ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንዲፈቱ ተጠየቀ።

ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ አሁን ድረስ 154 የሚሆኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በእስር ላይ እንደሚገኙ ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ አስታወቀ።

በኢፌዴሪ መከላከያ ሲያገለግሉ በነበሩ የትግራይ ተወላጆች እስርን አስመልክቶ ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ባወጣው ሪፖርት ነው ይህን ያስታወቀው ።

ድርጅቱ ባወጣዉ ሪፖርት ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ለዓመታት ሲያገለግሉ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች በወቅቱ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በማንነታቸው ተለይተው ወደ ተለያዩ ወታደራዊ ካምፖች መላካቸዉን በሪፖርቱ ገልጿል።

አሁንም ድረስ በአገሪቱ 16 የተለያዩ እስር ቤቶች ያልተፈቱ የሰራዊቱ አባላት እንደሚገኙ ድርጅታችን ለማረጋገጥ ችሏል ሲል በሪፖርተመቱ ተመላክቷል፡፡

ታሳሪዎች ጉዳያቸው በወታደራዊ ፍርድ ቤት የታየ እና እየታየ ያለ መሆኑን የተረዳን ቢሆንም አብዛኞቹ ይግባኝ እንዳይጠይቁ የውሳኔ ግልባጭ ተከልክለው ይገኛሉ ሲል ሁኔታውን አስታውቋል።

በአሁኑ ሰዓት ክስ ቀርቦባቸው በፍርድ ሂደት የሚገኙ እና የተፈረደባቸው የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ቁጥርም በአጠቃላይ 154 መሆኑ ተጠቅሷል።

ከዚሁ መካከል ቁጥራቸው 37 የሚሆኑት ታሳሪዎች ከፍተኛ የፀጥታ ስጋት ባለባቸውና በ 8 ቱ የአማራ ክልል ከተሞች ታስረው የሚገኙ ሲሆን በክልሉ ባጋጠመው ጦርነት ምክንያት ታሳሪዎቹ በከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥ ይገኛሉ ብሏል፡፡

ድርጅቱ በምርመራው እነዚህ የጦር ሰራዊት አባል የነበሩ ግለሰቦች በሃዋሳ፣ቃሊቲ፣እንጅባራ፣ደብረ ታቦር፣ደብረ ማርቆስ፣ሸዋ ሮቢት የመሳሰሉ የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ታስረዉ ይገኛሉ ብሏል።

በመሆኑም ድርጅቱ የፕሪቶሪያዉ የሰላም ስምምነት እንዲከበር፣ሰራዊቶቹ በጦርነት ያልተሳተፉ ከጦርነቱ ቀድመዉ የታሰሩ በመሆናቸው የሚመለከተዉ አካል መፍትሄ እንዲሰጣቸዉ እንዲሁም የሚመለከታቸዉ የሀገር ዉስጥ እና የዉጭ ተቋማት የመከላከያ አባላቱ እንዲፈቱ ጫና እንዲያደርጉ ሲል ለጣቢያችን በላከዉ ሪፖርት ላይ ጠይቋል ።

አቤል ደጀኔ

ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply