ከአስራ-አምስት ቀናት በፊት ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ “…መከላከያንና ፖሊስን በሰው ሃይል አጠናክሩ… በፌስ ቡክ መጮሁ ኢትዮጵያን አይታደጋትም…፣” በሚል የድጋሚ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ባስታውስህ ምን ይመስልሃል? ይህችን ጥሪ በዚህ ወቅት ከጠ/ሚሩ የሰማሃት ለሁለተኛ ጊዜም እንደሆነ አትዘነጋውም፣ አይደል? በርግጥ ማንኛውም ዜጋ ለሃገሩ ዘብ የመቆም ሃላፊነት እንዳለበት አንተም እኔም አንስተውም። እንደውም በነዚያ በታደሉት ሃገራት ውስጥ የውትድርና ጥሪ የውዴታ ግዴታ ነው ሲባልም እንሰማለን። የኛም ሃገር ስዎች ይሄን መሳዩን ወታደራዊ ግዳጅ ለዘመናት ሲተገብሩት ቆይተዋል። ይሁን እንጂ፣ የአሁኑን ዘመን (የጠ/ሚውን ዓይነት) ጥሪ በመቀበሉ ረገድ ወጣቱ ቸልተኝነት ማሳየቱ (በርግጥም አሳይቶ ከሆነ) ‘በምክንያት ይሆን?’ የሚል ሃሳብ ብጤ በእዝነ-ልቦናዬ ሽው ይልብኛል። ወዳጄ፣ እንዴት የሚለውን ለመረዳት ከፈለክ ተከተለኝ።
የዛሬ ዓመት በሕዳር ወር ተመስገን ደሳለኝ በፍትህ መጽሄት ላይ (አንደኛ ዓመት ቁጥር 54 ህዳር 2012)፣ “መከላከያ የማን ነው፣” በሚል ርዕስ የጻፈውን ጽሁፍ ለአንድ አፍታ ላስታውስህ። እንዲህ ነበር የሚለው፤ “…የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐብይ አህመድ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ለማ መገርሳ [አሁን በቦታው ባይኖሩም በወንበራቸው ቀንዓ ያደታ ተተክተዋል]፣ ም/ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ [አሁን ዋናው ቦታ ላይ ተደላድለው እንዲቀመጡ ተደርጓል]፣ በሽግግር ወቅት ወሳኝ የሆነው የጥናትና ምርምር ሃላፊነት ብ/ጄ ተሾም ገመቹ፣ ቁልፍ ለሆነው አየር ሃይል አዛዥነት ብ/ጄ ይልማ መርዳሳ፣ ከግዙፍ የጦር አውሮፕላን እስከ ተራ የውሃ ኮዳ ገዝቶ የሚያቀርበው የሎጅስቲክስ መምሪያ ሜ/ጄ አብዱራህማን አደም፣ በርካታ የንግድ ድርጅቶችን ለሚያስተዳድረው የመከላከያ ፋውንዴሽን ሜ/ጄ ኩመራ፣ ከመከላከያ ተነጥሎ በላቀ ሚዛናዊነት የተደራጀው ‘ሪፐብሊካን ጋርድ’ ብ/ጄ ብርሃኑ በቀለ፣ የዘመኑ ኢንፎርሜሽን ውጤት የሆነው ወታደራዊ ተቋም ‘ኢንሳ’ አቶ ወርቁ፣ ብሔራዊ መረጃ ኮማንደር ደመላሽ… ዝርዝሩ አታካች ነው። እነዚህ ሁሉ ወሳኝ ሃላፊነቶች በአንድ ብሔር ተወላጆች ቁጥጥር ስር መዋላቸው ‘አጋጣሚ’ ተብሎ የሚታለፍ አይደለም። ከብሔሩ ልሂቃን ያደረ ዓላማ አኳያም መታየት አለበት። …” ይለናል ተመስገን ደሳለኝ!
ልብ አድርግ፣ ና እና መከላከያንና ፖሊስን አጠናክር የሚባለው በዚህ ዓይነት ከአንድ ብሔር ብቻ ተጠራርተው የወታደር ተቋሙን እየመሩ ባሉ ከፍተኛ መኮንኖች ስር በመሆን የ‘ግደል’ ትዕዛዝ ተቀብሎ ለመተግበር ነው። እነዚህ ወታደራዊ መኮንኖች ያራምዱታል ተብሎ የሚታሰበው የፖለቲካ አቋማቸው ደሞ በአንድ ብሔር የበላይነት ላይ መሰረቱን ያደረገ ነው። ተመስገን፣ “…ከብሔሩ ልሂቃን ያደረ ዓላማ አኳያም መታየት አለበት፣” እንደሚለው ማለት ነው። ይህም ሲባል ሰዎቹ አቋማቸው የአንድ ብሔር የብቻ ጥቅም እንጂ፣ የመላው ሀገር ብሔራዊ እንድነትና አብሮ መኖር አይደለም ተብሎ መጠርጠሩን ለማጉላት መሆኑን በፍጹም አትዘንጋ። ታዲያ በዚህ ዓይነት ውጥንቅጡ ለወጣ የውትድርና ስራ የትኛው ሃገር ወዳድ ዜጋ ነው ይመጣል ወይም ይቀጠራል ተብሎ የሚታሰበው! እንደ ሃገር ቅድሚያ መሰጠት ያለበትስ በየክልሉ፣ በተለይም በኦሮሚያ፣ በሚያስፈራ ሁኔታ እየተገነባ ያለውን ልዩ ሀይል ማፍረስ መሆን አልነበረበትም? በአሁኑ ሰዓት በየቦታው እንደ እብድ ውሻ እየተገደለ ያለውን መከረኛ አማራ ነብስ ይማር ለማለት በማይፈልግ ወይም በማይደፍር ሰው በሞላባት የጉድ ሃገር ውስጥ ማን ለማን እንዲሞት ተፈልጎ ነው የተመዝገቡ ጥሪ የሚደረገው?
ጌትዬ፣ ውትድርና በሌላው ሃገር ምን እንደሚመስል አብዝቼ ለአንተ ለመንገር አልሞክርም። ቢሆንም ትንሽ ልበል… ይሄ የተከበረ ሞያ በነዚያ በታደሉት ሃገራት ውስጥ የሚከናወነው ዘርና አጥንት እየተቆጠረ፤ ደም እየተመረመረ፣ የአያት ቅምአያት ስም በመደዳ እየተንበለበለ አይደለም። ሀገር የሁሉም ናትና በወታደሩ አጥንት ዳር ድንበሯ ይታጠራል፣ የህዝቧ ደህንነት የጠበቃል፤ ይልሃል የሌላው ሃገር ያማያወላዳ የውስጥ መመሪያ። የውትድርና መርህ ከሞላ ጎደል በዚህ ላይ የተመሰረተ ነው። የሌሎች ሃገሮች ወታደሮች የሚያምርና የሚያፈዝ የሰልፍ ትርዒት ከማድረግ ባሻገር ዜጎችን ከተፈጥሮ አደጋዎች ለመከላከል ውድ ህይወታቸውን እስከመክፈል የሚያደርስ የነፍስ-አድን ስራ በወኔና በሙሉ ፍላጎት ሲከውኑ ስታይ በርግጥም የየሃገራቱ መሰልጠን ያስቀናሃል። በዚህ በኩል ያለመታደልህም ያስቆጭሃል። በሌላው ሃገር በየመንገዱ የሚታዩት የሰራዊት አባላት በተራው ዜጋ፣ “ስላገለገልከኝ አመሰግንሃለሁ!” በሚል የአክብሮት ሙገሳ ይሰጣቸዋል፣ ሲባል ስትሰማ በርግጥም በመንፈስ ቅናት ተንገበገባለህ!። አዎን፣ በዛሬይቱ ጎስቋላዋ ኢትዮጵያችን ውስጥ ግን የዚህ ዓይነቱን የውትድርና ስርዓት ለማየት አልታደልንም። ይልቁንም፣ ዜጎችን ሰላማዊ ሰልፍ ለምን ወጣችሁ በሚል ብስናይፐር አናት አናታቸውን የሚበጠርቁ፣ በክላሽ ደረት ደረታቸውን የሚነድሉ፣ በቆመጥ መላ አካላቸውን የሚቀጠቅጡ፣ ጎበዝ ወታደሮች ነው ያሉን። ወዳጄ፣ በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በሐረር፣ በሶማሌና በወላይታ ሶዶ ላይ ንጹሃን ዜጎችን እያነጣጠረ በስናይፐር ሲገድላቸው የነበረ ወታደር የጣሊያን አለያም የአልቃይዳና የአልሸባብ ነው እንደማትለኝ እርግጠኛ ነኝ። ታዲያ ኑ እና በውትድርና ተቀጠሩ የሚባለው በነዚያ በዘረኝነት የጨለማ ጥግ ውስጥ በተወሸቁ ጄኔራሎች የሚተላለፉ ተመሳሳይ የግደሉ ትዕዛዞችን ተቀብሎ ለመተግበር ነው? እመነኝ፣ አማራ-ጠል የሆነውን የጄኔራል ጌታቸው ጉዲናን ተዕዛዝ እየተቀበሉ ወገናቸውን ለመግደል የጠመንጃ ቃታ መሳብ የማይፈልጉ ሃገር ወዳድ ወጣቶች ቁጥራቸው በአሁኑ ስዓት የበዛ ነው። አባቴ፣ በዘረኝነት ለናወዙ ወታደራዊ አዛዦች በአሽከርነት ወይም በገዳይነት ለመቀጠር የሚፈልጉ ወጣት ኢትዮጵያውያንን በዚህች ሰዓት ማግኝት የሚቻል አይመስለኝም!
በወለጋ ውስጥ በተለያዩ ዞኖች፣ በሻሸመኔ፣ በመተከልና በሌሎችም ቦታዎች ሰላማዊ ዜጎች ለ ‘ድረሱልንና፣ ለእባካችሁ ጥላችሁን አትሂዱ፣’ ጥሪያቸውና ልመናቸው ከመከላከያ ሰራዊቱ ይሰጣቸው የነበረው መልስ ምን እንደነበር ታስታውሳለህ? …“ከበላይ ትዕዛዝ አልደረሰንም፣” የሚል አስገራሚ ምላሽ አልነበረም? ይኽውልህ፣ እነዚህ የበላይ ወታደራዊ አዛዦች እነማን እንደሆኑ ታዘብ! አንድ ወታደር ይሄንን ካልሰራ፣ ወይም ወገኑን ከአደጋ ካልጠበቀ ምንድን ነው ሌላ ስራው? እንደዚህ ከሆነስ በአሁኑ ስዓት ኑ እና በውትድርና ተቀጠሩ የሚለው ተደጋጋሚ አድክም ጥሪ ምን የሚሉት ነገር ነው? ለተመሳሳይ የዜጎች የድረሱልን ጥሪ ተመሳሳይ፣ የ“ትዕዛዝ አልደረሰንም” መልስ የሚሰጡ ጀሌዎችን ለማበራከት! …ኧረ እይሰማም!!
ወንድሜ፣ ዛሬ የራሳችንን የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች ከመኪና ላይ ለማውረድ የማንችልበት ዘመን ላይ መሆናችንን አትርሳ! በራሳችን ሃገር በጋጠ-ወጦችና ስርዓተ-አልበኞች ማን አለብኝነት ምክንያት መኖር ያቃተን የምድር ጎስቋሎች እየሆንን ነው! መንግስት ተብዬው ቀጠርኩላችሁ የሚለን ፖሊሶች ለእንደዚህ ዓይነቶቹ ችግሮች የሚሰጡት ምላሽ ምን እንደሆነ ታውቀዋለህ። “ተስማሙ፣” የሚል የልግጫ መልስም አይደል! አዎ! …ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ በተገደለ ሰሞን በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች የታየው መከራና እልቂት በሃገር ውስጥ ‘መንግስት አለ ወይ’ የሚያስብልም አልነበር! ያን ጊዜ ከድንጋይ፣ ከዱላና ሜንጫ እየሸሹ ወደ ፖሊስ የተጠጉ ሰላማዊ ዜጎች ከጎጠኛ ፖሊሶች ምን ምላሽ ይሰጣቸው ነበር? ምንስ ተደረጉ? “…ዞር በሉ ከዚህ፣” በሚል አልተገፈተሩም! በቆመጥ አልተደበደቡም? በዚህ ዓይነት መንግስት የራሱን ዜጎችና ንብረት መጠበቅ ባልቻለበት ሃገር ላይ እየኖርን (መኖር ከተባለ) ስለመሆናችንስ ከቶ ማን ይጠራጠራል! ታዲያ እንደነዚህ ዓይነት የውትድርና ስራዎችን ለማከናወን ነው ዜጎች የሚጠሩት? በርግጥም ያንድ ክልል ጓደኛሞችና የጎጥ ስብስቦች በተጠራቀሙበት ተቋም ውስጥ ሌላው ዜጋ ለቅጥር የሚጠራው ለምንድ ነው? ትዕዛዝ እየተቀበለ ሰላማዊ ዜጎችን እንዲገድል? …ኧረ በጣም አይሰማም!
ከልጅነት እስከ ዕውቀት በረሃ ለበረሃ ተንከራተው ሃገራቸውን በታማኝነት በውትድርና ሞያ ያገለገሉ ዜጎች በየጎዳናው ተበትነው ባሉበት ሃገር ውስጥ ማን ነው ተመልምሎ መስዋዕትነት ለመክፈል የሚፈልገው! ለዚያውም ውንድሙን፣ እህቱን፣ እናቱን፣ ሌሎች ሰላማዊ ዜጎችን እንዲገድል? የሆነስ ሆነና፣ የእነሱ፣ የተገዳዮቹ ዕጣ ነገ በእርሱ በራሱ ላይ እንደማይደርስበት ምንድን ነው ማስተማመኛው? ዜጎች ዘራቸውና አጥንታቸው እየተቆጠረ ተወልደው ከኖሩበት ቀዬ በግፍና በገፍ በሚመነጠሩበት ሃገር፣ በዘረኝነታቸው አንቱ የተባሉ ጎጠኞች ከአማካሪ እስከ መሪ የአመራር እርከን ላይ በሞሉበት ተቋም ውስጥ ወጣቶች ለመቀጠር ፍላጎቱ ባይኖራቸው ሊደንቀን አይገባም።
በመጨረሻም ሃገሪቱን እንመራለን ለምትሉ ሁሉ… የውትድርና ጥሪውን ለጊዜው አቆዩት። ቅድሚያ ሊፈታ የሚገባው ችግራችን ይሄ አይደለም። ሃገር አደጋ በተጋረጠባት ጊዜ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወታደር መሆን እንደማያቅተው ታውቃላችሁ። ይልቁንም ሃገሪቱ እየስመጠች ካለችበት ማጥ ውስጥ ለማውጣት ፍላጎቱ ካላችሁ ጊዜ አታባክኑ። ከጎጥ ከረጢታችሁ ወጥታችሁ በዘር የተከፋፈለችውን ሃገር አንድ አድርጉ። የጎሳ ፖለቲካ በአውዳሚነቱ እንጂ በአልሚነቱ የትም ሃገር አይታወቅምና ለዚህ የሚሆን መፍትሄ አምጡ። ምክር ተቀበሉ። አትታበዩ! ይሄንን ለማድረግ አሁኑኑ ወደትግበራ ግቡ። በዙሪያችሁ በተኮለኮሉ አሮጌና ዘረኛ አማካሪዎቻችሁ እየተመራችሁ ሃገራችንን ወደ መቀመቅ አትክተቷት። ይህች ጥንታዊት ሃገር ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በእናነተ የደከመ አመራር ምክንያት ወደገደል አፋፍ እየተገፋች ነው። በማይመስልና በሰለቸ የውትድርና ጥሪና አንጀት ጠብ በማይል ዲስኩራችሁ አታዝጉን። ሃገር በባዶ ዲስኩር፣ በማስመሰል፣ በማጭበርበር፣ በንዝህላልነት፣ በአጥንት ቆጠራ፣ በምንቸገረኝነት፣ በ’ኮንቪንስና በኮንፊዩዥን’ አትመራም። ልብ አድርጉ… ትታችሁ የምታልፉት አሳፋሪና ጥቁር ታሪካችሁ በዚህች ቅጽበት እየተከተበ ነው!