ከሞግዚት አስተዳደር ወደ ሞጋሳ አስተዳደር!!! – ሚሊዮን ዘአማኑኤል

ባንኩ፣ወርቁ፣መሬቱ፣ጦሩ ከኛ፣ በኦነግ ማዘዣ ጣቢያ!!! የብልጽግና ፓርቲ ኮማንድ ፖስት!!!
‹‹አደባባይ ቆሞ አበጀሁ ቢላችሁ፣
ይህን ባለጊዜ ምን ትሉታላችሁ፡፡
ሁለት ጊዜ በላሁ እዚህ ቤት ገብቼ፣
ፊትም በወረራ ዛሬም ተመርቼ፡፡››
ለኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የተከናወኑ ጸረ ህዝብ ሥራዎች መቼ እንደተጀመረ በማስረጃ ሄዳችሁ ለማጣራት ወኔና ህዝባዊ ኃላፊነት ካላችሁ መጀመሪያ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የበላይ አመራሮች ላይ የደረሰ ዘረኛ የተረኛነት ስሜት የተነሳ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የእርቅ ፕሮግራም ላይ ታከለ ኡማ ሳይገኝ መቅረቱ ስርዓቱ አንዱን ልጅ አንዱን የእንጀራ ልጅ አድርጎ የፈረጀ ለመሆኑ ጉዳዩን በማጣራት ተዋናዬቹን በማነጋገር ያለውን ሁኔታ መረዳት ትችላላችሁ፡፡ የ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መግለጫ ከሁለት አመት በኃላ መሆኑና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ዘረኛና ተረኛ አሠራራቸውን ለመረዳት መሻታችሁ ከሩቅ ጊዜ ወዲህ ብትሉ አይሻልም፣ሁለት አመት አለፈ፡- ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከራሳችን መዋቅርም ሆነ ከከተማው ነዋሪዎች የሚያደርሱን ተጨባጭ የመሬት ወረራዎች፤ የኮንዶሚኒየም ቤት እደላዎች እና ከተማዋን በግለሰቦች በጎ ፍቃድ የምትንቀሳቀስ የማስመሰል አካሄድ በጊዜ ካልታረሙ ቀድሞውንም ውስብሰብ የነበሩ የከተማዋን ችግሮች የሚያባብሱ እንዲሁም በዜጎች መካከል የሚፈጥሩት ቅራኔ በቀላሉ የሚፈታ አይሆንም፡፡ ይህንን ከግምት በማስገባት የኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቅዳሜ ሰኔ 13 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ከመሬት ወረራ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለነዋሪዎች ማስተላለፍ ጋር እና ማንኛውም የመንግሥት አድሎ አሠራሮችን መረጃ የሚያሰባስብ እና የሚመረምር ልዩ ኮሚቴ አቋቁሟል። ለዚህ ኮሚቴ መረጃ መስጠት የምትፈልጉ ዜጎች በስልክ ቁጥር +251944107659 በመደወል፥ በዋትሳፕ፥ በቴሌግራም እንዲሁም ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀው የኢሜይል አድራሻ [email protected] እንድታደርሱን በትህትና እንጠይቃለን። የተቋቋመው ልዩ ኮሚቴ የደረሰበትን ማስረጃዎችም በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል።››1 ይላል፡፡ እንግዲህ አጣሩት፣ ጉዳዩ እንዲህ ነው፡፡

‹‹የአዲስ አበባ አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የበላይ አመራሮች የእርቅ ፕሮግራም››2 ላይ ታከለ ኡማ ሳይገኝ የመቅረቱ ዋና ሚስጢር በአራቱ አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት ፍቃደኛ ባለመሆን ኦዴፓ የበላይ አመራሮች በአዲስ አበባ ውስጥ
{1} በአዲስ አበባ አስር ክፍለ ከተሞች የንዋሪዎች መታወቂያ ወረቀት በከተማው ንዋሪዎች ላልሆኑ ሰዎች በመሠጠት ላይ እንዳለ በማስረጃ ቢጋለጡም ከንቲባው ጉዳዩን ከማድበስበስ አልፈው ህገወጥ ስራውን ለማስተባበል አልሰነፉም፡፡ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የአዲስ አበባ ከተማ ሥነ-ህዝብን ስብጥር ቁጥርን በአንድ ዘር በመሙላት ቀጣዩን ምርጫ ለማሸነፍ የተደረገ ያልሞት ባይ ታጋዳይ ፍልሚያ አድርገዋል፡፡ የመከላከያ ሚንስትሩ ኦቦ ለማ መገርሳ በአደባባይ ስብሰባ ላይ ዲሞግራፊውን ለመቀየር የሠሩትን ስራ ኢዜማ ማስረጃውን ከህዝብ ወይስ ከሚዲያ ነው የሚጠይቀው፡፡ ‹‹የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም›› ቢሉት ኢዜማ ማን ነገረህ? ይለናላ ሊያጣራው፡፡ የምንወዳቸው የኢሣት ትንታግ ጋዜጠኞች፣ ጉዳዩን ፈልፍሎ ማውጣት እንጂ ስራችሁ ህዝቡማ ዳግም ፈራ፣ ለአንዱ ሲዘንብለት፣ ለአንዱ አላካፋ አለው፡፡ ጎደኞቻችሁ ባልደራሶች የሚዋሹ መስሎችሁ ከሆነ ተሳስታችሆል፡፡ ኢትዬ360 ጋዜጠኞች የህዝብ ድምፅ በመሆናቸው ህዝብ ለእነሱ ማስረጃውን ያቀርባል፡፡ የኢሣትና ኢዜማ ወርቃማ ዘመን የነፃነት ጎህ ሲቀድ ሲታያችሁ ለእኛ የዘረኛነትና ተረኛነት በአናታችን እርግብግቢት እየጠለቀ መምጣቱ አየን፣ መሠንበት ደጉ፡፡

{2} ኮንዶምንየም ቤቶች፤ የኮዬ ፌጫና ገላን የሚገኙ ሠላሣ ሶስት ሽህ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ዜጎች ከባንክ ተበድረው ገንዘብ አጠራቅመውና በባንክ ቆጥበው ኮንዶሚኒም ከሰሩ ዜጎች ተነጥቆ ለኦሮሚያ ዲያስፖራ ተመላሽ፣ ቄሮና ኦዴፓ ካድሬዎች ተሰጥቶል፡፡ ኢዜማ መሪ ፕሮፊሰር ብርሃኑ ነጋ ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ያሸጋግረናል እያለ ሲያሞካሸውና ባልደራስ አንበሳ እስክንድር ነጋን ሲያጣጥለው እንደነበር ልብ ይሎል!!!

{3}ሥራ ቅጥር፤ በአዲስ አበባ አስር ክፍለ ከተሞች የሥራ ቅጥር ሁኔታን ከመጋቢት አስር 2010ዓ/ም ዶክተር አብይ ሥልጣን ከያዘበት ቀን ጀምሮ እስከ መጋቢት አስር 2012 ዓ/ም ድረስ በክፍለ ከተሞች፣ ማዘጋጃ ቤት፣ በጉምሩክ፣ በአየር መንገድ፣ በባንክ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ሠራዊት፣ የሥራ ቅጥር ስም ዝርዝር አይቶ ማጣራት የትንታግ ጋዜጠኞች ሥራ መሆኑን መዘንጋት በህግ ያስጠይቃል፡፡ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዘመን፣ ከዚህ በኃላ ስንት አመት እኖር ይሆን፣ የከተማው ደሃ ንዋሪዎች በወያኔ ኢህአዴግ ዘመንም አልተመቸው፣ በኦዴፓ ብልፅግና ፓርቲ ዘመንም አልተመቸው፡፡ የቢሮክራሲው ዘዋሪዎች የፓርቲው ካድሬዎች የትላንት ኢህአዴግ የዛሬ ብልጽግና መሆናቸውን ዶክተር ብርሃኑ ነጋ፣ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ኢሣት ጋዜጠኞች አጥታችሁት ይሆን!!!

{4} የአዲስ አበባ አስተዳደር ሹመት በአሰራሩ መሠረት ሳይሆን በታከለ ኡማና በኦሮሞ ድርጅቶች ምሲጢራዊ የለሊት ስብሰባና የፖለቲካ ሴራ በህገወጥ መንገድ መከወኑ የሚታወቅ የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ የአዲስ አበባ አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የበላይ አመራሮች የእርቅ ፕሮግራም ላይየአዴፓው በአቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የኦዴፓ አቶ አለሙ ስሜ የተመራ አስታራቂ ቡድን ለመወያየት መድረክ ቢዘጋጅም አቶ ታከለ ኡማ በእርቅ ሥነ-ስርዓቱ ሳይገኝ መቅረቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ኢዜማ በኦዴፓ ብልፅግና እና በአዴፓ ብልፅግና ያለውን የስልጣን ሽሚያ፣ የስልጣን ቅርምት፣ የተረኝነት ስሜት፣ የጥቅም ግጭት፣ ለተገቢው ቦታ ተገቢው ሰው ያለመመረጥ፣ የከተማውን ንዋሪዎች የወደፊት ተስፋና ህይወት ያጨለመ መሆኑን ለመረዳት እንቆቅልሹን መፍታት ያሻል፡፡ የትላንቱን ኢህአዴግ ካድሬ ዛሬ ብልፅግና ስላልከው፣አባ ዱላ አባ ዱላ ነው!!! አካፋን አካፋ፣ ኢዜን ኢዜማ፡፡
{5} የአዲስ አበባ ህዝብ የእራሱ ፖሊስ ሠራዊት የለውም፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ ከተለያዩ ክልሎች የተመለመሉ የፖሊስ ሠራዊት በመዋጮ ይሠፍሩበታል፡፡ ከ1997 ዓ/ም ምርጫ በኃላ የፖሊስ ሠራዊቱ ከህዝብ ጋር አብሮል በማለት ህዝባዊ ፖሊስ ኃይል በወያኔ ኢህአዴግ ዘረኛ ጠርናፊዎች ዛሬም በኦዴፓ ብልጽግና ዘረኛ ተረኛ ፖሊሶች በግፍ ይተዳደራል፡፡
እንደ ኢዜማ መግለጫ ከሆነማ ‹‹በዚህ አጋጣሚ በሕገ ወጥ መንገድ የከተማዋ ነዋሪዎች ጥቅም ላይ የሚፈጸሙ የአድሎ አሠራሮች እና የመሬት ወረራ ላይ በየትኛውም ደረጃ የሚሳተፉ በየትኛውም የሥልጣን እርከን የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ አውቀው የእስካሁን ጥፋታቸውን እንዲያርሙ እና ከአሁን በኋላም ከዚህ ተግባር እንዲታቀቡ አጥብቀን እናሳስባለን። ሕዝቡ በሕገ ወጥ መንገድ የሚፈፀሙ የመሬት ወረራዎችን እና ማንኛውንም የአድሎ አሠራሮች በጥንቃቄ እንዲከታተል እየጠየቅን ከእንደዚህ ዓይነት ሕገ ወጥ ድርጊት ጋር በማንኛውም መልኩ ግንኙነት ያለቸው ንብረቶችን ከመግዛት እንዲሁም በማንኛውም መልኩ ልውውጥ ከመፈጸም እንዲቆጠብ እናስገነዝባለን።›› ይለናል
መሬቱማ
• የአዲስ አበባ ጥናት መቶ ሃያ ሁለት ሽህ ሄክታር መሬት ከአዲስ አበባ ክልል ተወስዶ ወደ ኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ማዘዋወር ታቅዶል፡፡ ከስድስት ክፍለ ከተሞች ሠላሣ ወረዳዎች ወደ ኦሮሚያ ለማዘዋወር ተቅዶል፡፡ በዚህም መሠረት ከየካ ክፍለከተማ ስድስት ወረዳ፣ ቦሌ ሁለት ወረዳ፣ ጉለሌ አምስት ወረዳ፣ ንፋስ ስልክ አንድ ወረዳ፣ አቃቂ ሰባት ወረዳዎች፣ ኮልፌ ቀራኒዬ ዘጠኝ ወረዳዎች ናቸው፡፡ ኢዜማ ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ቢሮቸው ሄዶ መጠየቅ ይጠበቅበታል፡፡
• ኢንጅነር ተሃከለ ኡማ 460 ሽህ ካሬ ሜትር የታጠረ ቦታ ለ150 አርሶ አደሮች ተመልሶል፡፡ በአርሶአደሮች ስም ዲያስፖራዎችና የኦዴፓ ካድሬዎች በዚህ ቅርምት ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር መሬት ሰጪም በጉልበት ነጣቂም መሆኑ ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ ንብረት መንጠቅ የህግ ጥሰትና አድሎዊና ዘረኛ አመለካከት ብዙ ዜጎችን በድሎል፡፡
• ኢንጅነር ተሃከለ ኡማ አስተዳደር 14000 (አስራ አራት ሽህ) ኮንዶምኒየም ቤቶች ለአንድ ብሄረሰብ አባላት ለኦሮሞ የመንግሥት ሠራተኞች አስር ሽህ ብር ለእጣ በማስከፈል በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ፕሮጀክት አራት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አቶ ስንታየሁ ቸኮል አጋልጠዋል፡፡ ኢዜማ!!!
እንደ ኢዜማ መግለጫ ከሆነማ ‹‹የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የለውጥ ባህሪን በመረዳትና የሽግግር ጊዜ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመገንዘብ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የሚከናወኑ ሥራዎችን በአጽንዖት እየተከታተለ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ የከተማው ነዋሪ በመረጠው ተወካይ በሚተዳደደርበት ጊዜ ይፈታሉ ብሎ የሚያስባቸው ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል በማሰብ በከተማ ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች አባሎቹን ማደራጀት እና የድርጅት አቅምን ማዳበርን ዋነኛ ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ እንደቆየም የሚታወቅ ነው፡፡›› ይለናል፡፡ ፕሮፊሰር ብርሃኑ ነጋ በ1997ዓ/ም ከንቲባ መሆኑን የረሳ ይመስላል፣ ግን ብዙ ደም ተከፍሎበታል፡፡ በ2010ዓ/ም ለአንድ ዓመት የተሸጋገረው የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ምርጫ፤-ምርጫው እስኪደረግ ከተማይቱን ስለሚያስተዳድራት ባለሥልጣን ወይም አካልም ሆነ ከተማይቱን ስለሚያስተዳድርበት ደንብ ለከተማይቱ ህዝብ ያስረዳ ወገን የለም፣ አባ ከና ያለም ሰው የለ!!! የህዝብ ተወካዬች ምክር ቤት የአዲስ አበባና ድሬዳዋን ያሸጋገረውን ምርጫ እንደገና ማካሄድ እንዳለበት መቼ ይወስናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በ2010ዓ/ም ይካሄድ የነበረውን የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ምርጫ በነበረው ወቅታዊ የፀጥታ ምክንያት በአንድ አመት መራዘሙን አሁንም ምርጫው መቼ እንደሚካሄድ ማወቅ እንደማይቻል ይገልፃል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማን ህዝበ ውሳኔ በህዝብ ትግል ተገዶ ሲያደርግ የታፈነው የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ህዝብ ባልመረጣቸው የኦነግና ኦዴፓ ብልፅግና ፓርቲ ካድሬዎች ሲታፈን ምርጫ ቦርድ በህዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ትልቅ በደል ፈፅሞል፡፡ ምክንያቱም የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች የተቆቆሙባቸው ቻርተር ምርጫ በየአምስት አመቱ እንደሚካሄድ መደንገጉን ከንቲባ ብርሃኑ ይረሱታል ለማለት አያስደፍርም፡፡ በ1997 ዓ/ም ምርጫ ወቅት ቅንጅት አዲስ አበባን አልረከብም ብሎእራሱን ሲያገል ጊዜያዊ አስተዳደር ተመርጦ ነበር፡፡በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ሹም የነበሩትን ወደ ሌላ ሾሞና በትኖ ለኢንጅነር ታከለ ኡማ በማመቻቸት በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ሠራተኛ ያልሆነ ሰው በመሾም ህገወጥ ዘረኛና ተረኛ አፀያፊ ሥራ ሲሰራ ኢዜማ የሹመቱ አዳማቂና በጊዜው አግባብ አይደለም ያሉትን ተችዎች በማጥላላት ታከለ ኡማ እንደ አብይ ያሸጋግረናል በማለት የቤተመንግስትና የፓርቲ መርህ አልባ ግንኙነት ለመፈፀሙ እራሱን አልገመገመም፡፡ታከለ ኡማ አሁን ያለው ካቢኔ ዛሬም የአንድ አመቱን ጊዜውን ጨርሶ አሁንም በማስተዳደር ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለአዲስ አበባና ድሬዳዋ ህዝብ ላይ ሳይመረጡ በግፍ በሚያስተዳድሩት ዘረኛና ተረኛ አመራሮች ለደረሰ በደል አንድ ቀን በፍርድ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ከምርጫ መሠረታዊ መርሆዎች አንዱ በየጊዜው (Periodic) መሆን ነው፡፡ ምርጫ መራጩ ፍቃዱን በነፃነት የሚገልፅበትና ዋስትና የሚሰጥበት መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር በሃቅ ካጫወቱን፡፡

ለኢዜማ የቤት ሥራ ስለ፡-‹‹መሬት ባንክና ልማት ስራ አፈፃፀም 95 በመቶ እንደተከናወነ ባደረገው ግምገማ አረጋገጠ መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ የሚገኙ 20 የመሬት ይዞታዎች የሚካሄደው የሙከራ የይዞታ መለየት እና መቀየስ ስራ አፈፃፀም 95 በመቶ እንደተከናወነ ባደረገው ግምገማ አረጋገጠ በሃገራችን የተጀመረዉን ለዉጥ ዘላቂ ለማድረግ በአዲስ መልክ ከተቋቋሙ የፌዴራል ስራ አስፈጻሚ ተቋማት መካከል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን (መባልኮ) አንዱ ነዉ። መንግስት ሃገሪቱ ያላትን የመሬት ሃብት መረጃ በአግባቡ በማደራጀት ይዞታዎችን በማልማትና በማስተዳደር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ እንዲያስገኝ ለማስቻል የተለያዩ እርምጃዎችን በመዉሰድ ይገኛል። በዚህም መሰረት ኮርፓሬሽኑ በመላው ሃገሪቱ ያለውን የፌዴራል መሬት ይዞታን ለማልማትና ለማስተዳደር ያመች ዘንድ የመሬት መረጃዎችን ለማሰባሰና የይዞታ ካርታ ስራ ለማከናወን ከጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር ‘የፌዴራል መሬት ይዞታዎች ካርታ ዝግጅት’ በሚል የጋራ መግባቢያ የሰነድ ስምምነት በመጋቢት ሁለት 2012 በመፈራረም ስራው በፕሮጀክት ደረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል፡፡
በዛሬዉ እለት ግንቦት 12 2012 ዓ.ም የፕሮጀክቱን የመጀመሪያ ደረጃ የገመገሙት የተቋማቱ ሃላፊዎች በአዲስ አበባ ንዑስ ፕሮጀክት በሁሉም ክ/ከተሞች ከሚገኙ ወደ ሁለት መቶ ከሚጠጉ የመሬት ይዞታዎች ውስጥ በ 20 የመሬት ይዞታዎች የሚካሄደው የሙከራ የይዞታ መለየት እና መቀየስ ስራ በተያዘዉ እቅድ 19 ለሚሆኑት የድንበር መለየትና የኮኦርድኔት ነጥቦችን መልቀም ፣ በይዞታው ስር ያሉትን የህንጻ አገልግሎት መለየትና መመዝገብ እና የቁራሽ መሬቶችን ጂኦግራፊያዊ (spatial feature) መረሰስ ስራዎች ክንዉን ገምግመዋል፡፡
በዕቅዱ መሰረት የመስክ ሥራው አፈፃፀም 95 በመቶ ሲሆን በተቋማት አለመተባበር፡ የመረጃ እጥረት እንዲሁም በወቅታዊ የCOVID-19 ወረርሺኝ ምክንያት አጠቃላይ አፈፃፀሙ 5 በመቶ ዝቅ እንዲል ማድረጉን በዛሬዉ እለት ገምግመዋል፡፡ እሰካሁን የተሰሩት የፓይለቲንግ ስራዎች በኣንድ ቡድን የተሰሩ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ከ 5 ያላነሱ ተጨማሪ ቡድኖችን በማዋቀር እንዲሁም ለተቋሞች ከፍተኛ ግንዛቤን በማስጨበጥ ስራውን በታቀደለት ጊዜ እንዲያልቅ በአፋጣኝ ወደ ቀጣይ ምእራፍ ለመግባት የስራ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተለዩት ይዞታዎች መካከል የኢትዮጵያ ሲቪል አቪይሽን ባለስልጣን ፡ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ፡ የኢፌድሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ፡ የላይኛዉ አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቲያትር ይዞታዎች ይገኙበታል፡፡››3
ለተጨማሪ መረጃ መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ህዝብ ግንኙነት ቢሮ መረጃ ያጠያይቁ እንላለን፡፡

ምንጭ፡-
{1} የ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ :በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የሚከናወኑ ሥራዎች/ሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ.ም/የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት
{2} የአዲስ አበባ አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የበላይ አመራሮች የእርቅ ፕሮግራም ላይ ታከለ ኡማ ሳይገኝ ቀረ፡፡ (ዲስምበር 7/ 2019እኤአ)
{3} ‹‹መሬት ባንክና ልማት ስራ አፈፃፀም 95 በመቶ እንደተከናወነ ባደረገው ግምገማ አረጋገጠ›› ዘሃበሻ

Leave a Reply