ኦፌኮ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም በተቀሰቀሰው ጦርነትና በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ግጭት በመባባሱ እጅግ ማዘኑን ገለጸ

በኹሉም ወገን ያሉ ተፋላሚ ሀይሎች ግጭቱን በማብረድ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲሹ ጠይቋል

ዕረቡ ነሐሴ 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አገራችንን ለከፍተኛ ሰብዐዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኪሳራ የዳረጋት ጦርነት ዳግም በሰሜን ኢትዮጵያ በማገርሸቱና በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ግጭት በመባባሱ እጅግ ማዘኑን ገልጿል።

ፓርቲው በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ”የእነዚህ ግጭቶች መባባስ እና መቀጠል ህዝቡን ዳግም ለከፋ ሞት እና መፈናቀል የሚዳርግ ከሆኑ ባሻገር ለንብረትና መሰረተ ልማቶች ውድመት የተዳረጉ አካባቢዎችን ለበለጠ አለመረጋጋት ይዳርጋል።“ ብሏል።

ጦርነት ለኢትዮጵያ ውስብስብ የፖለቲካ ችግሮች መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል የገለጸው ኦፌኮ፤ እነዚህ ችግሮች በዘላቂነት ሊፈቱ የሚችሉት በእውነተኛ እና ኹሉን አቀፍ ድርድር ብቻ መሆኑ ፅኑ እምነቱ መሆኑንም አስታውቋል።

ስለዚህም በኹሉም ወገን ያሉ ተፋላሚ ሀይሎች ግጭቱን በማብረድ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲሹ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ጠይቋል።

በተጨማሪም በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ኹሉ ተጨማሪ ሞት እና የዜጎችን መከራ ለማሰቀረት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በንቃት እና በተቀናጀ ልኩ እንዲረባረብም ጥሪ አቅርቧል።

አለም አቀፉ ማህበረሰብ በመላው ኦሮሚያ የተሰፋፋውን ጦርነት ለመፍታት ቀርቶ እውቅና ሊሰጠው አለቻሉን እንዳሳሰበው የገለጸው ኦፌኮ፤ በክልሉ በተለይም በግጭት እና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ያለው ሰብዓዊ ኹኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጿል። በመሆኑም የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ እየተባባሰ ያለው ግጭት በአስቸኳይ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በድርድር እንዲፈታ ኹኔታዎችንን እንዲያመቻች ጠይቋል።

በመጨረሻም ፖርቲው ከኢትዮጵያ ህዝብን፣ ገዥው ፓርቲን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሚዲያ ተቋማትን፣ የማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች እና አክቲቪስቶች ግጭቱን ከሚያባብሱ ንግግሮች እንዲታቀቡና ችግሩን ለማርገብና ለመፍታት በአንድ ድምፅ እንዲተባበሩ ጥሪውን አቅርቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply