ከስልጣን አልወርድም ያለውን ስርዓት በፖለቲካዊም ሆነ በኃይል ማስወገድ ነው ሲል ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ገለጸ

  በትግራይ ክልል ከሰሞኑን የተበራከተውን የተፈናቃዮች ሠላማዊ ሰልፍ በተያያዘ የሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት) ፓርቲ ሊቀ መንበር አሉላ ኃይሉ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት “ዘላቂ መፍትሄው ከስልጣን አልወርድም ያለውን ስርዓት በፖለቲካዊ መንገድም ሆነ በኃይል ማስወገድ መቻል ነው”።

ከሰሞኑን በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቀዬቸው ተፈናቅለው በዓብይ ዓዲ እና ጭላ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ችግራቸው በዘላቂነት እንዲፈታና የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እንዲተገበር በሠለማዊ ሰልፍ መጠየቃቸው ይታወሳል።

በጉዳዩ ላይ ከቀናት በፊት መግለጫ ያወጣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት) ፓርቲ ሊቀ መንበር አሉላ እንደተናገሩት “የፌደራል መንግስት ለፈረመው የፕሪቶሪያው ውል ተገዢ ሊሆን የገባል፤ በህገ መንግሰቱ መሰረት ግዛታዊ አንድነታችን ይከበር፣ ወራሪ ኃይሎች ከቀዬችን ይውጡልን እና ሰብዓዊ እርዳታ በአስቸኳይ ይቅረብልን” ማለታቸውን አስታውሰው በሥልጣን ላይ ያሉ አካላት ተጠያቂዎች ናቸው ብለዋል።

“መብቶችን አስከብራለሁ ችግሮችን እፈታለው ሀላፊነቶችን እወጣለሁ ብሎ ስልጣን የያዘ አካል አለ፤ ከውጤቱ አንጻር ግን በረሀብ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሰዎች አሉ” የሚሉት የሳወት ሊቀ መንበር፤ የፌደራሉ መንግስት የውጭ እርዳታ ሲቆም ዜጎቹን ለማስተዳደር በቂ ድጋፍ የማቅረብ ግዴታ ያለበት ቢሆንም ያንን አላደረገም፤ በተጨማሪም እርዳታው በስርቆት ምክንያት አልደረሰም ሲባል የሰረቀውንም ሆነ ያሰረቀውን የመከታተል ሀላፊነቱን ባለመወጣቱ ደግሞ የክልሉ መንግሰት ተጠያቂ ነው።

“እነዚህን ማህበረሰቦችን ወደ ቦታቸው ከመመለስ አኳያ ከፕሪቶሪያው ስምምነትም ከህገ መንግስት መብታቸውም አንጻር ሲታይ ዜጎቼ ናቸው ብሎ ሀላፊነት የወሰደ አካል በሙሉ በክልልም ሆነ በፌደራል ደረጃ ያለ አካል ተጠያቂ መሆን አለበት” ሲሉም በአጽንዖት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። 

በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮች በሠላማዊ ሰልፍ ያነሱት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈጸም ጥያቄ ከተፈረመ 1 ዓመት ከ3 ወራትን ያስቆጠረ ቢሆንም አልተተገበረም ሲሆን የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀ መንበር በተፈናቃዮቹ ጥያቄ ይስማማሉ። 

ሰልፍ የወጡት ሰዎች ኢትዮጵያዊ ናቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ህግ አለ መብታቸውን የሚደነግግ ህገ መንግስትም መኖሩን የሚጠቅሱት ኃላፊው፤ መብታቸውን የሚያስፈጽሙ የመንግስት አካላት ደግሞ የማስፈጸም ግዴታ አለባቸው ብለዋል።

አዲስ ማለዳ በወቅታዊ የክልሉ ሁኔታ ላይ ከሳወት በተጨማሪ የብሔራዊ ዓባይ ባይቶና ትግራይ (ባይቶና) እንዲሁም የዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲ (ዓረና) አመራሮችን ለማናገር ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀ መንበር ግን ጉዳዩ የፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ ስላለ ተብሎ ሳይሆን “እንደሰብዓዊ አስተሳስብ እንጂ ከፖለቲካ አንጻር ብቻ መታየት የለበትም” ሲሉም ገልጸዋል። 

ለትግራይ ክልል ወቅታዊ ፈተናዎች ቀዳሚው ክፍተት የቱ ጋር ነው ስትል አዲስ ማለዳ ላነሳችው ጥያቄ አሉላ ኃይሉ አስተዳደሮቹ እርስ በእርስ የሚካሰሱ በመሆኑ ለይቶ አንዱን መጠቆም ከባድ ነው ብለው “ቢሆንም ግን አንድ ክልል ላይም ሆነ አካባቢ ላይ ባለው ሁኔታ ተጠያቂ ሊሆን የሚችለው በቅርበት ያለው አካል ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

በተጨማሪም ችግሩ የትም ቢፈጠር “እንደ ሀላፊነት ሁሉንም ዜጎች ማስተዳደር እና ችግራቸውን መፍታት ደግሞ የፌደራል መንግስቱ ሀላፊነት ነው፤ ነገሩን ከፖለቲካ አንጻር ብቻ ሳይሆን እንደ ሰብዓዊ ግዴታ መታሰብ አለበት” በማለት አሳስበዋል።

በሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀ መንበር ምልከታ ተኩስ እና ጦርነቱ ቢቆምም የጦርነቱ ዳፋ ግን ተባብሶ ቀጥሏል። በትግራይ ክልል ያለውን ድርቅ በተመለከተ “ከአሁን በፊት ድርቅ አጋጥሞ አያቅም ለማለት ሳይሆን የመቋቋም አቅም ግን ነበር፤ አሁን ግን የመቋቋም አቅም የለም፣ የእርሻ ማሽኖች ተቃጥለዋል፣ እንስሳቶች ቆስለዋል ብዙ ችግር ደርሷል፤ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ምንም በሚባል ደረጃ ነው፤ ወጣቱ የስራ አጥ ሆኗል፤ የጸጥታ ችግሩም በተወሰነ መልኩ እንዳለ ነው። እነዚህን ችግሮች ሊያስተካክል የሚችል አመራር የለም፤ እንደውም የሚባባስበት ሁኔታ ነው ያለው፤ ከዚህ በመነሳት ክልሉ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ መገመት አይከብድም” ሲሉ አሉላ ኃይሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሊቀ መንበሩ ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ ብለው የሚያስቡት ከጦርነቱ በፊትም ሆነ በኋላ “በትግራይ ህዝብ ጫንቃ ላይ የተቀመጠ እድሜ ልኩን ከስልጣን አልወርድም ያለውን ስርዓት በፖለቲካዊ መንገድም ሆነ በኃይል ማስወገድ መቻል ነው”።

ይህ ስርዓት የትግራይ ህዝብን ጨቁኖ እንዲይዝ እያደረገ ያለው ደግሞ የፌደራሉ መንግስት ነው ሲሉ የሚወቅሱት የሳወት ሊቀ መንበር፤ “ስለዚህ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው ህዝቡ ጫንቃው ላይ የተቀመጠውን አገዛዝ ማሶገድ ሲችል ነው”ብለዋል። በተጨማሪም የፖለቲካው ችግት ከተፈታ የኢኮኖሚውም ሆነ ሌሎች ችግሮች መፍትሄ እንደሚያገኙ ገልጸዋል።

በዚህ ሳምንት በመቀለ ከተማ ተፈናቃዮች ያደረጉትን ሠላማዊ ሰልፍ ተከትሎ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ “እዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የወደቃችሁት ሥራችንን መሥራት ስላልቻልን ነው” በማለት አስተዳደራቸው የበኩሉን ኃላፊነት እንደሚወስድ ገልጸው ነበር። አክለውም ተፈናቃዮቹ በቅርቡ ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንደሚመለሱ ቃል መግባታቸው አይዘነጋም። 

Source: Link to the Post

Leave a Reply