You are currently viewing ከቅዱስ ሲኖዶስ በተላለፈው መልእክት እየፈጸሙ ባሉ ወገኖች ላይ ከህግ አግባብ ውጪ ግድያ፣ እስራት፣ ድብደባ እና ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እየፈጸሙ ያሉ የጸጥታ አካላት በህግ ተጠያቂ…

ከቅዱስ ሲኖዶስ በተላለፈው መልእክት እየፈጸሙ ባሉ ወገኖች ላይ ከህግ አግባብ ውጪ ግድያ፣ እስራት፣ ድብደባ እና ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እየፈጸሙ ያሉ የጸጥታ አካላት በህግ ተጠያቂ…

ከቅዱስ ሲኖዶስ በተላለፈው መልእክት እየፈጸሙ ባሉ ወገኖች ላይ ከህግ አግባብ ውጪ ግድያ፣ እስራት፣ ድብደባ እና ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እየፈጸሙ ያሉ የጸጥታ አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥሪ ቀረበ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ከሀይማኖት ጋር ተያይዞ ባለው ወቅታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ባወጣው መግለጫ የመንግስትን አካሄድ አውግዟል። በእለተ እሁድ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ባልተሰጣቸው አካላት 26 ኤጲስ ቆጶሳት የተሾሙ ሲሆን ይህንንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ህገ-ወጥ ነው ሲል ያወገዘው መሆኑ ይታወሳል። በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በዋናነት በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ያልተሰጣቸው አዲስ የተሾሙ አካላት ወደ አብያተ ክርስቲያናት በመንግስት የጸጥታ አካላት ጭምር ታጅበው በመግባታቸው እና ምዕመኑ ይህንን ባለመቀበሉ ምክንያት በተፈጠሩ ግጭቶች በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈጽመዋል ብሏል ኢሰመጉ በመግለጫው፡፡ የጸጥታ አካላት በፈጸሙት ጥቃት ለደረሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መካከል በኢሰመጉ እንደአብነት ከተጠቀሱትም:_ 1) በሻሸመኔ ከተማ ከመንግስት የጸጥታ አካላት በተተኮሱ ጥይቶች የሰዎች ህይወት ማለፉን፣ የአካል ጉዳት መድረሱ፣ 2) በያቤሎ አካባቢ በቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ላይ ጭምር እስራት፣ ማዋከብ እና ድብደባ መፈጸሙን እና 3) በተለያዩ አካባቢዎች ይህንን አካሄድ በተቃወሙ የእምነቱ ተከታዮች ላይ እና የቤተክርሲቲያኒቱ አገልጋዮች ላይ ድብደባዎች እንደተፈጸሙ፣ 4) ቤት ሰብሮ በመግባት የህግ ስነስርዓትን ያልተከተሉ እስራቶች እንደተከናወኑ እና በርካታ ቁጥር ያለቸው ሰዎችም በብዛት እየታሰሩ መሆኑን ጠቅሷል። ከዚህም በተጨማሪ ከቅዱስ ሲኖዶሱ በተላለፈ መልእክት መሰረት ጥቁር ልብስ የለበሱ ሰዎች በአንዳንድ አካባቢዎች እስራት፤ እንግልት እና መዋከብ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ አመላክቷል። ይህ ድርጊትም በአንዳንድ ተቋማት እና ድርጅቶች ጭምር በተመሳሳይ መልኩ እየተፈጸመ መሆኑን ኢሰመጉ ጠቅሷል። ይህ ጉዳይ ወደየማይሆን አቅጣጫ በመሄድ ተባብሶ ከፍተኛ የሰውና የንብረት ጥፋቶችን ከማስከተሉ በፊት የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና የበኩላቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡ ኢሰመጉ በደረሱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ስራዎችን በመስራት ዝርዝር ዘገባ የሚያዘጋጅ መሆኑን አሳውቋል። ኢሰመጉ በመጨረሻም የሚከተለውን አሳስቧል:_ 1) ሀይማኖት የማህበራዊ መስተጋብር አንዱ ክፍልና መብት በመሆኑ መንግስት የማህበረሰቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት በመረዳት የፌዴራል እና የክልል መንግስታት የዜጎችን ደህንነት እንዲያስከብር፣ 2) የፌደራል መንግስት እንዲሁም የክልል መንግስታት እና በዋናነት ችግሮች እየተፈጠሩበት ያለው የኦሮሚያ ክልል መንግስት:_ ሀ) የጸጥታ አካላት በቤተ ክርስቲያን እውቅና ያልተሰጣቸውን ኤጲስ ቆጶሳት በተለያዩ አብያተክርስቲያናት መመደብ አግባብ አይደለም በማለት የተቃወሙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ላይ የሚፈጽሙትን ከህግ አግባብ ውጪ የሆነ ግድያ፣ አካል ማቁሰል፣ ድብደባ እና እስር አንዲያቆሙ እንዲሁም ለ) ከቅዱስ ሲኖዶስ በተላለፈው መልእከት መሰረት ጥቁር ልብስ የለበሱ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ እስሮች እና ድብደባዎችን እንዲያስቆም፣ ሐ) ከህግ አግባብ ውጪ ግድያ፣ እስራት፣ ድብደባ እና ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የፈጸሙ የጸጥታ አካላትን መንግስት በህግ ተጠያቂ እንዲያደርግና መ) የሚወስደውን እርምጃም ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ እንዲሁም ሠ) ጉዳዩ መፍትሄ እንዲያገኝ እና ወደ ግጭት እንዲቀየር ለማድረግ ነገሮችን ወደ ሌላ አቅጣጫ የሚስቡ አካላት ሁሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሲል ነው ኢሰመጉ ጥሪ ያቀረበው፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply