ኦነግ ሸኔ በሰሜን ሸዋ ደራ ወረዳ የገጠር ቀበሌዎች በንፁሃን ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መክፈቱ ተነገረ፡፡

የወረዳው አስተዳዳርም የሽብር ቡድኑን ጥቃት ለመመከት በቂ የፀጥታ ኃይል እንደሌለው ለጣቢያችን አስታውቋል፡፡
ከዚህ ቀደም በአሸባሪዉ ኦነግ ሸኔ ተደጋጋሚ ጥቃትን ሲያስተናግድ የቆየዉ ይህ ህዝብ አሁንም የሽብር ቡድኑ ንጹኃን ዜጎችን እየገደለ፤ እያፈነ፤ ንብረት እያወደመና እያቃጠለ እንደሚገኝ ነዋሪዎቹ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ድምፃቸዉን አሰምተዋል፡፡

የኦነግ ሸኔ አበላት ከባለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ወደ ወረዳዋ በስፋት በመግባት 16 የሚጠጉ የገጠር ቀበሌዎችን ተቆጣጥረዉ እንደሚገኙ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ቡድኑ በተቆጣጠራቸዉ የገጠር ቀበሌዎችም በርካታ ንጹኃን በአሰቃቂ ሁኔታ ጭምር እንደተገደሉ፤ ንብረታቸዉ እየተዘረፈባቸዉና ቤታቸዉ በአሳት እንደወደመባቸዉ የወረደዋ ነዋሪዎች ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ አስታዉቀዋል፡፡
የደራ ወረዳን ወደ አዲስ አበባ የሚያገናኘዉ መንገድ በሽብር ቡድኑ ቁጥጥር ስር በመዋሉ ዜጎች በነጻነት እንዳይቀሳቀሱ መሰራታዊ ሸቀጦችም እንዳይገቡ ከተደረገ ብዙ ጊዚያትን አስቆጥሯል ነዉ የተባለዉ፡፡

ይህ መስመር መዘጋቱን ተከትሎ የወረዳዋ ነዋሪዎች በአማራ ክልል መርሃቤት ወረዳ በኩል ወደ አዲስ አበባ ሲገቡና ሲወጡ የነበረ ቢሆንም በአማራ ክልል ባለዉ ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ያም መስመር ዝግ ሆኗል ተብሏል፡፡
እናም የደራ ወረዳ ነዋሪዎች ከጸጥታዉ ችግር በተጨማሪ ከፍተኛ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀዉስ ዉስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በተለይም በመንገዱ መዘጋት የጤና አገልግሎት ችግር በመፍጠሩ ነብሰ ጡር እናቶች ጭምር ህይዎታቸዉን እያጡ ነዉ ተብሏል፡፡
በወረዳዋ የገጠር ቀበሌዎች የሚኖረዉ ህዝብ የሽብር ቡድኑን ጥቃት ለመሸሽ ወደ ወረዳዋ ከተማ ጉንዶ መስቀል እየተሰደደ በመሆኑ የደረሱ ሰብሎች እየተበላሹ እንደሆነም ሰምተናል፡፡

እናም የክልሉም ሆነ የፌደራሉ መንግስት በአስቸኳይ ይድረስልን ሲሉ የደራ ወረዳ ነዋሪዎች ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል፡፡
እኛም ለመሆኑ ነዋሪዎቹ ያነሷቸዉ ጥያቄዎችና ስጋቶች ምን ያህል እዉነታ አላቸዉ የሚለዉን ለማጣራት የወረዳዉን አመራሮች ጠይቀናል፡፡
የደራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሺበሺ አያሌዉ በጉዳዩ ላይ ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ የሽር ቡድኑ ንፁሃን ላይ ጥቃት ከፍቷል በ8 ቀበሌዎች በስፋት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም አረጋግጠዉልናል፡፡

ይህ ቡድን በወረዳዋ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከሁለት አመት በላይ እንደተቆጠሩ ሰምተናል፡፡ በዚህም ብዙዎች ሞተዋል ታፍነዉ ተወስደዋል ከቤት ንብረታቸዉ ተፋናቅለዉ ተሰደዋል፡፡
ለመሆኑ ቡድኑን ከወረዳዉ ለምን ማስወጣት አልተቻለም? ለሚለዉ ጥያቄ ዋና አስተዳዳሪ ሲመልሱ “በወረዳዋ ያለዉ የፀጥታ ሃይል በቀ አይደለም” ነዉ ያሉት፡፡

በሽብር ቡድኑ መንገድ መዝጋትና በአማራ ክልል ባለዉ ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት በተዘጉት ሁለቱ መንገዶች ምክንያት በወረዳዋ የተፈጠረዉን የኢኮኖሚና የመህበራዊ ቀዉስስ ለመፍታት ከሚመለከተዉ አካል ጋር አየተሰራ እንደሆነም አቶ ሺበሺ ተናግረዋል፡፡

በአባቱ መረቀ

መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply