ከሰላም ሥምምነቱ በሗላ በትግራይ በመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ዋጋ ላይ ቅናሽ መታየቱ ተገለጸ

ረቡዕ ጥቅምት 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት የደረሱትን የሰላም ሥምምነት ተከትሎ በትግራይ በምግብ ፍጆታዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ መታየቱ ተገልጿል።

የቢቢሲ ጋዜጠኛ ከመቀለ እንደዘገበው የጤፍ ዋጋን ጨምሮ የእህልና ሌሎች ዋጋ ንረቶች አሁን ድንገተኛ ቅናሽ አሳይተዋል።

የእህል እና የጥርጥሬ ገበያ የዋጋ ቅናሽ አሳይቷል። በተለይ ቅናሹ በመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ላይ በይበልጥ ተስተውሏል ተብሏል።

ቀደም ሲል የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ 14 ሺሕ ብር የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል የተፈረመውን የሰላም ሥምምነት ዜናን ተከትሎ ወደ 8 ሺሕ ብር ዝቅ ብሏል።

ስንዴም በተመሳሳይ ከፍተኛ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፤ በአንድ ጊዜ ከ9 ሺሕ ብር ወደ 3 ሺሕ ወርዷል።

በተመሳሳይ የዘይት፣ የስኳር እና የበርበሬ ዋጋም መጠነኛ ቅናሽ እንደታየበት የመቀለ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የመቀለ ነዋሪዎች ሥምምነቱ እንዳስደሰታቸው እና በበጎ እንደተመለከቱት ተናግረዋል።

ብዙዎች ሥምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ፍላጎታቸው መሆኑንም የተናገሩ ሲሆን፤ መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል።

ዘጋቢው በስፍራው ተዘዋውሬ ታዘብኩት ባለው መሠረት፤ የበርካታ ሰዎች ዋናው መነጋገሪያ ባለፈው ሳምንት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ የተፈረመው የሰላም ሥምምነት ነው።

በትግራይ የሚገኙ ነዋሪዎች ወደ አማራ እና ሌሎች ከተሞች የሚወስዱ መንገዶች ኹሉ እንዲከፈቱና የሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ እንደሚሹም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከሰላም ሥምምነቱ ጋር ብዙ ነዋሪዎችን እያነጋገረ ያለው የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት ጉዳይ ሲሆን፣ በርካታ ሰዎች ሕገ መንግሥቱ መከበር እንዳለበት ቢያምኑም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሙሉ እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ይህም የሆነው ባለፉት ኹለት ዓመታት መከላከያ በርካታ ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸሙ ነው ማለታቸውን ዘገባው አመላክቷል።

የመቀለ ሰማይ አሁን ሰላም በመሆኑና የድሮን ጥቃት ስጋት ገሸሽ በማለቱ ነዋሪዎች መንቀሳቀስ መጀመራቸውን የገለጸው የቢቢሲ ዘገባ፤ ነዋሪዎች ወደ ገበያም ያለ ስጋት እየወጡ መሆኑን ገልጿል።

ለኹለት ዓመታት የቆየው ጦርነት በተለይ በትግራይ ክልል ላይ ከባድ ጠባሳን ያሳረፈ ሲሆን፣ ሸቀጦች እንቅስቃሴ በመስተጓጎሉም መሠረታዊ ፍጆታዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይተው ቆይተዋል።

The post ከሰላም ሥምምነቱ በሗላ በትግራይ በመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ዋጋ ላይ ቅናሽ መታየቱ ተገለጸ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply