ከትዕግሥት በኋላ የሚከሠት “ሕግ የማስከበር ሥራ” ያለውን አስከፊ ውጤት “ከቅርቡ ታሪካችን ልንማር ይገባል”- ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት 

በትግራይ ክልል ያለው የልማት ስራ “መንግሥታዊ ኃላፊነት እንጂ ፍርሃት” አይደለም ተብሏል

ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት በወቅታዊ ሀገራዊ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ከተመካከረ በኋላ ባወጣው መግለጫ “በስምምነቱ መሠረት የህሐት ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው” ብሎ “የማንነት እና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ ያለባቸውን አካባቢዎች ጉዳይ እልባት ለመስጠት እንዲቻል የተቀመጠው አቅጣጫ ተግባራዊ መደረግ አለበት” ሲል አስታውቋል።

ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ በረጅም የፖለቲካ ዕድሜዋ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ባለመቻሏ በርካታ “የታሪክ ስብራቶች” ተከስተዋል ብሏል። “የታሪክ ስብራቶቹን” ለመጠገን “ነባሩን ፖለቲካዊ ችግር በሀገራዊ ምክክር መፍታት፤ የቅርብ ዘመናችንን የፖለቲካ ችግር ደግሞ በሽግግር ፍትሕ እና በተሐድሶ ማረም” በሚል አገራዊ ምክክሩን፣ የሽግግር ፍትህ ሂደቱን እና የተሃድሶ ስራዎች ላይ መንግስት የሰራቸውን ስራዎች ገልጿል።

ግጭቶችን በስምምነት የመፍታት ልማድ “አለመኖርን ቀይሯል” የተባለው የፕሪቶሪያ ስምምነት ደም አፋሳሽ ጦርነትን በማስቆም የመልሶ ግንባታ ስራዎች እንዲሰሩ ማድረጉን አዲስ ማለዳ ከብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ መግለጫ ተመልክታለች። 

የደህንነት ምክር ቤቱ “ካለፈው ስሕተታቸው ሳይማሩ ዛሬም ተመሳሳይ ችግር ለመፍጠር የሚከጅሉ” ያላቸውን እና በስም ያልጠቀሳቸው አካላት “ሁላችንም ተባብረን አደብ ማስገዛት ይኖርብናል” በማለት አሳስቧል። በተጨማሪም “ከትዕግሥት በኋላ የሚከሠት ሕግ የማስከበር ሥራ የሚኖረውን አስከፊ ውጤት ከቅርቡ ታሪካችን ልንማር ይገባልና” ሲል አጽንዖት ሰጥቷል። 

በትግራይ ክልል፤ የሰላም ድርሻው ታላቅ በመሆኑ “መንግሥት ከሚጠበቅበትም አልፎ ቁስልን ለመሻር የሚያስችል ሥራ እየሠራ ነው” የተባለ ሲሆን “ይሄ ግን መንግሥታዊ ኃላፊነት እንጂ ፍርሃት ተደርጎ መወሰድ የለበትም” ሲል የደህንነት ምክር ቤቱ አስጠንቅቋል።

“ወጣቶች በተለያዩ ምክንያቶች ተገፋፍተው በጽንፈኞች እና በግጭት ጠማቂዎች ወደ ጦር ዐውድማ የሚማገዱበት አጋጣሚ አለ” ያለው ምክር ቤቱ፤ መንግስት “እንቅስቃሴያቸው ሕገ ወጥ ስለሆነ ብቻ ጉዳዩን በጉልበት ብቻ ይፈታ ማለት እንደሌለበት ይገነዘባል” ብሏል። ለዚህም ማኅበረሰቡን ተቀላቅለው ሰላማዊ ሕይወት ለመኖር ፍላጎት ያላቸውን ታጣቂዎች ሁሉ ለመቀበል መንግሥት ፈቃደኛ መሆኑንም የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ገልጿል።

የምክር ቤቱ መግለጫ የታጠቁ አካላት ያላቸውን በስምም ሆነ በትክክል በቦታ ያልጠቀሰ ሲሆን “ጽንፈኛ የፖለቲካ አመለካከቶች እንዲሁም የተደራጁ የወንጀል እና የዘረፋ ፍላጎቶች በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ናቸው” በማለት መግለጹን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች። መንግስትም እንቅስቃሴያቸውን ለመቆጣጠር እየሰራ መሆኑ ተመላክቷል። 

በአማራ ክልል በተሰራ የጸጥታ እና ደህንነት መዋቅር ማደራጀት ስራ “የክልሉን መንግሥት አፍርሶ በኃይል ሥልጣን ለመያዝ ያሰበው ኃይል ፍላጎቱን ለማሳካት እንዳይችል ተደርጓል፤ በተሠራው የሕግ ማስከበር ሥራ የክልሉን መንግሥት እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመታደግ ተችሏል” ሲል የደህንነት ምክር ቤቱ አስታውቋል።

ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤቱ በመላ አገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀዬቸው መመለሳቸውን እና ለመመለስ እየተደረገ ስለሚገኝ ጥረት ገልጿል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply