ኦነግ በሆሮ ጉድሮ ዞን አማራ በሆኑ የሃይማኖት አባቶች፣ በዲያቆናትና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ አሰቃቂ ግድያና እገታ ፈፀመ

ከውስጥ ተባባሪዎቹ፣ ስንቅና ትጥቅ አቀባዮቹ ጋር በመሆን የአማራን ዘር በማጥፋት ላይ የተጠመደው ኦነግ ሸኔ የተባለው የሽብር ቡድን የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በሆሮ ጉድሮ ዞን አቢ ደንጎሮ ወረዳ ንፁሃን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶችን፣ዲያቆናትንና በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ አማራዎችን በስለትና በጥይት መጨፍጨፉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ከስፍራው ያገኘናቸው ምንጮች እንደገለፁት ጥቃቱ የተፈፀመው በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሮ ዞን አቢደንጎሮ ወረዳ ዴቢስ ቀበሌ ባለእግዚአብሄር ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ነዋሪ በሆኑ አማራዎች ነው።
እስካሁን በደረሰን መረጃ መሰረት መርጌታ ጤናው የተባሉ አባት ከቤታቸው ታርደው ተገኝተዋል፤ ቄስ ማንደፍሮ ደሴ የተባሉ አባትም በጥይት ስለመመታታቸው ተገልጧል፤ ወ/ሮ ወርቅነሽ ማስረሻና ወርቅ ሰው ፍቃዴ የተባሉ ሁለት እናቶችም እንደተገደሉ ነው ምንጮች የገለፁት።
ዘግይቶ ከአቢ ደንጎሮ እንደመጣ የተነገረለት ከኦሮሚያ ልዩ ኃይልም አንድ አባል በተኩስ ልውውጥ መገደሉ ተሰምቷል።
በኦነጎች ታግተው አድራሻቸው ከጠፉት ከ29 በላይ አማራዎች መካከልም የቄስ ማንደፍሮ 4 ልጆች፣ የመርጌታ ጤናው፣ የወርቅነሽ ማስረሻና የወርቅ ሰው ፍቃዴ ቤተሰቦች፣ ብርሃኑ በላይ፣ በይን ደሳለኝ ከ 3 ልጆችጋር፣ ወርቁ ሹመት፣ ድንቄ ሹመት ከ4 ልጆች ጋር፣ አበዛሽ ሹመት ከ3 ልጆች ጋር፣ ዲያቆን አገኘሁ ሹመትና ሌሎች ከአሁን ቀደም በጃርዴጋ ጃርቴ ከተፈፀመባቸው መከራና ስቃይ ሸሽተው የመጡ አማራዎችም ብዛታቸውና ስማቸው ለጊዜው ባይታወቅም በሽብር ቡድኑ ታግተው ስለመወሰዳቸው ነው ነዋሪዎች የተናገሩት።
ታግተው ወደጫካ የተወሰዱት እጣፈንታም ከሞት ያለፈ ነው ለማለት በእጅጉ እንደሚቸግር የተናገሩት ምንጮች አስከፊ ጊዜ ላይ መድረሳቸውን ገልፀው ከሰው ይልቅ መሬትን ያስበለጠው መንግስት ለመታደግ እስካልቻለ ድረስ እባካችሁ ከአካባቢው በሰላም እንድንወጣ እርዱን ሲሉ ተማፅነዋል።
እየተደረገ ያለው ተደጋጋሚ ጥቃት መንግስት ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን ዘር እየለየ አማራን በመጨፍጨፍ ማፈናቀልና መዝረፍ ነው ብለዋል።
ከክልሉ ውጭ ያለው አማራ በተለይ በኦሮሚያ ወለጋና በመተከል አማራው በዘሩ ተመርጦ በጅምላ እየተረሸነ ቢሆንም የአማራ ብልፅግና ነኝ የሚለው መንግስትን ጨምሮ የኦሮሚያም ሆነ የፌደራል መንግስት ዜጎችን ለመታደግ አልቻሉም።

ምንጭ:- አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ

Source: Link to the Post

Leave a Reply