ከአላማጣ እስከ ቆቦ እየተከናወነ የሚገኘው የመካከለኛ መስመር የጥገና ሥራ 50 በመቶ መጠናቀቁ ተገለጸ

ዕረቡ ጥቅምት 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ከአላማጣ እስከ ቆቦ እየተከናወነ የሚገኘው የመካከለኛ መስመር የጥገና ሥራ 50 በመቶ መጠናቀቁን ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት የጥገና ሥራው ከአላማጣ እስከ ቆቦ እና ከአላማጣ እስከ ላሊበላ መሆኑንም የወልዲያ ዲስትሪክት ዳይሬክተር ሽመልስ ወ/ሰማያት ተናግረዋል፡፡በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን በከፈተው ጦርነት የተጎዱ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን የመጠገን ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ሽመልስ ገልጸዋል።

በዚህም ከአላማጣ እስከ ቆቦ እየተከናወነ የሚገኘው የመካከለኛ መስመር የጥገና ስራ 50 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የ66 ኪሎ ቮልት የትራንስሚሽን መስመር ጥገና ሥራም መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

የጥገና ሥራው በኹለት ምድብ ተከፍሎ እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት ሽመልስ፤ ከ40 እስከ 50 የሚደርሱ የዲስትሪክቱ ሠራተኞች ተሣትፈዋል። በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ጥገናውን ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡በአካባቢው በሚገኙ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በሰሜን ወሎ አካባቢ 10 የኤሌክትሪክ ኮንክሪት ምሰሶችና ከ46 ትራንስፎርመሮች በላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውና በአካባቢው ለመስኖ ፕሮጀክት የተተከሉ የእንጨት ምሰሶች ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

The post ከአላማጣ እስከ ቆቦ እየተከናወነ የሚገኘው የመካከለኛ መስመር የጥገና ሥራ 50 በመቶ መጠናቀቁ ተገለጸ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply