ከሐምሌ 1 እስከ 10 ከፍተኛ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል በተዳፋት አካባቢዎች ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ አሳሰበ

ዕረቡ ሰኔ 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በሐምሌ ወር የመጀመሪያዎቹ አስር ቀናት ከፍተኛ ጎርፍ ስለሚኖር በተዳፋትና ገደላማ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከሐምሌ 1 እስከ 10 ቀን 2014 የሚኖረውን የአየር ፀባይ ሁኔታ ትንበያ በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በመግለጫውም፤ በሐምሌ ወር የመጀመሪያዎች አስር ቀናት በአገሪቱ መደበኛ እና በአንዳንድ አካባቢዎች ነጎድጓዳማ እና በረዶ የቀላቀለ ዝናብ ይጠበቃል ብሏል።

በትንበያው መሰረት በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረው የዝናብ ሁኔታ ከባድ እና ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል መሆኑን ገልጿል።

በዚህም በምዕራባዊ የአገሪቱ አካባቢዎች አጋማሽ እና መካከለኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከ100 እስከ 200 ሚሊ ሜትር፤ በተወሰኑ ቦታዎች ከ200 ሚሊ ሜትር በላይ ዝናብ እንደሚጠበቅ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በሐምሌ ወር በመጀመሪያዎቹ አስር ቀናት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ እና በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይጠበቃል ብሏል።

በአብዛኛው የአባይ፣ ባሮ-አኮቦ፣ ተከዜ፣ አዋሽ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ ኦሞጊቤ፣ አፋር-ዳናከል፣ የላይኛውና መካከለኛው ዋቢ-ሸበሌ እንዲሁም ገናሌ-ዳዋ ተፋሰሶች ከፍተኛ እርጥበት ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በታችኛው ገናሌ-ዳዋ፣ ስምጥ ሸለቆ እና ኦሞ-ጊቤ ተፋሰሶችም መጠነኛ እርጥበት ይኖራቸዋል ተብሏል።

ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ለጎርፍ አደጋ ሊጋለጡ ስለሚችሉ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኢንስቲቲዩቱ ማሳሰቡን ኢዜአ ዘግቧል።

የዝናቡ ሁኔታ በመኸር አብቃይ እና ዘር መዝራት ባልተጀመረባቸው አካባቢዎች የተሻለ እርጥበት ስለሚኖር አርሶ አደሮች አጋጣሚውን እንዲጠቀሙበት አስገንዝቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply