“ከመመሞታችን በፊት ድረሱልን” ጡረተኞች

ትግራይ ክልል በመቀሌ ከተማ የሚገኙ ጡረተኞች የ18 ወራት ያልተከፈላቸው የጡረታ ደመወዝ እንዲከፈላቸው ዛሬ በሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል።

ሰልፉን ተከትሎ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የትግራይ ክልል አረጋውያን ማህበር ሊቀ መንበር አርአያ ገሰሰ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዛሬው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከ200 በላይ የሚሆኑ አረጋውያን “ባለውለታ ይከበራል እንጂ በረሃብ እና በበሽታ አይቀጣም፣ ፍትሕ ለጡረተኞች” የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

በክልሉ የሚገኙ ጡረተኞች ከሐምሌ 2013 እስከ ጥር 2015 ድረስ የአንድ ዓመት ከሰባት ወር የጡረታ ደሞዝ ያልተከፈላቸው መሆኑን አረጋውያኑ ከዚህ ቀደም ለአዲስ ማለዳ መናገራቸው ይታወቃል።

ዛሬ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ጡረተኛ “ዋናው ጥያቄያችን ለ18 ወራት ያልተከፈለንን የጡረታ ደመወዝ እንዲከፈለን ነው” ብለዋል።

“ጡረተኛው በብዙ ችግር ላይ ነው ያለው፤ ከመመሞቱ በፊት ድረሱለት ነው የምንለው” ሲሉም ጭንቀታቸውን ገልጸዋል።

በየትኛውም ዓለም ላይ የጡረታ ደሞዝ አይከለከልም የሚሉት ሌላ አስተያየት ሰጪ፤ የሚመለከተው አካል በአስቸኳይ መፍትሔ ይስጠን ሲሉ ገልጸዋል።

የጡረተኞቹ ተወካይ የሆኑት ክፍለማሪያም “ጡረተኞች እየሞቱብን ነው፣ በበሽታ እየተጠቁብን እና የቤት ኪራይ አልከፈላቹም በሚል እየተከሰሱ ነው” ይላሉ።

“ጥያቄያችንን በተደጋጋሚ ያቀረብን ቢሆንም ምን መፍትሔ ሳይሰጠን ቆይቷል” ያሉ ሲሆን ዛሬ ባቀረቡት ጥያቄ የሰሜን ሪጅን ማህበራዊ ዋስትና እና የመንግስት ሰራተኞች ኤጀንሲ በሰጠው ምላሽ “በዚህ ሳምንት የአንድ ወር የጡረታ ደሞዝ ይከፈላችኃል። የቀረውን የ17 ወር ክፍያ ከፌደራል እና የክልሉ መንግስት ጋር በመነጋገር ላይ ነን” የሚል ምላሽ እንዳገኙ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

“ኤጀንሲው ገንዘብ አላጣም” የሚሉት ክፍለማሪያም “የግል መሥሪያ ቤት የነበሩ ጡረተኞች የጡረታ ደመወዝ እየተከፈላቸው ነው። እኛ ምን አደረግን ዜጎች አይደለንም ወይ?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

በትግራይ ክልል አረጋውያን ማህበር ስር ያሉ ጡረተኞች ከዚህ ቀደም የ18 ወር የጡረታ ደሞዝ እንዲከፈላቸው አገር ውስጥ ካሉ ጠበቆች ባሻገር በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ጠበቆችን ማናገራቸውና “ፊርማ አሰባስባቹ ላኩ” መባላቸውን አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይዘነጋም።

በመላው ትግራይ 52 ወረዳዎች አባላት እና አመራሮች ያለው እና ከዓመታት በፊት በነበረው መረጃ 75 ሺህ የሚሆኑ አረጋውያንን አቅፎ የያዘው የትግራይ ክልል አረጋውያን ማህበር ውስጥ የሚገኙ ጡረተኞች ጥያቄያቸውን በተደጋጋሚ ሲያነሱ ቆይተዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply