ከስምምነቱ በኋላም “ጥሰቶች ቀጥለዋል” – የተመድ ኮሚሽን

https://gdb.voanews.com/01000000-0a00-0242-bd1b-08dbb877cd62_cx0_cy8_cw0_w800_h450.jpg

የሰላም ሥምምነት ከተፈረመ ከአንድ ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የጦርና በሰብዕና ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ቀጥለዋል ሲል የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ባለሙያዎች ቡድን ዛሬ፣ ሰኞ አስታውቋል።

ለሁለት ዓመታት በተካሄደውና ባለፈው ኅዳር በቆመው ጦርነት በሺሆች የሚቆጠሩ መገደላቸውን፣ በሁለቱም በኩል ያሉ ወገኖች መደዳ ግድያ፣ መድፈር እና በዘፈቀደ ማሰርን ጨምሮ ጭካኔ የተሞላባቸው ወንጀሎችን በመፈፀም ሲወነጃጀሉ መቆየታቸውንና ለተፈፀሙት የመብቶች ጥሰቶች ማናቸውም ኃላፊነት አለመውሰዳቸውን ሮይተርስ በዘገባው አስታውሷል።

ይህንኑ ጉዳይ እንዲመረምር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያቋቋመው ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ባለሙያዎች ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐመድ ቻንዴ ኦትማን ከሪፖርቱ ጋር ያወጡትን መግለጫ ሮይተርስ ሲጠቅስ “ስምምነቱ በአብዛኛው ተኩስ እንዲቆም ቢያደግም በሃገሪቱ ሰሜን፣ በተለይ በትግራይ ለግጭቱ መፍትኄ ማስገኘትና አጠቃላይ ሰላም ማስፈን አልቻሉም” ማለታቸውን ገልጿል።

“በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እጅግ በጣም አሳሳቢ መሆኑን” ሊቀመንበሩ መናገራቸውንና ኮሚሽኑ በሪፖርቱ “ትግራይ ክልል ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በአሳሳቢ ሁኔታ ቀጥሏል” ማለታቸውን፤ “የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት በሲቪሎች ላይ ጥቃት እንደሚፈፅም” ማስፈሩን ሮይተርስ ዘግቧል።

ሪፖርቱ “በጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች ከክልል ልዩ ኃይሎች ትግራይ ክልል ውስጥ መጠነ ሰፊና የተቀናጀ ጥቃት ሲቪሎች ፈፅመዋል” ያለው የኮሚሽኑ ሪፖርት “የእነዚህ ኃይሎች አባላት በግድያ፣ በማሰቃየት፣ በመድፈርና ተመጣጣኝ በሆነ ፆታዊ ጥቃት፣ ወሲባዊ ባርነት፣ ሰውን በባርነት መያዝና በማሰር ወይም በሌሎች የከበዱ ነፃነቶችን የመግፈፍ አድራጎቶች ወንጀሎችን ፈፅመዋል” እንደሚል ዘገባው ይናገራል።

የኢትዮጵያ መንግሥትና የጦር ኃይሎቹ በግልም ሆነ ከኤርትራ ኃይሎች ጋር ሆነው የሚባሉትን ወንጀሎች አለመፈፀማቸውን እየተናገሩ ክሦቹን በተደጋጋሚ ማስተባበላቸውን፣ መንግሥቱ በቀረቡት የተናጠል አቤቱታዎች ላይ ምርመራዎችን እንደሚያካሂድ ቃል መግባቱን፣ የአማራ ክልል ባለሥልጣናትም ኃይሎቻቸው ትግራይ ውስጥ የጭካኔ አድራጎቶችን አለመፈፀማቸውን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply