“ከህወሓት አዲስ ነገር መጠበቅም ህልም ነው!” ዶ/ር አብርሃም በላይ

“እነዚህ ሰዎች ወይም ቡድኖች እዚህም እዚያም ያጠፉት ጥፋት ሰፊ ነው፤ እናም ሰላም ከሆነና ለውጥ ከመጣ ተጠያቂ ነን ብለው ያምናሉ፤ እነዚህ ሰዎች በሰላም ጊዜ እነሱ በማይመሩበት ምህዳር ላይ ዕድሜ አይኖራቸውም፤ ጥፋታቸው በጣም ከባድ ስለሆነ ይሄን ያውቁታል” – ዶክተር አብርሃም በላይ

ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር

• ዋናው ፍላጎታቸው የራሳቸውን ዕድሜ ማርዘም ብቻ ሳይሆን፤ አገርም በትነው ይሁን ሰላም አሳጥተው የትግራይን ህዝብና ወጣቱን ወደማይሆን ነገር እየገፋፉ፤ የውሸት ትርክቶችን እየተረኩ ከመሃል መጣብህ፣ ከፌዴራል መጣብህ፣ ከአማራ ክልል አማራ መጣብህ፣ ኤርትራ መጣብህ፣ ወዘተ የሚል የውጭ እይታ ቅኝት ውስጡን እንዲያይ የጭንቀትና የሴራ እንቅስቃሴያቸውን ለህዝባችን እየተረኩ ነው።

• ጠቅላላ ወጣቱን ተነስ መሳሪያ ታጠቅ እያሉ የሚቀሰቅሱበት እና ለእነሱ ትንሽ ቀሪ ዕድሜ ወጣቱን ጨርሰው ለመጥፋት እያደረጉት ካለው እንቅስቃሴ በላይ ክህደት የለም። ከዚህ በላይ አገር አጥፊነትም የለም።

• የትግራይን ህልውና ወደፊት የሚወስደው ይሄ ወጣት ነው እንጂ እነሱ አይደሉም። እነሱ በዕድሜያቸውን ጨርሰዋል። አዲስ ነገር ሊያስቡ አይችሉም። ከእነርሱ አዲስ ነገር መጠበቅም ህልም ነው።

• ይህን ወጣት ኃይል ለልማትና ለሰላም እንዳይውል፤ ዕድሜያቸውን ለጨረሱ አካላት ህይወት እንዲከፍል በየቀኑ እየቀሰቀሱት ነው።

• እነዚህ ከዚህ ተሰብስበው የሄዱ ቡድኖች ዕድሜያቸውን ለማርዘም የፈጠሯቸው ትርክቶች ናቸው እያስቸገሩ ያሉት እንጂ፤ የትግራይ ህዝብ መስዋዕትነት የከፈለው ለሰላም ነው። የትግራይ ህዝብ መስዋዕትነት የከፈለው ለፍትህ፣ እኩል ተጠቃሚነትና ፍትሐዊነትን በዝች አገር ለማረጋገጥ ነው።

• የትግራይ ህዝብ መስዋዕትነት የከፈለው አገር እንዲበተንም አይደለም። ስለዚህ የእነዚህ ቡድኖች ሥራ ከትግራይ ህዝብ መሰረት የወጣ/ያፈነገጠ ብቻ ሳይሆን፤ በጥቅሉ የትግራይ ህዝብን የሚገልጽ አይደለም።

• የዚህ ቡድን እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎትና እንቅስቃሴም፤ በተለይ ደግሞ የትግራይን ህዝብ የማይመጥንና የማይገልጽ እንቅስቃሴ ነው።

• ቀድሞ ለትግራይ ህዝብ ምንም ሳያደርጉለት እዚህ የራሳቸውን ኔትዎርክ ሲያስተካክሉ፣ ሀብት ሲዘርፉ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጽሙ የነበሩ ቡድኖች እንዳለ ተሰብስበው ከነሐጢያታቸው ነው ወደ ህዝባችን ተለጥፈው ያሉት።

• ከዚህ ሲሄዱ “በቃ ከዚህ በኋላ ትግራይን ለማልማት ነው የተመለስነው” በሚል የማዘናጊያ ቋንቋ ነው ወደ ህዝባችን የገቡት። ህዝባችን ደግሞ የዋህ ነው ልጆቹን መጣል አይፈልግም።

• ተመልሰው ሲመጡ ትግራይን ያለማሉ በሚል ቋንቋ ስለሆነ የገቡበት ህዝቡም ትግራይን ያለማሉ ብሎ አምኖ ነው የተቀበላቸው። እነርሱ ግን እዚህ ሲፈጽሙት የነበረን ሴራ በሙሉ ትግራይ ውስጥ ለመድገም ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት።

• እንደውም ከሴራዎቹ ከሚታወቁት የኢኮኖሚ ሴራዎችን እና የሰብዓዊ ጥሰቶች አልፈው፤ ትግራይ ውስጥ ሌላ አገርን የማበጣበጥና አገርን የመበተን ፍላጎቶች ነው ያላቸው።

• እነሱ ያጠፉትን ጥፋት የሚሸፍን እስከሆነ ድረስ፤ ወይም ደግሞ ሸፍኖ የሚያቆይና ዕድሜ የሚሰጥ እስከሆነ ድረስ እነዚህ ሰዎች የማያደርጉት ነገር የለም።

• አብዛኛው ብቻ ሳይሆን ትግራይ ውስጥ የነበረው አጠቃላይ የህወሓት አባልና እዚያ አካባቢ ያለው ማህበረሰብ ብታየው የእነዚህ መንፈስ የለውም። እስከ ቀበሌና ጎጥ ወርደህ ብታየው እዚያ ያለው ማህበረሰብ በዚህ የሚገለጽ አይደለም።

• ህዝቡ ሰላም ይፈልጋል፤ እነርሱ ግን ሰላም እያሳጡት ነው። ህዝቡ ፍትህ ይፈልጋል፤ እነርሱ ፍትህ እያሳጡት ነው። ህዝቡ አንድነትና መከባበርን ይፈልጋል፤ እነርሱ ግን ይሄን ለማሳጣት ነው እየሠሩ ያሉት።

• የትግራይ ህዝብ ለብቻው ለመጠቀም ጠይቆ አያውቅም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ እኩል ተጠቃሚነቱ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ ነው ሃሳቡም፤ ፍላጎቱም። መተሳሰብ እንዲኖር ነው። በጋራ ለመኖርና ለኢትዮጵያዊነት መስዋዕት የሚከፍል እንደ ትግራይ ህዝብ የት እንዳለ ሊገባኝ አይችልም።

• እንደ ህወሓትም ሁሉንም አባለት በአንድ ዓይን ማየት በጣም ትክክል አይደለም። ህወሓት ውስጥ ሆነው የትግራይን ህዝብ ፍላጎት፣ ለትግራይን ህዝብ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ በትግራይ ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲኖር፤ በትግራይ የሚፈለገው ልማት እንዲመጣ፤ ትግራይ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን፤ በስፋት ሲነቀሳቀስ የሚውል በሌብነት የሌለ፣ በኔትወርክ ጥቅም ያልተሳሰረ፣ ለህዝብ ብሎ የሚኖር ብዙ አባል አለ።

• በዚህ ሰዓት የትግራይን ህዝብ ለጦርነት መቀስቀስና ወጣቱን ወደ ጦርነት ለማስገባት ማሰቡ በራሱ እብደት ነው፤ ከዚህ በላይም በሽተኝነት የለም። ከዚህ በላይ ጥፋትም የለም። በዚህ ሰዓት ገበሬው መሬቱ ፆም እንዳያድር መቀስቀስ እያለባቸው፤ ሲቀሰቅሱት የሚውሉት ሌላ ነው።

• ወጣቱ አፈናው አስፈርቶት እነሱ ያሉትን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ቢመስልም፤ ተመልሶ ራሳቸውን እንደሚበላቸው ግን ምንም ጥርጥር የለኝም። መጨረሻቸው የሚወድቁበትና አጠፋፋቸው በጣም አደገኛ ነው የሚሆነው።

• እንደዚህ ዓይነት አካሄዶች እውነታው እየተገለጠ ስለሆነ፤ ከእነሱ ውጪ ሌላ ጠላት እንደሌላው የትግራይ ህዝብ ራሱ እየገለጠ እየሄደ ስላለ እውነታው ሲታወቅ ራሳቸው በራሳቸው የሚጠፉ ይመስለኛል።

• የብልጽግና አስተሳሰብ መሰረቱ ደግሞ፣ ወጣቶችን ለጥፋትና ጦርነት ሳይሆን ለልማትና አገር ግንባታ ማሰለፍ ነው። የብልጽግና አስተሳሰብ እንደ አገርም የመበልጸግ አስተሳሰብ ነው።

• የብልጽግና ፍላጎት የትግራይ ህዝብና ወጣት ክላሽ እንዲሸከም አይደለም። ይሄ የድሮ አካሄድ ቀርቷል፤ ተመልሶ ሊመጣም አይችልም። ህዝብን ክላሽ አስታጥቆ መታገል የሚያስብ ካለ ይህ የማይንቀሳቀስ አንድ ቦታ ተቸክሎ የቆመ አስተሳሰብ ነው።

• የዚህ ሃሳብ ባለቤት ደግሞ 40 እና 50 ዓመት በክላሽ ስናደርግ ነበርና አሁንም እንደዚያ ዓይነት ለውጥ ይመጣል ብሎ የሚያስብ፤ ምንም የሃሳብ ለውጥ ለማድረግ ፍላጎት የሌለው፤ የሃሳብ ለውጥ በአጠገቡ የማያልፍበት ፓርቲ ቢኖር ህወሓት ነው፤ በተለይም የተወሰኑት ቡድኖች አካሄድ ነው።

• የብልጽግና አስተሳሰብ የህዝባችንን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፤ በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲኖር ማድረግ ነው።

• የብልጽግና አስተሳሰብ የትግራይ ተወላጅ ሆኖ በየትኛውም አካባቢ ተሳቅቆ ሳይሆን ኮርቶ እንዲሠራ ማስችል ነው። እነዚያ ቡድኖች በሠሩት ሐጥያት የትግራይ ተወላጅ ማዘንም፤ መሰቃየትም የለበትም።

• በእነሱ ምክንያት ህዝባችንም መሰደብ የለበትም፤ መሰደድም የለበትም። የትኛውም ቦታ ያለ ትግራዋይ እነርሱ በፈጠሩት ችግር ብዙ ችግሮች ሲፈጠሩ ቆይተዋል።

• አሁን እሱን ለማስቆም ነው በትኩረት እየሠራን ያለነው። ማንም የትግራይ ተወላጅ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ሆኖ በነፃነት እንዲሠራ፤ ይሄንን ለማበላሸት የሚሠራ አካል ካለም ዕርማት እንዲደረግ በስፋት እየሠራን ነው ያለነው።

• እናም ለትግራይ ህዝብ የምናመጣለት ኢትዮጵያዊነቱ ተጠብቆ፤ ልማቱና ፍትሐዊ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ፤ እና በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ነፃ ሆኖ እንደ ድሮው እንዲንቀሳቀስና እንዲሠራ የሚያደርግ ነው።

• የተፈጠረው ችግር ደግሞ እነዚያ የጥገኛ ቡድኖች የፈጠሩት እንጂ የትግራይ ህዝብም የትግራይ ተወላጆችም ሆኑ ሌሎች የፈጠሩት አይደለም።

• ጥፋተኛ ደግሞ ዘርም ሆነ ሌላ ቅጥላ የለውም፤ ቤተሰቡን እንኳን አይወክልም፤ የሚወክለው ራሱን እንደመሆኑ ጥፋተኛ ተደርጎ መቀመጥ ያለበት ራሱ ነው። ስለዚህ ጥፋተኞች ጥፋተኛ ናቸው፤ ሌላው ህዝብ ግን በነፃ እንዲሠራ የሚያስችለውን ጉዳይ በስፋት እየሠራን ነው።

ምንጭ ፣ አዲስ ዘመን ሐምሌ 27 ቀን 2012 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply