ከብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫኢትዮጵያ ሀገራችን ወደ ታላቅ ምእራፍ በምትሻገርበት ድልድይ ላይ ትገኛለች፡፡ አንዳንዶች ከድልድዩ ወደኋላ ሊመልሷት ይታገላሉ፡፡ ሌሎቹ ድልድዩን…

ከብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

ኢትዮጵያ ሀገራችን ወደ ታላቅ ምእራፍ በምትሻገርበት ድልድይ ላይ ትገኛለች፡፡ አንዳንዶች ከድልድዩ ወደኋላ ሊመልሷት ይታገላሉ፡፡ ሌሎቹ ድልድዩን ሰብረው ገደል ሊከቷት ይለፋሉ፡፡

ታጋይ ልጆቿ ደግሞ በድልድዩ ላይ ብዙ ሳትቆይ ወደፊት እንድትራመድ ለማድረግ ይታገላሉ፡፡ ብልጽግና ሦስተኛውን መርጧል፡፡

ድልድይ ያለፈውን መንገድ ያህል ጠንካራ አይሆንም፡፡ ገደሉን ለመሻገር ግን የግድ ነው፡፡

ረዥም ጊዜ በድልድዩ ላይ መቆየትም አደጋ አለው፡፡ በቶሎ መሻገርና ወደጸናው መሬት መድረስ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለንበት የሽግግር ጊዜም የሚነግረን ይሄንን ነው፡፡

የሽግግሩ ወቅት ዓላማው በዚያው መቆየት ሳይሆን ወደ በለጸገች ኢትዮጵያ መሸጋገሪያ ነው፡፡ እየገጠሙን ያሉትም የሽግግር ጊዜ ፈተናዎች ናቸው፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከመጋቢት 7- 8 ባደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያ ካለፈው መንገድ የመጣችበትን፣ ወደ ብልጽግና ለመሻገር በድልድዩ ላይ የቆየችበትን፣ በድልድዩ ላይ በቆየችባቸው ወቅቶች የገጠሟትን ፈተናዎች፤ ከድልድዩ ወደኋላ ለመመለስ የሚታገሏትን ኃይሎች፣ ድልድዩን ተሻግራ ወደ ብልጽግና እንዳትሸጋገር ያጋጠሟትን ተግዳሮቶች በዝርዝር መርምሯል፡፡

አሁን እያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎች በዋናነት ከአምስት ነገሮች የመጡ መሆናቸውን የፓርቲያችን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አምኗል፡፡ ለእነዚህም ተገቢ ነው ያለውን የትግል ስልት ቀይሷል፡፡

መላ ኢትዮጵያውያንም እነዚህን ፈተናዎች ለማሸነፍ እንዲቻል ከብልጽግና ጋር አብረው እንዲታገሉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የመጀመሪያው ፈተና ታሪክ ካሸከመን ዕዳዎች የሚመነጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አያሌ አኩሪ ታሪኮችና በታሪክ ውስጥ ያገኘናቸው ዕድሎች አሉን፡፡ በእነዚህ እንኮራለን፤ ለኢትዮጵያ ብልጽግናም እንደ አንጡራ ሀብት እንጠቀምባቸዋለን፡፡

በተቃራኒው ደግሞ በታሪካችን ውስጥ ያልፈታናቸው፣ ተጨማሪ ችግር አድርገን የጨመርናቸውና ያልተግባባንባቸው ዕዳዎችም አሉን፡፡ እነዚህ ዕዳዎቻችን የእኛ ብቻ አይደሉም፡፡ በዓለም ላይ ሀገር የመሠረቱ ሕዝቦች ሁሉ የሚገጥሟቸው ናቸው፡፡

እነዚህ ዕዳዎች የመነታረኪያ፣ የመጋጫና የመከፋፈያ ምክንያቶች ሊሆኑብን አይገባም፡፡ ዕዳዎቹን ወረስናቸው እንጂ አልፈጠርናቸውም፡፡ መጡብን እንጂ አልሄድንባቸውም፡፡

የተሻለው የመጀመሪያ መፍትሔ ለዕድሉም ለዕዳውም ተገቢውን ዕውቅና መስጠት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ዕድሉን ለመጠቀም፣ ዕዳውን ደግሞ ለማራገፍ ጠንክሮ መሥራት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሠለጠነና የሰከነ አካኼድ አዋጪ መሆኑን የዓለም ታሪክ አሳይቶናል፡፡

ያለፉ ዕዳዎቻቸውን በጠብ፣ በግጭትና በመከፋፈል ለመፍታት የሄዱ ሀገሮች ተጨማሪ ዕዳ አመጡ እንጂ መፍትሔ አላገኙም፡፡ ያለፉ ዕዳዎቻቸውን በሠለጠነና በሰከነ መንገድ በምክክርና በውይይት፣ በይቅርታና በዕርቅ ለመፍታት የሞከሩ ሀገሮች ግን ወደተሻለ መግባባትና ወደላቀ አንድነት ለመምጣት ችለዋል፡፡ እኛም የሚያዋጣን ይሄ ነው፡፡ የጀመርነው ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ እናድርግ፡፡

ለስኬቱም ከሁላችን የሚጠበቀውን ድርሻ እንወጣ፡፡ ዕዳዎቻችንን በምክክር፣ በይቅርታና በዕርቅ እናርማቸው፡፡ ያለፉ ነገሮቻችን ትምህርት እንጂ እሥር ቤት እንዳይሆኑን አድርገን እንሻገራቸው፡፡

የፓርቲያችን አባላት፣ ደጋፊዎችና መላው ሕዝባችን ያለፉ ታሪካዊ ዕዳዎቻችንን እንደ ግጭት መሣሪያ ለመጠቀም የሚሹ ኃይሎችን በመታገል፣ ለሀገራዊ ምክክሩ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪ እናደርጋለን፡፡

ሁለተኛው ፈተና ነጻነትን ለማስተዳደር አለመቻል ነው፡፡ ነጻነት በነጻ አይገኝም፡፡ በነጻም አይቀጥልም፡፡ ለማግኘት መሥዋዕትነት ይጠይቃል፡፡ በነጻነት ለመኖር ደግሞ ኃላፊነትን መሸከም ያስፈልጋል፡፡ ከመሥዋዕትነትና ከኃላፊነት ውጭ ነጻነት አይኖርም፡፡ ሕዝባችን ባደረገው መራራ ትግል ካገኛቸው መብቶች አንዱ ነጻነት ነው፡፡ አካባቢን የማስተዳደር፣ የመደራጀት፣ ሐሳብን የመግለጥ፣ መንግሥትን የመቃወም፣ ሚዲያን የማቋቋምና የመጠቀም፣ እምነትን ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት የማምለክ፣ ወዘተ. ነጻነቶችን ሕዝባችን በትግሉ ተጎናጽፏል፡፡

እነዚህ ነጻነቶች ግን በራሳቸው አይቆሙም፡፡ የማድረግ መብት ባለበት ሁሉ ያለማድረግ ኃላፊነት አለ፡፡ ያለ ማድረግ መብት ባለበት ሁሉም የማድረግ ኃላፊነት አለ፡፡ የሞራል፣ የባህል፣ የሕግ ተጠያቂነቶች ነጻነትን በኃላፊነት እንድንጠቀምበት የሚያስገድዱን ናቸው፡፡ ነጻነት የሌለበት የኃላፊነት ሥርዓት ጭቆናን ያስከትላል፡፡ ኃላፊነት የሌለበት የነጻነት ሥርዓትም ሥርዓት አልበኛነትን ያመጣል፡፡

በአካባቢ አስተዳደሮች፣ በሚዲያዎች፣ በእምነት ተቋማት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በአክቲቪስቶች አካባቢ የሚስተዋለው ነጻነትን የማስተዳደር ችግር፣ በቶሎ ሊገራ የሚገባው መሆኑን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ በነጻነት መተዳደር ማለት ሕግ በማክበር፣ ሌሎችን ሳይጎዱ፣ ሀገር ሳያፈርሱና ግጭት ሳይቀሰቅሱ፣ መብትን ለመጠቀም መቻል ነው፡፡ ሕግ እያፈረሱ፣ የሌሎችን መብት እየጣሱ፣ ግጭትና ጥላቻን እየቀሰቀሱ፣ ብሎም ሀገር እያተራመሱ መንቀሳቀስ ግን ወንጀል እንጂ ነጻነት ሊሆን አይችልም፡፡ ወንጀል ደግሞ የሕግ ተጠያቂነትን ማስከተሉ የግድ ነው፡፡

በመሆኑም በሀገራችን ነጻነትን ማስተዳደር ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን ምልክቶች እያሳዩ ነው፡፡

በነጻነት ስም በሚፈጸም ወንጀል የተነሣ በትግላችን ያገኘነውን ነጻነት እያጣነው ነው፡፡ ነጻነት ከኃላፊነት ጋር ሚዛናዊነቱን ጠብቆ እንዲሄድ የመንግሥት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎች፣ የፍትሕ ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባችሁን እንድታደርጉ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ ያቀርባል፡፡

ሦስተኛው ፈተና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እየገነገኑ መምጣታቸው ነው፡፡ ዛሬ ባለችው ኢትዮጵያ ማንም የበላይና የበታች ሆኖ መኖር አይችልም፡፡ አንዳችን ያለ ሌላችን ልንኖር አንችልም፡፡ በመከፋፈልና በመለያየት፣ በግጭትና በጥላቻ ምንም ዓይነት ዕድገትና ብልጽግና አይመዘገብም፡፡ ሰላምና ደኅንነታችንም አይረጋገጥም፡፡

እንደ ውሻ አጥንት ከጠላት በሚወረወርልን አጀንዳ እየተራኮትን፣ ለልማት የምናውለውን ጉልበትና ጊዜ ለሤራ ትንተና እያባከንን፣ አንድ ጋት ወደ ብልጽግና ፈቀቅ ልንል አንችልም፡፡ ሀገር መውደድ ሌላውን ወገን በመውደድ እንጂ በመጥላት አይገለጽም፡፡ ለሌላው ወገን መሥዋዕትነት በመክፈል እንጂ በግጭትና በትንኮሳ አይለካም፡፡

የሕዝብን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ከሚንዱ፣ ጥላቻንና ግጭትን ከሚያባብሱ ንግግሮችና ድርጊቶች በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥትና የፓርቲ ኃላፊዎች ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ የፓርቲና የመንግሥት አመራሮች ችግሮች በውይይት እና በሕግ አግባብ ብቻ እንዲፈቱ ማድረግ አለባቸው፡፡

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩና መሠረት እንዲይዙ መሥራት አለባቸው፡፡ ሰላም እንዲሰፍን፣ ልማት እንዲጠናከር፣ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር፣ መታገል በዋናነት ከአመራር የሚጠበቅ ሚና መሆኑን ለአፍታም ልንዘነጋው አይገባም፡፡

የሃይማኖት አባቶች፣ ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶችና ምሁራን ያለፉ ቁስሎችን ከሚቀሰቅሱ፣ ጥላቻን ከሚያነግሡ፣ ሕዝብ በጥርጣሬ እንዲተያይ ከሚያደርጉ፣ የሀገርን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ ከሚጥሉ ድርጊቶችና ንግግሮች እንዲጠበቁ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ ያቀርባል፡፡ የሚመለከታቸው የፍትሕና የጸጥታ አካላትም ይሄን መሰል ንግግሮችንና ተግባራትን በቸልታ እንዳይመለከቱ ያሳስባል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply