ከስምንት ቀናት በኋላ የሚያልቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግስት እንዲያነሳ ጥሪ ቀረበ

ማክሰኞ ግንቦት 20 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በኢትዮጵያ እንደ አዲስ እየተባባሱ የመጡት የሲቪክ ምህዳሩን የሚያጣብቡ ድርጊቶች እንዳሳሰቡት አስታውቋል።

ይኼውም የጸጥታ እና ደህንነት አካላት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ምርመራ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን እያዋከቡ ከመሆኑንም ባሻገር በቲያትር እና ጥበብ መልኩ የሚቀርቡ ሥራዎችን በማገድ እንዲሁም የቲያትር ባለምያዎቹን ለእስር የመዳረግ እርምጃዎች በተደጋጋሚ እየተስተዋሉ እንደሚገኙ ካርድ ገልጿል።

በዚህም “ካርድ እነዚህ አደገኛ እና ሕገ መንግስታዊ መብቶችን የሚጋፋ ድርጊቶች ተቀባይነት የላቸውም” ብሎ እንደሚያምንም አመላክቷል።

ስለሆነም መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሳ፣ ሐቀኛ የተጠያቂነት ስርዓት እንዲዘረጋ እንዲሁም የሲቪክ ምህዳሩን እንዲያከብርና እንዲጠብቅ ጥሪውን አቅርቧል።

እንዲሁም ካርድ “የሲቪክ ምኅዳሩን የሚያጣብቡ እርምጃዎች ዒላማ ከሆኑ ወገኖች ጋር በአጋርነት የሚቆም መሆኑን ገልጿል። በአማራ ክልል የተከሰተውን የትጥቅ ውጊያ ተከትሎ ሐምሌ 28 ቀን 2015 የታወጀው እና በዚህ ዓመት ከጥር 28 ጀምሮ ለአራት ወራት የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከስምንት ቀናት በኋላ የጊዜ ገደቡ ይጠናቀቃል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply