You are currently viewing ከሁሉም ሰላም ይቀድማል !! ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች ሴት አባላት ጥምረት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች የተሰጠ የአቋም መግለጫ አሻራ ሚዲያ… ሰሜን አሜሪካ  በሃገራችን ኢትዮጵያ በሰሜኑ ክ…

ከሁሉም ሰላም ይቀድማል !! ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች ሴት አባላት ጥምረት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች የተሰጠ የአቋም መግለጫ አሻራ ሚዲያ… ሰሜን አሜሪካ በሃገራችን ኢትዮጵያ በሰሜኑ ክ…

ከሁሉም ሰላም ይቀድማል !! ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች ሴት አባላት ጥምረት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች የተሰጠ የአቋም መግለጫ አሻራ ሚዲያ… ሰሜን አሜሪካ በሃገራችን ኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል እንደ አዲስ ያንዣበበውን ጦርነትና እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎቻችን ሁኔታ፣ ይህንን ተከትሎ የተፈጠረው የኑሮ ውድነትና አጠቃላይ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ቀውስ እና ለሃገሪቷ ችግሮች መፍትሄ ያመጣል ተብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረውን የብሄራዊ ምክከር አስመልከቶ ጥምረቱ በተለያየ ጊዜ ውይይቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። በሃገራችን በለውጥ ማግስት በመንግስት ተስፋ ሰጪ ውሳኔዎች ተወስነዋል፡፡ በዚህም የፖለቲካ እስረኞች፣ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ከእስር ተፈተዋል፡፡ የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር ይረዳሉ የተባሉ የህግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፤ ይሁን እንጂ በለውጡ ማግስት ጋብ ብሎ የነበረው የፖለቲካ ቀውስ ብዙም ሳይቆይ የዜጎች ሞት፣ መፈናቀል ፣ ረሃብ ፣ የኑሮ ውድነት ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ በፌደራል መንግስትና በህውሃት መካከል የተጀመረው የእርስ በርስ ጦርነት ባለፈው አስራ ስምንት ወራት በሃገራችን ከተከሰቱ ፖለቲካዊ ቀውሶች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ጦርነቱ ሃገራችንን በሰው ህይወት መጥፋትና በንብረት ውድመት እጅግ ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ህይወት ተቀጥፏል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ አያሌ ሴቶች፣ህፃናትና አረጋዊያን ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል፤ በተለይም ሴት እህቶቻችን ለፆታዊ ጥቃት እንዲሁም ሰብዓዊ ክብራቸው ተደፍሯል፡፡ ጦርነቱ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ ስራ አጥነት፣ስደት፣የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ፣ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት በባንኮችና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የጎላ ክፍትት በመፍጠሩ የጥቁር ገበያው ህገወጥነት ይበልጡኑ ተስፋፍቷል፡፡ ባለፉት ጊዜያት ሃገራችን ከደረሰባት ሰብአዊ፣ ቁሳዊና የስነ ልቦና ስብራት ሳታገግም ለዳግም ግጭት መነሳት በማንኛውም መመዘኛ በተለይም እኛ ለችግሩ ዋነኛ ተጋላጭ በሆንን ሴቶች ተቀባይነት እንደሌለው ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ለሚቀሰቀስ የእርስ በእርስ ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጎዱት ሴቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም ያንዣበበው ጦርነት ዳግም እንዳይቀሰቀስ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ በተጨማሪም መንግስት ህግን ማስከበር ባለው ሂደት ውስጥ ያለው የእስር ግልጽነት አለመኖር፣ የተፋጠነ ፍትህ ያለመሰጠት ሁኔታ፣የታሳሪዎች ሰብአዊ መብትና ደህንነት አለመጠበቅ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ፡፡ ለዚህም መንግስት የተለያዩ የመፍትሔ አቅጣጫዎችንና ስራዎችን እየሰራሁ ነው ቢልም ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አንፃር ስንገመግመው ከባህር በጭልፋ የመቅዳት ያክል ነው፡፡ በመሆኑም መንግስትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ የበኩላቸውን ሚና በመጫወት ሃገሪቷ ከገባችበት አስከፊ ችግር እንድትወጣ ማድረግ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት ጥምረት የሃገራችንን ዘመን ተሻጋሪ ችግሮች አሁናዊ ምክንያቶች ለመፍታት ሁሉን አካታች ብሄራዊ ምከከር በአፋጣኝ መደረግ አለበት ብሎ ያምናል ለተግባራዊነቱም የሚጠበቅብንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ለስኬታማነቱ ሃገራዊ ግዴታዎቻቸውን እንዲወጡ እየገለጽን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት ጥምረት የሚከተሉትን ባለ8 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል። 1. የኢትዮጵያ መንግስት፣ህውሃት እና ኦነግ ሸኔ የሰላም አማራጭ እንዲከተሉ ጥሪ እያአቀርብን ጦርነት ለማንም ጠቃሚ ባለመሆኑ ከየትኛውም ወገን የሚነሳ የጦርነት ጉሰማ የምንቃወም መሆኑን እናሳውቃለን። እንዲሁም የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሃገሪቷን ሠላም በሚያደፈርስ መልኩ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ 2. በማንኛውም ሁኔታ ለሚቀሰቀስ የእርስ በእርስ ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጎዱት ሴቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም እንደ አዲስ ያንዣበበው ጦርነት ዳግም እንዳይቀሰቀስ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ 3. በቀደመው ጦርነት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ፣በከፍተኛ እንግልትና ርሃብ ውስጥ ላሉ ዜጎቻችን ከመንግስት አስቸኳይ ሰብዓዊና የህይወት አድን ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንጠይቃለን፡፡ 4. በኢትዮጵያ የተጀመረው ብሄራዊ መግባባት ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም በሃገርም በውጭም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፤ መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሃገር ሽማግሌዎችና እናቶች፣ ባህላዊ መሪዎች፣ ሃገር በቀልና አለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን አወንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረከቱ እንዲሁም ብሄራዊ ምክከሩን አስመልከቶ የተቋቋመው ኮሚሽን ብሔራዊ ምክክሩ ሁሉን አካታች፤ ግልፅና ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲቀጥል እና ውጤታማ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ እንጠይቃለን ፡፡ 5. እንደሴት ፖለቲከኞች ጥምረት በየጊዜው በሴት እህቶቻችን ላይ የሚፈፀም ግድያና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በመንግስት በኩል የቅድመ መከላከል ስራ እንዲሰራ፣ ጥቃት እንዲቆምና ለችግሩም ተመጣጣኝ ፍትህ እንዲሰጥ ስንል አንጠይቃለን ፡፡ 6. በሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ እየናረ የመጣውን የዋጋ ግሽበትና የትራንስፖርት ችግር በማህበረሰቡ የኑሮ ሁኔታ ላይ አስከፊ ተጽእኖ እያሳደረ በመሆኑ ችግሩ በመንግስት በኩል አስቸኳይ መፍትሔ እንዲበጅለት እንጠይቃለን። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት እንዲባባስ የሚያደርጉ ገበያውን የተቆጣጠሩ ህገወጥ ደላሎችና ሃላፊነት የጎደላቸው ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ጊዜውን የጠበቀ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡ 7. መንግስት በተለያየ ጊዜ ህግ ማስከበር መስረታዊ ግዴው መሆኑ እሙን ነው። ነገር ግን በህግ ማስከበር ሂደቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ማለትም በቁጥጥር ስር የሚውሉ ግልሰቦች የእስር ሂደት ግልጽ አለመሆን፤ የእስር ሂደቱ የህግ አግባብን በተከተለ መልኩ አለመሆን፤ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግልሰቦች በአፋጣኝ ለፍትህ ተቋማት ቀርበው ውሳኔ አለማግኘት፤ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች አለመከበር፤ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል ናቸው። በመሆኑም መንግስት በየትኛውም ሁኔታ መሰረታዊ የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች እንዲያከብር አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ 8. መንግስት በአጠቃላይ በሀገራችን ኢትዮትጵያ በየትኛውም ቦታና ሁኔታ በዜጎች ላይ የሚደርስን ጥቃት ባስቸኳይ እንዲያስቆም እንጠይቃለን፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት ጥምረት ግንቦት 24/2014 ዓ.ም አዲስ አበባ

Source: Link to the Post

Leave a Reply