ከተማዋን በማስተዳደር ኃላፊነቴ ወቅት ባለማወቅ ለበደልኩት ለማንኛውም በደል ይቅርታን በትህትና እጠይቃለሁ። – ታከለ ኡማ
ውድ የከተማችን ነዋሪ ወገኖቼ፦
የኢትዮጵያውያን ሁሉ መዲና የሆነችውን ታላቅ ከተማ የማስተዳደርን ዕድል ላለፉት ሁለት ዓመታት በማግኘት ለማገልገል በመቻሌ ትልቅ ክብር ይሰማኛል።
–
ወደዚህ ኃላፊነት አከራካሪ በሆነ መንገድ ብመጣም፤ በወሬ ሳይሆን በሥራ፣ በብሔር ሳይሆን በኢትዮጲያዊነት የሚያምነው መልካምና ሰው ወዳድ ሕዝብ ጋር በፍቅር አብሮኝ ስለሠራና ስላሠራኝ ምስጋናዬ ሁልጊዜም ከፍ ያለ ነው።
አሁን በሥራ ላይ ያለው በእህቴ በወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሚመራው አስተዳደር የዛሬውን ቀን (ጷግሜ 1, 2012) “የይቅርታ ቀን ” ብሎ በሰየመው መሠረት፣ እኔም እንደከተማው ነዋሪና የቀድሞ አገልጋያችሁ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ ይቅርታ ይሁንልን እላለሁ።
–
ከተማዋን በማስተዳደር ኃላፊነቴ ወቅት እንዲሁም እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ባለማወቅ ለበደልኩት ለማንኛውም በደል ይቅርታን በትህትና እጠይቃለሁ። ይህ ታሪካዊ ጉዞ በብዙ ስኬቶችና ፈተናዎች ታጅበን ብዙ ትምህቶችን የተማርንበት ነበር። በወጣትነት፣ የዚህን ግዙፍ ከተማ ኃላፊነት ለመወጣት ስሞክር ፣ የተለያየን ወገን ፍላጎቶች ሚዛንን ጠብቆ ለማስኬድ የነበረው ጥረት ውስጥ፤ ሰው ነኝና ጥፋት ሳይኖር ስላማይቀር በኔ በኩል ጎሎ ለተገኘው ሁሉ በድጋሚ ይቅርታን በትህትና እጠይቃለሁ።
–
እኔንም ለበደሉኝ፤ ያለበደሌ ለከሰሱኝ፣ ያለ ተግባሬ መጥፎን ስም ሰጥተው ላሳጡኝ፤ ሕዝብን ለማገልገል በምተጋበት ወቅት አላስፈላጊ ጦርነትን በመክፈት ሲያደክሙኝና አላሠራ ሲሉኝ ለነበሩት ሁሉ ከልብ የሆነ ይቅርታን አድርጊያለሁ።
የአዲሱ አመት የምህረት፣ የፍቅርና የአንድነት አመት ይሁንልን። ከስህተታችን የምንታረምበት፣ ካለፈው ተምረን ወደፊታችንን የምናሳምርበት ይሁንልን።
Source: Link to the Post