ከአላማጣ እና ከሌሎች የራያ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች፤ በቆቦ ኢንዱስትሪ መንደር እንዲጠለሉ መደረጋቸው ተገለጸ

በአማራ እና የትግራይ ክልሎች “የወሰን ይገባኛል” ጥያቄዎች ከሚነሱባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው የራያ አካባቢ ባለፉት ቀናት ውጊያ መካሄዱን ተከትሎ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ቆቦ ከተማ መግባታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ወቅት ከቆቦ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ የኢንዱስትሪ መንደር በጊዜያዊነት እንዲጠለሉ መደረጋቸውንም አስታውቀዋል።

በአወዛጋቢዎቹ የራያ አካባቢዎች ውጊያ የተቀሰቀሰው፤ ከአካባቢው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ በማይጨው እና መኾኒ ከተማዎች ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ መሆኑን የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ከሰላማዊ ሰልፎቹ  በኋላ በሪ ተኽላይ እና ገርጃለ በተባሉ አካባቢዎች፤ በትግራይ ኃይሎች እና በአማራ ክልል ታጣቂዎች መካከል “ከባድ የተኩስ ልውውጥ” ሲደረግ እንደነበር እማኞቹ አስረድተዋል። 

ለቀናት ከቆየ የተኩስ ልውውጥ በኋላ የትግራይ ኃይሎች፤ ዛታ፣ ኦፍላ፣ ራያ ጨርጨር የተባሉ ወረዳዎችን እና የኮረም ኮተማን ከሰኞ ጀምሮ በቁጥጥር ስር ማድረጋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። በዚያው ዕለት ቀትር አካባቢ በአላማጣ ከተማ የነበሩ ታጣቂዎች እና ኃላፊዎች ከተማይቱን ለቅቀው መውጣታቸውን የዓይን እማኞች ገልጸዋል።

የአላማጣ ከተማ ከሰኞ አመሻሽ ጀምሮ በመከላከያ ሰራዊት እና በፌደራል ፖሊስ አባላት ቁጥጥር ስር ከገባ በኋላ በከተማይቱ መረጋጋት መታየቱን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የአላማጣ ነዋሪዎች አመልክተዋል። በትላንትናው እና በዛሬው ዕለት መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ቢቀጥልም፤ የህዝብ አገልግሎት ሰጪዎች እና ተቋማት ግን አሁንም ዝግ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።  

የመንግስት ሰራተኞች በጸጥታ ስጋት ምክንያት ወደ ስራ ገበታ ለመመለስ መቸገራቸውን እና የተወሰኑትም ከተማይቱን ለቅቀው መሄዳቸውን ነዋሪዎቹ አክለዋል። በአላማጣ ከተማ የነበሩ የስራ ኃላፊዎች፤ ከትላንት በስቲያ ከሰዓት በአጎራባች ወደምትገኘው ቆቦ ከተማ መግባታቸውን የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ አበራ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።   

ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በኋላ በአማራ ክልል አስተዳደር ስር በቆየችው አላማጣ ከተማ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች፤ በትላንትው ዕለት “በብዛት” ወደ ቆቦ ከተማ መግባታቸውን አቶ ሃይሉ ገልጸዋል። ከአላማጣ ከተማ እና ከሌሎችም የራያ አካባቢዎች ወደ ቆቦ ከተማ የሚገቡ ተፈናቃዮች በዛሬው ዕለት መቀጠላቸውንም አስረድተዋል። የተፈናቃዮቹ ቁጥር በአስር ሺህዎች የሚገመት መሆኑንም አቶ ሃይሉ አክለዋል። 

በሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደ ቆቦ መግባታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጠው የከተማይቱ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት፤ ትክክለኛ አሃዙ የሚታወቀው ግን በቀጣይ ከሚደረገው ቆጠራ በኋላ መሆኑን ገልጿል። የቆቦ ከተማ አስተዳደር ተፈናቃዮቹን በኢንዱስትሪ መንደር ባሉ የፋብሪካ “ሼዶች” ለጊዜው እንዲጠለሉ ማድረጉንም ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የራያ አላማጣ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሞላ ሕሉፍን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ሰለሞን በርሀ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል]

Source: Link to the Post

Leave a Reply