመስለኛል ። ብለዋል።

The post ”እኛ ደቡብ አፍሪካ የሄድነው ወልቃይት ወደ አማራ ይሁን ወደ ትግራይ ይሁን የሚለውን ለመወሰን አይደለም” ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply