ከመፈናቀልና ከውጊያ መልስ ወደ ከፍተኛ ት/ት ተቋም ያለፉ ተማሪዎች ቁጥር ይፋ ሆነ፤ ከ3 ት/ቤቶች ምንም ያለፈ ተማሪ የለም። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መጋቢት 9 ቀን 2014 ዓ.ም…

ከመፈናቀልና ከውጊያ መልስ ወደ ከፍተኛ ት/ት ተቋም ያለፉ ተማሪዎች ቁጥር ይፋ ሆነ፤ ከ3 ት/ቤቶች ምንም ያለፈ ተማሪ የለም። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መጋቢት 9 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ወደ ከፍተኛ ት/ት የገቡ ተማሪዎች 24 በመቶ ብቻ ማለፋቸውን የብሄረሰብ አስተዳደሩ ት/ት መምሪያ አስታውቋል። በብሄረ-ሰብ አስተዳደሩ ከሚገኙ 16 የመሰናዶ ት/ቤቶች ውስጥ 15 ት/ቤቶች ተማሪዎችን ያስፈተኑ ሲሆን፣ ከተፈተኑ 2923 ተፈታኞች 705ቱ ብቻ የከፍተኛ ት/ት መግቢያ ያመጡ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ 1107 የሚህኑ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ለፈተና ቀርበው 369 ወይም (33) በመቶ ያለፉ ሲሆን በማህበራዊ ሳይንስ የት/ት ዘርፍ ደግሞ 1816 ተማሪዎች ተፈትነው ማለፍያ ነጥብ ያመጡት 336 ናቸው፤ ይሄውም በመቶኛ ሲሰላ 18.5 ናቸው። ከ1636 ለፈተና ከቀረቡ ሴት ተማሪዎች ውስጥ 380 (23.2) በመቶ የሚሆኑት ማለፍ ችለዋል። ወደ ከፍተኛ ት/ት ማለፍያ ምዘና ከተሰጡ 15 ት/ቤቶች 3 ት/ቤቶች ምንም ያለፈ ተማሪ የሌለ ሲሆኑ ከአንድ ት/ቤት አንድ ተማሪ ብቻ ማለፍ ችሏል። የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ት/ት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሰይፉ ሞገስ እንደ ተናገሩት፣ እነዚህ ተማሪዎች የተፈተኑበት ወቅትና ጊዜ፣ ትምህርት የሚማሩበት ስላልነበረና ይልቁንም በወቅቱ የዋግ ተማሪ ጣቶች ክላሽን እጅ እስክርቢቶ ያልጨበጡ በመሆናቸው ውጤቱ ይሄው ሆኗል ብለዋል። መምሪያ ሀላፊው አክለውም፣ ለፈተና የተቀመጡበት ጊዜ፣ አይደለም ስለፈተና ማሰብ በህይወት ተረጋግተው ለመቀመጥ እንኳን ያስቻለ ጊዜ አልነበራቸውም። ስለሆነም የዋግ ተማሪውች ለመማር፣ ለማንብም ሆነ ለፈተና ያሚያበቃቸው ጊዜ ስላልነበራቸው፣ ወቅቱን፣ ችግሩና ሁነቱን የዋጀ ውሳኔ መወሰን ነበረበት ብለዋል። እንደ መምሪያ ሀላፊው ገለጻ፣ በመፈናቀልና በውጊያ ላይ፣ እንዲሁም በዱር በገደል የነበሩ አርበኛ የዋግ ተማሪዎች፣ ለፈተና መቅረባቸው ሳይበቃ ክፍል ገብተው አመቱን ሙሉ እንደተማሩ ተደርገው እንዲመዘኑ መደረጋቸው ለውድቀት ተዳርገዋል ሲሉ ተናግረዋል። ቤተመጽሀፍት ገብተው ሳያነቡ፣ ብዕር ሳይጨብጡ፣ ደብተር ሳያነግቱ፣ ክላሽን አንግተው፣ ቦብ ታጥቀው፣ ጫካ እያደሩና ባሩድ እያሸተቱ የባጁ ተማሪዎች መለክያ፣ ሚዛናዊ ስላልሆነ የሚመለከታቸው አካላት ለነገሩ ትኩረት ሰጥተው የማስተካከል እድሎች ካሉ እንዲታይ ሲሉ መምሪያ ሀላፊው ጠይቀዋል። እንደ ዋግ የታለፈው ጊዜ ለማንም ግልጽ ነው፤ ተማሪዎች ደግሞ በልጅ አእምሯቸው ተቀርጾባቸው የቀረውን የጦርነት መንፈስ፣ የመሻርያ ጊዜና ሁነቶች እንኳን ሳይኖሩ፣ የመፈተን እድሉን ብቻ ለመጠቀም ሲሉ ፈተና መውሰደዋል፤ ይህ ሲሆን፣ ያሳለፉትንና እያሳለፉ ያሉትን አስቸጋሪ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የማለፍያ ነጥብ ታሳቢ ይደረግ ይሆናል የሚል የብዙ ባለ ተስፋዎች እሳቤ ነበር፤ ያ አልሆነም። ይህ ባለመሆኑ ጉዳቱ ግለሰቦች ላይ ብቻ የሚቀር አሊያም የሚያርፍ አልሆነም። እዚህም እዚያም ያለው ችግር ሲደማመር ነገ የምንሰራት ሀገር ጎደሎ ትሆንብን አለች፤ በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰፊ ቁጥር ያለው ተማሪ አለማለፉ በሀገሪቱ ላይ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ታሳቢ ያደረገ ማስተካከያ መስጠት የሚቻልበት አግባብ ላይ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ መምምሪያ ሀላፊው ተናግረዋል። የዋግ ኽምራ ኮሚዩኒኬሽን በማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳጋራው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply