ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ የኢትዮጵያ ቅርሶች ለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመለሱ

ቅርሶቹ ከአንድ መቶ ሀምሳ ሶስት አመት በፊት ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ መሆናቸውን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል ፡፡

በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጦርነት ላይ ይጠቀሙበት የነበረ የጦር ጋሻ ፣ ከቆዳ የተሰራና በእጅ የተጻፈ የብራና መፅሀፍ ቅዱስ እሰከነመያዣው፣ ትልቅ እና አነስተኛ መስቀሎች ፣ ጽዋ የሚወሰድበት ዋንጫ ከነማንኪያዎቹ፣የጳጳስ አክሊል ከቀንድ የተሰሩና በብር የተለበጡ የቀንድ ዋንጫዎችን ከነመስቀሉ በትላንትናው እለት ኤምባሲው ተረክቧል ፡፡

ቬሄራዜድ በመባል የሚታወቀው የዩናትድ ኪንግደም የበጎ አድራጎት ድርጅት ከለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅርሶቹ ዙሪያ ወራትን የወሰዱ ድርድሮችን እና ለሽያጭ ቀርበው የነበሩትን ከገበያ እንዲነሱ በማድረግ ቅርሶቹ ለባለቤታቸው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲመለሱ ውሳኔ ላይ መደረሱን በርክክቡ ወቅት ላይ ተገልጿል።

ለንደን በሚገኘው አቴናም በተባለና የዩናይትድ ኪንግደም ልሂቃን ክለብ በተካሄደ የርክክብ ስነስርአት ላይ በለንደን የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ እንደተናገሩት ቬሄራዜድ በጎ አድራጎት ድርጅት ከኤምባሲው ጋር በመተባበር ላደረገው ሰፊ ጥረት ምስጋና በማቅረብ ፣እነዚህ የሀገር ሀብቶች ከቅርስነት በላይ የኢትዮጵያን የጀግንነትና የሀይማኖት ታሪኮች ለትውልድ ጽኑ የሆኑ ማስታወሻዎች በመሆናቸው ኢትዮጵያዊያን እራሳችንን መልሰን እንድናገኝ የሚረዱን መለያዎቻችን ናቸው ብለዋል ፡፡

The post ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ የኢትዮጵያ ቅርሶች ለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመለሱ appeared first on Fidel Post.

Source: Link to the Post

Leave a Reply