እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመፍታት መንግስት በትኩረት እንዲሰራ የደብረታቦር ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 29 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ…

እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመፍታት መንግስት በትኩረት እንዲሰራ የደብረታቦር ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 29 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በአማራ ክልል ምክር ቤት የደብረታቦር ከተማ ህዝብን የወከሉት ወ/ሮ አለምነሽ ዋጋየ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተዉጣጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በልማት እና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የምክር ቤቱ የበጀት እና ፋይናስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አለምነሽ ዋጋየ እንደገለፁት የሕብረተሰቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ምክር ቤቶች ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው መሆኑን ተናግረው የከተመውን ህዝብ የወከልን በመሆናችን ያሉትን ችግሮች ወስደን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንሰራለን ብለዋል፡፡ የደብረታቦር ከተማ እና አካባቢው ህዝብ በህልውና ማስከበር ዘመቻው ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጉን ጠቅሰው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የከተመዋ የሪጂኦፖሊታንትነት ደረጃ ጥያቄ እንዲመለስ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ወ/ሮ አለምነሽ ተናግረዋል፡፡ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር እና የልማት ችግር ለመፍታት አመራሩ እና ባለሙያው በተገቢው ሁኔታ መስራት አለበትም ብለዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎችም በሰጡት አስተያየት የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር የስራ ሀላፊዎች እና ባለሙያዎች በተገቢው ሁኔታ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በህልውና ማስከበር ዘመቻው ላይ መሰዋትነት ለከፈሉ ወገኖች እና ለወጣቶች ፍትሀዊ በሆነ አግባብ የስራ እድል መፈጠር እንዳለበትም ገልፀዋል፡፡ የከተማዋን ፀጥታ ለማስፈን እና ወንጀልን ለመከላከል ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካሉ ጋር በጋራ መስራት አለበትም ብለዋል፡፡ በከተማችን ሰፊ የሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር በመኖሩ ሊስተካከል እንደሚገባም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተገኙት የደብረታቦር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባሻ እንግደው እንዳሉት የከተማዋን ልማት ለማስቀጠል እና እየታየ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመፍታት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ ዘገባው የደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ነው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply