ኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሩ የሲቪል ሰዎችን ደህንነት ለማስከበር በቂ የፀጥታ ኃይሎች በቋሚነት ሊሰማሩ ይገባል ሲል ኢሰመኮ አሳሰበ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 8…

ኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሩ የሲቪል ሰዎችን ደህንነት ለማስከበር በቂ የፀጥታ ኃይሎች በቋሚነት ሊሰማሩ ይገባል ሲል ኢሰመኮ አሳሰበ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ. ም አዲስ አበባ ሸዋ ጊዳ ኪራሙ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ የምስራቅ ወለጋ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በአስጊ ሁኔታ ይገኛሉ ያለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን_ኢሰመኮ ኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሩ የሲቪል ሰዎችን ደህንነት ለማስከበር በቂ የፀጥታ ኃይሎች በቋሚነት እንዲሰማሩ አሳስቧል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን_ኢሰመኮ በምስራቅ ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች የተለያዩ ወረዳዎች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በመስፋፋት ላይ መሆናቸውን ጠቅሷል። ችግሩ ይፈታ ዘንድም መንግስት በቂ የፀጥታ ኃይሎችን በአፋጣኝና በቋሚነት በአካባቢው ሊያሰማራ እንደሚገባም ኢሰመኮ አሳስቧል። ኮሚሽኑ መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጊዳ ኪራሙ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ የምስራቅ ወለጋ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በአስጊ ሁኔታ እንደሚገኙ ገልጧል። ወደ ወረዳው የሚወስዱ የተዘጉ መንገዶችን ማስከፈትን ጨምሮ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከፌዴራሉ ኃይሎች ጋር ሊቀናጁ እንደሚገባም ከአሁን ቀደም ማሳሰቡ ተወስቷል። ይህንኑ ግጭት በመሸሽ ከምስራቅ ወለጋ ሊሙ ወረዳ፣ ጉደያ ቢላ ወረዳ፣ ኪረሙ ወረዳ፣ ሌቃ ዱለቻ ወረዳ፣ በዲጋ ወረዳ፣ እና ከሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በአጠቃላይ 43,139 በላይ ሰዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙ የዞኑ የአስተዳደርና የፀጥታ አካላት ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ወደ እነዚህ አከባቢዎች የሚያደርሱ መንገዶች አሁንም ዝግ በመሆናቸውና በአከባቢው ያለው ውጥረት አሁንም ባለመርገቡ ምክንያት ሰዎች መሰረታዊ አቅርቦቶችንና ሕክምና ለማግኘት ጭምር በከፍተኛ ችግር ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ በተለይም የአካባቢውንም ሆነ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ስምሪት በተመለከተ በተደጋጋሚ እየታየ ያለው አንዱ ችግር የፀጥታ አስከባሪዎች አንድ አካባቢን ለቅቀው መሄዳቸውን ተከትሎ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መሆናቸውን ገልጧል። በመጨረሻም የአካባቢው ሰላምና ደህንነት ሙሉ በሙሉ እስከሚረጋገጥ ድረስ በቂ የፀጥታ ኃይሎች በተለይ ለግጭትና ጥቃት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ በቋሚነት ተመድበው መንግስት የሁሉንም ነዋሪዎች ደኅንነት የማስጠበቅና ከጥቃት መከላከል ግዴታና ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” ብለዋል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ አክለው፣ በግጭቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች አፋጣኝ የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስም አሳስበዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply