“ኢትዮጵያዊያን እያሉ ኢትዮጵያን ፈጽሞ ማሸነፍ የሚታሰብ አይደለም። ያሸነፈው ይህ የድልና የጀግንነት ባለቤት የሆነ ባለ ታሪክ ታላቅ ሕዝብ ነው፤ ያሸነፈው የኢትዮጵያ እናቶች ፀሎትና እንባ ነው።”
ዶር ዐብይ አሕመድ፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስተር
ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን መንግሥት አመራር፤ በተለይ ጀግናውን፤ ሕብረብሄሩን፤ አገር ወዳዱን የኢትዮጵያን መከላከያ ኃይል የሚተቹት ፈረንጆች ከአድዋ ጦርነት በኋላም ሊዋጥላቸው ያልቻሉት ጉዳይ አለ። በሃገር መስፈርት ብንገመግማት፤ ለድርድር የማትቀርበው ኢትዮጵያ! ኢታሊ፤ ጀርመኒ፤ ፍራንስ፤ ሮማንያ፤ አሜሪካ ወዘተ ከመመስረታቸው በፊት የተመሰረተችና የታወቀች አገር ናት። ይህች አገር በጠቅላላ የአገርና የነፍስ ወከፍ ገቢ ድሃና በቴክኖሎጅ ልማት በኩል ገና በማደግ ላይ መሆኗ ይህን አስደናቂ ታሪኳን ሊንደው አይችልም።
የምእራብ አገሮች፤ በተለይ ከተወሰኑት ውጭ የአውሮፓ መንግሥታት፤ ጩኸት የሚያሰሙትና ጫና የሚያደርጉት ለትግራይ ኢትዮጵያዊው ድሃ ሕዝብ ተቆርቁረው ሳይሆን፤ ከጀርባ የሚመኩበት ዋና መሳሪያቸው የሚለግሱት እርዳታ ስለሆነ ነው። የረሱት ሃቅ ግን፤ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ በውስጥ ጉዳያቸው፤ በነጻነትና በብሄራዊ ክብራቸው፤ በሉዓላዊ መብታቸው የማይደራደሩ መሆናቸውን ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቀርቶ፤ ድሃ ሆኖ እንኳን በብሄራዊ ነጻነቱና በክብሩ ፈጽሞ ተደራድሮ አያውቅም። ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት “ይህ ታላቅ ሕዝብ፤ ዘውግና ኃይማኖት ሳይለይ፤ በዘመናዊ መሳሪያ እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመጣውን የአሮፓ ሰራዊት ሽንፈት ተከናንቦ እንዲመለስ በማድረግ ታላቅነቱን ያስመሰከረ ሕዝብ ነው።” የአውሮፓ አገሮች በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ አግባብ የሌለው ጫና ለማድረግ የሚችሉበት መረጃ ፈልጌ ለማግኘት አልቻልኩም።
ስመራመረው ያለው ሃቅ እንደሚከተለው ነው። እኔ ዓለም ባንክ በነበርኩበት ወቅት፤ ህወሓት እየመረጠ ታማኝ አባላቱን በዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዳሰማራ አውቃለህ። የኢትዮጵያን ኤምባሲዎች የራሱ ድርጅት መገልገያ እንዳደረጋቸው አስታውሳለሁ። የዘረፈውን የውጭ ምንዛሬ እየተጠቀመ ዓለም አቀፍ የሃሰት መረጃዎች ስርጭት መረብ (Global network of diinformation) ዘርግቷል። የትዊተር ዘመቻው ስኬታማ የሆነበት ምክንያት ለብዙ ዓመታት በዘረጋው መረብ የሚካሄድ ነው። የተለየ ትኩረት ያደረገው በአውሮፓ ፓርላማ፤ በአሜሪካ ምክር ቤት፤ እንደ ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ማእከል፤ አልጀዚራ፤ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ባሉት ስብስቦች ላይ ነው። ለምሳሌ፤ በትግራይ ሕዝብ ላይ “ጦርነትና የዘር እልቂት እየተካሄደ ነው” የሚለው ከእውነቱ የራቀ ትርክት።
በኢትዮጵያ በኩል ግን፤ የተቀነባበረ እንቅስቃሴ አይታይም። ዲያስፖራው አሁንም የተከፋፈለ ነው (It is hopelessly fragmented). ሃቁ የሚያሳየው የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይልና የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ፍትሃዊ መሆናቸውን ነው። ግን ይኼ ብቻውን አይሰራም። ወደ መሬት መውረድ አለበት። ጦርነቱን የጀመረው ህወሓት ነው። ክህደቱን ያካሄደው ህወሓት ነው። እልቂት የሚያካሂደው ሀወሓት ነው። ሃሰት ሴና የሚያሰራጨው የህወሓት መረብ ነው።
ሌላው ሃቅ፤ በኢትዮጵያና በመላው ህዝቧ ላይ የተከሰተው ችግር የህልውና ጥያቄ መሆኑ ነው። ችግሩን የፈጠረው ከሃዲው ቡድን ህወሓት ነው። ይህ መሰሪ፤ ከሃዲ፤ ጠባብ ብሄርተኛ፤ ጨካኝ፤ ሽብርተኛና ዘራፊ ቡድን የጸነሰው እቅድ ስኬታማ ቢሆን ኖሮ ምን ይከሰት ነበር?
- የአገር ውስጥና የውጭ ጠላቶች የሚመኙትና የሚፈልጉት ኢትዮጵያን የማፈራረስ (Balkanization of Ethiopia) እቅድ ስኬታማ የሚሆንበት እድል ይፈጠር ነበር፤
- ህወሓት፤ ኦነግ ሽኔ፤ የእስልምና አክራሪ ኃይሎችና የኢትዮጵያ የውጭ ጠላት ተባባሪዎች የሚመኙትና የሚፈልጉት አንዱን ዘውግ ከሌላው ዘውግ፤ አንዱን ኃይማኖት ከሌላው ኃይማኖት ተከታዮች ጋር በማጋጨት ከማይካድራ እልቂት የባሰ የእርስ በእርስ ጦርነትና እልቂት ሊከሰት የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር፤
- ህወሓት የአገር ውስጡን የሰላምና የእርጋታ መደፍረስ ችግር እያስፋፋው ይሄድና፤ የኤርትራም መንግሥት እጅ አለበት በሚል ሰበብ ጦርነቱ የአፍሪካን ቀንድ በሙሉ እንዲበክለው የማድረግ ምኞቱና እቅዱ ስኬታማ ይሆን ነበር።
የምእራብ ተቋማትና አንዳንድ የአውሮፓ መንግሥታት በሰከነ ሁኔታ ያልተመራመሩት ይህንን የከበባ አደጋ ነው። አደጋው የኢትዮጵያን ህልውና ይመለከታል የምልበት ምክንያትም ይኼው ነው። ህወሓት ሆነ ኦነግ ሸኔ፤ የእሥልምና አክራሪዎች ሆኑ የኢትዮጵያ ጠላት መንግሥታት ግጭቶቹ ማንን ይጎዱ ይሆን ወደሚል ስሌት ገብተው አያውቁም። ለምሳሌ፤ በትግራይ ክልል የተካሄደውን ግጭት ቀረብ ብለን ብንመራመረው በከፍተኛ ደረጃ የተጎዳውና የሚጎዳው ተራው፤ ድሃው የትግራይ ኢትዮጵያዊው ሕዝብ ነው። ከሃዲዎቹ ወይንም የጁንታው አባላት ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከአገር ቤት እያወጡ በገፍ በዘረፉት ኃብት እየደጎሟቸው ነው። ድሃውን ዜጋ ለአደጋ አጋልጠው የእነሱን የቅርብ ቤተሰቦች ማውጣታቸው በራሱ መስፈርት መሆን አለበት።
በተመሳሳይ፤ የህወሓት ደጋፊ የትግራይ ኢትዮጵያዊያን ግዴታ ህወሓት የሚያካሂደው ጦርነት ለትግራይ ክልልና ሕዝብ፤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ሸክሞችን እንዳወረሰ መረዳት ነው። ለምሳሌ፤ ገቢና የስራ እድል የሚፈጥረውን ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ህወሓት ሲያወድመው ያወደመው ልማትን ነው። ያወደመው የገቢና የስራ እድልን ነው። አግባብ የሚኖረው መረባረቢያ ጉዳይ፤ የምእራብ ተቋማት፤ መንግሥታት፤ አበዳሪና ለጋስ ድርጅቶች፤ በመላው ዓለም የሚኖረው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በጋራ ሆኖ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደፊት የሚያካሂደውን የመልሶ ማቋቋምና መገንባት ስራ መደገፍ ነው።
ይህን ለማድረግ ደግሞ ቅድመ ሁኔታ አለ። ሰላምና እርጋታ ይባላል። ሕግን የማስከበር ግዴታ ይባላል። እነዚህ ቅድመ ሁኒታዎች ከሌሉ እንዴት መልሶ ማቋቋምና መልሶ መገንባት ይቻላል?
የምእራብ ተቋማትና ሌሎች ለህወሓት ወገንተኛ የሆኑት አካላት እንዲያጤኑት የምጠቁመው ከእነሱ ይልቅ ለትግራዩ ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ሰላም፤ ደህንነት፤ ኑሮ፤ መልሶ መቋቋምና ከዚያም ዘላቂ ልማት በመጀመሪያ ደረጃ የሚሰራው ወንድምና እህቱ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የኢትዮጵያ መንግሥት መሆናቸውን ነው። እርዳታ ያለ ሰላም የሰራበት አገር የለም። እርዳታ ያለ ሃላፊነት የሰራበት አገር የለም። በተጨማሪ፤ ፈረንጅዎች በሚለግሱት ሳንቲም ኢትዮጵያ ብትለማ ኖሮ፤ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት የተገኘው ግዙፍ እርዳታ እመርታዊ ለውጥ ያስገኝ ነበር። የውጭ ምንዛሬ ተዘርፏል። ከአገር ሽሽቷል። የህወሓት ደጋፊዎች የሃሰት ትርክቱን በመላው ዓለም ስኬታማ ለማድረግ የቻሉት ህወሓት በዘረፈውና ከአገር ባሸሸው ግዙ የውጭ ምንዛሬ ድጋፍ ነው።
የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ፎርብስ ያደረገውን አንድ ጥናት ብቻ ቢመለከቱት ደህና ነበር። ከጥቂት ዓመታት በፊት የተደረገው ጥናት ህወሓት መራሹ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ መንግሥት ብቻ ያገኘውን “$30 ቢሊየን የውጭ እርዳታ” ሙሉ በሙሉ በሆነ ደረጃ ባለሥልጣናቱ እንደ ዘረፉትና ከአገር እንዳሸሹት ዘግቧል። ይህ ግዙፍ እርዳታ ለልማት ቢውል ኖሮ፤ የትግራይ ኢትዮጵያዊ የሚጠጣው ውሃ ይኖረው ነበር። ወጣቱ የስራ እድል ይኖረው ነበር። እኔን የሚዘገንነኝ፤ አብዛኛውን የለገሱትን የውጭ ምንዛሬ የዘረፈው ህወሓት መሆኑን ለመቀበል መቸገራቸው ነው። ሌብነት መኖሩን ቢገነዘቡም እርምጃ የወሰዱበት ጊዜ ፈልጌ አላገኘሁም። ራሳቸው እንደሚሉት የእነሱ እንባ “የክሮኮዳይል እንባ” ነው።
ተጨማሪም ትዝብት አለ። ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታትን ከመሰረቱት አገሮች መካከል አንዷ ናት። የአፍሪካን አንድነት ድርጅት መስርታለች፤ አስተናግዳለች። ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለዓለም የወል ደህነነት (International Collective Security) ከፍተኛ አስተዋፆ ካደረጉት የተወሰኑ አገሮች መካከል የአንበሳውን ድርሻ የያዘች አገር ኢትዮጵያ ናት። የኢትዮጵያን ደህንነት ከዚህ አንጻር እንዲመለከቱት እጠቁማለሁ። ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ የተናገሩትን ላስታውስ። “ኢትዮጵያዊያን በሰላም አስከባሪነት ረገድም ከኮሪያ ልሳነ ምድር (The Korean Peninsula)፤ ከሰሜን አፍሪካ እስከ ደቡብ ምስራቅና ምእራብ አፍሪካ ሃገራት ድረስ ሰላምን በማስከበር ትልቅ ሚናን የተጫወተ ታላቅ ሃገርና ሕዝብ መሆኑን ለወዳጆቻችንም ሆነ ለጠላቶቻችንም ቁጭ ብለው እንዲማሩ ልንነግራቸው እንወዳለን።”
የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አባላት በዳርፉር፤ በደቡብ ሱዳን፤ በሶማልያ የሚጫወቱትን የሰላም አስከባሪነት ሚና የምእራብ መንግሥታት ሊረሱት አይችሉም። ይህ ሲሆን ደግሞ ማጤን የሚገባቸው ይህችን ታላቅ አገርና ጀግናውን ሕዝቧን የከዳውንና ወንጀለኛውን ቡድን፤ ህወሓትንና ጅራት ሆኖ እልቂት የሚያካሂደውን አጋር ኦነግ ሽኔን መከላከል ከመቸ ወዲህ ነው አግባብ የሌለው እርምጃ ሊሆን የቻለው? ብለን የመጠየቅ መብትና ግዴታ ያለብን መሆኑን አሰምርበታለሁ። ለሃገሩና ለመላው ሕዝቡ ቃል የገባው የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል ዋናው ሚናው የአገሪቱን ግዛታዊ አንድነት፤ ነጻነትና ሉዐላዊነት ማስከበር መሆኑን ረስተውት አይመስለኝም። ከረሱት ማስታወስ ያለብን ውጭ የምንኖረው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጭምር ነን። ይህን ለማድረግ የምንችለው ደግሞ ስንተባበርና እየተናበብን ስንሰራ ብቻ ነው።
ህወሓትና አጋሮቹ ያቀዱትን ስኬታማ ቢያደርጉ ኖሮ፤ ከላይ በገጽ አንድ ከአንድ እስከ ሶስት ያቀርብኳቸው ሁኔታዎች ይፈጸሙ ነበር። ኢትዮጵያ የመፈራረስ እድሏ ከፍተኛ ነበር። በህወሓት ከሃዲነትና አገራችንን ከማፈራረሱ አደጋ የማዳን ሂደት ከታሪክ አንጻር እንገምግመው። በአሜሪካ ከ1861-1865 በተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት በዝቅተኛ ሲገመት 750,000 አሜሪካኖች ሰለባ ሆነውበታል። አብዝኛዎቹ የሞቱት ከቆሰሉ በኋላ “የህክምና እንክብካቤ ቶሎ ስላላገኙ ነው” የሚሉ የታሪክ ባለሞያዎች አሉ። ቁም ነገሩ ግን፤ አሜሪካ ከሁለት እንዳትከፋፈልና አንድ ጠንካራ፤ የስለጠነች፤ ኃብታም፤ ሕበረብሄራዊና ዲሞክራሳዊ አገር እንድትሆን መስዋእት መከፈሉን ለማስታወስ ነው። ጦርነቱን የመሩት ፕሬዝደንት አብራሃም ሊንኮሎን አሜሪካን ታላቅ አገር ካደርጓት አባትና መስራች መሪዎች መካከል ከፍተኛ ቦታ ይዘዋል።
በቀውጢ ቀን ብልሃተኛና ቆራጥ መሪ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ኢትዮጵያም በታሪኳና በቀውጢ ቀን ታላላቅ መሪዎችን ያፈራች አገር ናት። የውስጥ ችግሮቻችን ወደ ጎን ብንተዋቸው ኖሮ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ ኢትዮጵያን በፈተናው ወቅቷ የመሯት በብልሃትና በጥንቃቄ መሆኑን አስመርበታለሁ፤ አምንበታለሁ። የፈለገውን ያህል ትችት ብታቀርቡ መብታችሁ ነው። እኔ ግን በዚህ የፈተና ወቅት ይህችን ታላቅ አገር መምራትና ከደረሰባት አደጋ ማላቀቅ ከፍተኛ የመሪነት መስፈርትን አሟልቷል እላለሁ። ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ የሚመሩት መንግሥት፤ የመከላከያው ኃይል፤ ፋኖ፤ የዐማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሽያ፤ የአፋር ልዩ ኃይል፤ ወዘተ እየተናበቡ ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ብቻ ሳይሆን ከከፋ ወይንም ከሩዋናንዳ ከባሰ የእርስ በእርስ ጦርነትና እልቂት በማዳን ላይ ናቸው። ለዚህ ታሪካዊ አስተዋፆ አድናቆቴን እገልጻለሁ፤ በሞያየ ድጋፌን እለግሳለሁ።
የምእራብና የሌሎች አገሮች ታዛቢዎች፤ በተለይ መገናኛ ብዙሃን፤ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከተደረገው ሴራ መስፈርት አንጻር ለማየት እንዴት አልቻሉም ብለን እንጠይቅ። ህወሓትና ኦነግ ሸኔ በተከታታይና በአጋርነት የፈጸሟቸውን ወንጀሎች ባጭሩ ልጥቀስ።
- የነፍስ ግድያዎችን ማካሄድ፤ የስቃይ ቅጣት መፈጸም፤ በተለያዩ ቦታዎች ዋሻዎችን፤ ማጎሪያዎችን፤ እስር ቤቶችን እየሰሩ በብዙ ሽህዎች የሚቆጠር፤ በተለይ የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ራያና ሌሎች የዐማራ ብሄር ሕዝብን በድብቅ እንደ ናዚዝቶች መግደልና ማሰቃየት፤ ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀል፤ መሬትን መንጠቅና የትግራይ ተወላጆችን በምትካቸው ማስፈር፤ አንዱን ዘውግ ከሌላው ጋር ማጋጨት፤ ጀኖሳይድ (የዘውግ እልቂት) ማካሄድና ጭፍጨፋውን መካድ፤ ሌብነትንና ሙስናን መመሪያ አድርጎ መዝረፍ፤ ግዙፍ የውጭ ምንዛሬን ከአገር ማሸሽ፤ ከውጭ ኃይሎች ጋር ሴራ ማካሄድ፤ የሃገር ክህደትን መፈጸም ወዘተ የመሳሰሉ ወንጀሎችን አካሂዷል።
- እነዚህ ወንጀሎች ሁሉ በመረጃ የተደገፉ ናቸው። ለምን ከምእራባዊያን ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን ሽብርተኞችን የሚያወግዝ ድምጽ አልሰማንም? የአሮፓ ፓርላማ፤ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና ኮሚሽነር፤ ሴናተር ካርደንና ሌሎች ትችት አቅራቢዎች ለምን ይህን ሃቅ ትኩረት ከመሰጠት ተቆጠቡ?
- ስንት ንጹህ ኢትዮጵያዊያን እስኪጨፈጨፉ ይጠብቃሉ?
- ኢትዮጵያ ሌላዋ ሶርያ፤ ሌላዋ የመን፤ ሌላዋ ሶማልያ፤ ሌላዋ ደቡብ ሱዳን እንድትሆን ነው የሚፈልጉት ማለት ነው? አይመስለኝም።
ግብዝነት ቀላል ቃል ነው። ቸልተኛነትም ቀላል ቃል ነው። ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ ደህንነት ካሰቡ ትችቱን ትተው አጥፊዎቹ እንዲያዙና የዘረፉትን ግዙፍ ኃብት እንዲመለሱ ቢረዱ የኢትዮያን ሕዝብን አድናቆት ሊያገኙ ይቾላሉ። ለምሳሌ፤ የአሜሪካ ፕሬዝደንት በጭፍጨፋና በሙስና የተከሰሱና መርጃ የተገኘባቸውን የውጭ አገር ወንጀለኞች በሃላፊነት የመያዝና የመጠየቅ መብት አለው (Magnitsky Act). ህወሓት ወንጀል ፈጽሟል፤ ለምሳሌ ማይ ካድራ የተካሄደው እልቂት። ከኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ የዘረፈው ግዙፍ ኃብት። ይህን ለማድረግ የሚቻልበት እድል አለ። አለያ ግን፤ እጃችሁን ከኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ሰብስቡ እላለሁ።
ግብዝነት ሲነግስ (The triumph of hypocrisy)
ህወሓት የቀሰቀሰው ከሃዲነትና የተቀነባባረ እልቂት ያስተማረን አስኳል ጉዳይ አለ። ይኼውም፤ የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት የሚተቹት መንግሥታት፤ ድርጅቶች ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን ሁለት መስፈርት ይጠቀማሉ፤ አንዱ ለምእራባዊያን፤ ለነሱ ለሚያጎበድዱና ለሚያገለግሉ የሚረዳ፤ ሁለተኛው፤ ለጥቁር አፍሪካ አገሮች የሚጎዱ። በኢትዮጵያ ላይ የሚካሄደው ሁለተኛው ነው።
ሽብርተኞች በለንዶን፤ በፓሪስና በሌሎች ከተማዎች እልቂት አካሂደዋል። ድርጊቱን በጋራ አውግዘዋል። በመቀሌ፤ በማይካድራ፤ በሻሸመኔ፤ በወለጋ፤ በቤኒ=ሻንጉል ጉሙዝ ዘውግ ተኮር እልቂት ተካሂዷል። እነዚህን ወንጀሎች የጸነሰው፤ ያቀነባበረው፤ የመራውና የፈጸመው ህወሓት ነው፤ አጋሩ ኦነግ ሽኔ ነው። እነዚህን ወንጀሎች ወደ ጎን ትተው ቅድሚያ የሰጡት ግን የኢትዮጵያ መንግሥትና መከካለከያ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት አካሂደዋል የሚል ትርክት ነው። በያንዳንዱ የምእራብ አገር በአንድ ጠቅላይ ግዛት፤ ለምሳሌ፤ በቫርያ (ጀርመኒ) የክፍለ ሃገሩ የመከላከያ ክፍል አልታዝዝም ብሎ ወንጀል ቢፈጽም ኖሮ ምን ይሉ ነበር? የጀርመን ሕዝብ በአንድ ድምጽ ድርጊቱን ይኮንነው ነበር። በቴክሳስ (አሜሪካ) የክፍለ ሃገሩ ብሄራዊ የዘብ ጠባቂ ኃይል (The State National Guard) በአሜሪካ የመከላከያ ኃይል አባላት ላይ ግድያና የመሳሪያ ዝርፊያ ቢያካሂድ ምን ይሉ ነበር? ወዘተ። የአሜሪካ ሕዝብ በአንድ ድምጽ ያውግዘው ነበር። በሁለቱም አገሮች የፌድራል መንግሥታት መሪዎቹ ሃላፊነት ሽብርተኞቹን መያዝና ለፍርድ ማቅረብ ነው።
ቁም ነገሩ ለጥቁር አፍሪካ የሚጠቀሙት መስፈርታቸው ግብዝነት የሚያሳይ መሆኑ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢትዮጵያ መከላከያ አባላት በትግራይ የሚያካሂዱት የሰላምና የእርጋታ ማስከበር እንቅስቃሴ በንጹሃን ዜጎች፤ በግል፤ በሕዝብና በመንግሥት ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የሚያደርጉት እጅግ የሚያስደንቅ እንቅስቃሴ ለምን ትኩረት አልተሰጠውም? ከአጥፊው ከህወሓት መንጋጋ ነጻ የወጡት ወገኖቻችን የሚሰጡትን አወንታዊ ግብዓት ለምን አላመኑትም? የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን መንግሥትና የራሱን መከላከያ ኃይል አባላት ወደ ጎን ትቶ ፈረንጆችን ለማመን የሚገደድበት ምክንያት ምንድን ነው?
ትችት የሚያቀርቡት ሁሉ ጥረት ቢያደርጉ ኖር ከኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይ፤ ከኢትዮጵያ መከካለያ ብዙ ሊማሩ ይችሉ ነበር። ቀይ ጥቁር፤ አፋር፤ ኦሮሞ፤ አማራ፤ ሶማሌ፤ አኟክ፤ ወላይታ፤ ክርስቲያን፤ ሙስሊም ወዘተ በሚል መለያ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነታቸው እየተደጋገፉና እየተናበቡ የፈጸሙት ጀብዱ በታሪክ ሲጠቀስ ይኖራል። በወል የሰበሰበቻቸው ኢትዮጵያ የምትባል መተኪያ የሌላት አገራቸው ናት። የሚከተሉት የኢትዮጵያን ብሄራዊ አጀንዳ ነው። የዐብይ አጀንዳ አይደለም፤ የዐማራ ወይንም የኦሮሞ አጀንዳ አይደለም። ኢላማው በትግራይ ሕዝብ ላይ ያተኮረ አይደለም።
የህወሓት አመራር ከፈጸማቸው በታሪክ ከሚጠቀሱት ወንጀሎች መካከል ከፍተኛውን ደረጃ ይዞ ያገኘሁት የማይካድራው እልቂት ነው። ከአንድ ሽህ አምስት መቶ በላይ ንጹህ ወገኖቻችን በዐማራነታቸው ብቻ ተፈርዶባቸው ተጨፍጭፈዋል። ይህንን የሚዘገንን አረመኔነት የፈጸሙትን ግለሰቦች ማን ጨፍጭፉ ብሏቸው ነው? ወንጀሉን የፈጸሙት ብየ ራሴን ስጠይቅ፤ ከዚያ በኋላ የሆነው ክስተት ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጨዋነት አስተማረኝ። ፈረንጆች ይህን ጨዋነት ሲያነሱ አላያቸውም። የኢትዮጵያዊነት ጨዋነትና ሰብእነት ለመላው ዓለም ትምህራዊ ነው።
ለማጠቃለል፤ የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል ለአገራቸው የገቡትን ቃል ኪዳን በሚያኮራ ደረጃ በማከሄድ ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪ ደግሞ የሚታይ የተራው ዜጋ ጨዋነት አስደናቂ መሆኑ ነው። በዚህ ጦርነት የኢትዮጵያዊያንን ደግነት፤ ጨዋነትና ሰብእነት (Humanity) የማያመሰግንና የማያደንቅ ግለሰብና ስብስብ ካለ ራሱን ቢፈትሽ ሊለወጥ ይችላል።
የህክምና ባለሞያዎችና ሌሎች አገር ወዳዶች በአካባቢው የቆሰሉትን ግለሰቦች በዘውግና በሌላ መለያ አድልዎ ሳያደርጉ የቆሰሉትን የትግራይ ብሄር አባላትን ጨምረው ወደ ጎንደር ሃኪም ቤቶች ወስደዋቸዋል። እነዚህ የቆሰሉ ግለሰቦች ባለው አቅም መሰረት እንክብካቤ ተደርጎላቸዋል።
አንድም የቂም በቀል እርምጃ አለመወሰዱ ይደነቃል። ጭካኔን በጭካኔ ሳይሆን ርህራሄ በተሞላበት መንፈስ የሚደረገው አገልግሎት ለተከታታይ ትውልድ ትምህርት የሚሰጥ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
እትዮጵያዊያን የሚሰሩትን ሁሉ ስገመግመው የውጭ ተችዎችና የህወሓት ደጋፊዎች እንደሚሉት የፈጠራና የብሄር ልዩነትን የሚያጋንን ትርክት አይደለም። ሕዝቡ የሚያደርገው የተቀደሰ ድርጊት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተችዎቹ የሚሉት ተጻራሪውን ነው። የምእራብ አገር ተቋማት፤ መገናኛ ብዙሃንና አንዳንድ መንግሥታት ከትችቱ ወጣ ብለው የኢትዮጵያ ሕዝብን ጨዋነት፤ የመላከያውን ኃይል ብልሃተኛነትን፤ የኢትዮጵያን የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት አዋቂነት ቢገመግሙት ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርግ አቋም ሊይዙ ይችሉ ነበር።
ይህን የመለያ እሴታችን ሳንሰለች በተደጋጋሚ ማስተማር ያለብን ደግሞ እኛም ጭምር ነን።
የትግራይ ኢትዮጵያዊያንና ሌሎቹ ተችዎች ትኩረት ማድረግ ያለባቸው ኢትዮጵያ ሰላም፤ እርጋታና የሕግ የበላይነት እንዲኖራት በመረባረቡ ላይ እንዲሆን እጠይቃቸዋለሁ።
የኢትዮጵያ መንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደግሞ ከዚህ እልቂት ይማራሉ የሚል እምነት አለኝ። ትኩረት ሊደረግባቸው ከምመኛቸው መካከል ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአሁን በኋላ ከፋፋይ፤ ለጠብ ጫሪዎች፤ ለጽንፈኞችና ለጅሃዲስቶች ወንፊቶች የሚከፍተውን፤ በተለይ አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝን ከሕገ መንግሥቱ መሰረዝና የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታዎች በዘውግና በኃይማኖት መመስረት ሕገ ወጥ መሆኑን መወሰን ይኖርባቸዋል። በዜግነት መብት ላይ ብቻ የተመረኮዘ መተኪያ ወሳኝ ቢሆን ይመረጣል።
በመጨረሻ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ህወሓትን፤ ኦነግ ሽኔንና የእስልምና ጽንፈኛ ድርጅቶችን ሽብርተኞች ናቸው ብሎ የመሰየም ግዴታ ያለበት መሆኑን በድጋሜ አሳስባለሁ።
ይህን ስያሜ የኢትዮጵያ መንግሥት ካላደረገ የውጭ መንግሥታትና ተቋማት ለእነዚህ አጥፊ ድርጅቶች የሚሰጡትን እውቅናና ድጋፍ እንዲስቡ ለማድረግ አይቻልም። በዲያስፖራው ተሰግስገው የሚደግፏቸውን ግለሰቦችና ስብስቦች ለመከሰስ የሚቻልበትም መንገድ አስቸጋሪና አድካሚ ይሆናል።
ኢትዮጵያ በቆራጥ ልጆቿ ተከብራ ትኖራላች!!
December 12, 2020