ከቦሌ ትምህርት ቤት እስከ 22 ያለው መንገድ አሽከርካሪዎችን ለከፍተኛ እንግልት እየዳረጋቸው መሆኑን ገለፁ፡፡

በመዲናዋ ከቦሌ ትምህርት ቤት እስከ 22 ያለው መንገድ ለረጅም ዓመታት ጥገና ሳይደረግለት በመቆየቱ እንዳማረራቸው አሽከርካሪዎች ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2015 ዓ.ም 823 ኪሎ ሜትር ልዩ ልዩ የጥገና ስራዎችን ማከናወኑን አስታውቋ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ይህ መንገድ ለሁለት ዓመታት ምንም ዓይነት ጥገና እንዳልተደረገለት አሽከርካሪዎቹ ይናገራሉ፡፡

መንገዱ መጠነኛ ጥገና ሲደረግለት ቢቆይም ከሁለት ዓመት ወዲህ ምንም ዓይነት ጥገና ባለመደረጉ ለማሽከርከር አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ነው የገለጹት።
የመንገዱ መበላሸት ፈጥኖ ለማሽከርከር እንቅፋት ከመሆን ባለፈ በተሽከርካሪ አካል ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡

ከጣብያችን ጋር ቆይታ ያደረጉ አንድ አሽከርካሪ እንደገለፁት “ይህ መንገድ ከአስር ዓመት በላይ በዚህ መንገድ እንደተቸገሩና ማንም ዞር ብሎ አለማየቱ እንደሳዘናቸው” ተናግረዋል፡፡

የአገሪቱ የመንገድ መሠረተ ልማት እያደገ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከግንባታው ባሻገር ግን የመንገዶችን የአገልግሎት ዘመን እንዲረዝም በእንክብካቤና በጥገና ሥራዎች ሊደገፍ እንደሚገባ ይታመናል፡፡

ነገር ግን አገሪቱ ለመንገድ ግንባታ የምታውለውን ወጪ ያህል ለመንገድ ጥገናዎች ብዙ ትኩረት እየተሰጠ ያለመሆኑ ይነገራል፡፡

መንገዱን ለረጅም ዓመታት የተጠቀሙት አሽከርካሪዎች መንገዱ ላለፉት ሁለት ዓመታት አካባቢ ምንም ዓይነት ጥገና ሳይካሄድለት መቆየቱ ለዘረፈ ብዙ ችግሮች እንደዳረጋቸው በመግለፅ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የዚህን መንገድ የቆየ ችግር በመመልከት መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንን ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራዎችን ብናደርግም ስልክ አላነሳ በማለታቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡

በአቤል ደጀኔ

መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply