You are currently viewing ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ተወካይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ፤ * የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለአማራ ሕዝብ ብሎም ለሀገራችን አለኝታ…

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ተወካይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ፤ * የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለአማራ ሕዝብ ብሎም ለሀገራችን አለኝታ…

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ተወካይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ፤ * የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለአማራ ሕዝብ ብሎም ለሀገራችን አለኝታ የሆኑ ዘርፈ ብዙ አወንታዊ አስተዋፅኦዎችን ሲያበረክት መቆየቱ ይታወቃል። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ድጋሚ የማይመለሰውን ክቡር የሆነውን ህይወት መስጠትን ጨምሮ የተለያዩ መስዋዕትነቶች ተከፍለዋል። ሆኖም ድርጅቱ በሕዝባችን በጥብቅ በሚፈለግበት ወቅት በተገቢው ቁመና ላይ መገኘት ባለመቻሉና ከውስጥ በተፈጠሩ ልዩ ልዩ ችግሮች ምክንያት በመጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም በተደረገው ጉባዔ አብን ሪፎርም አድርጎ ይታደስና ጠንክሮ ትግሉን ይመራ ዘንድ ቢጠበቅም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ለድርጅቱ አስፈላጊ የሆነው የሪፎርም ጉዳይም በጉባዔው በአጀንዳነት ተይዞ ውይይት ተደርጎ ተገቢ ውሳኔ… እንዲሰጥበት ቢሞከርም በሰብሳቢዎች ከፍተኛ ጫና ግብ ሳይመታ መቅረቱ የሚታወስ ነው። በጠቅላላ ጉባዔው ጥያቄ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ መሰረት እስከ ሰኔ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ጉባዔ በመጥራት የተሳካ ሪፎርም የማድረግ ፍላጎትና ዝግጁነት በድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ፣ የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን እንዲሁም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በኩል እንደሌለ በመገንዘብ የጠቅላላ ጉባዔው ተወካይ ኮሚቴ የተቋረጠውን ጉባዔ የማጠናቀቅ ኃላፊነት ወስዶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱም ይታወቃል። ሆኖም ግን እነዚህ የድርጅቱ አካላትና አመራሮቹ ለስኬቱ ከመስራት ይልቅ እንቅፋት ሆነው በመቆማቸው እንዲሁም የምርጫ ቦርዱ ለተወካይ ኮሚቴው እውቅና የሚሰጥ ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት የምርጫ ቦርዱ ባስቀመጠው ቀነ ገደብ ውስጥ ጉባዔውን ማካሄድ ሳይቻል ቀርቷል፡፡ የድጋሚ ጉባዔውን እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ለማካሄድ በማዕከላዊ ኮሚቴው ሰኔ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ተቋቁመው የነበሩ የጉባዔ አዘጋጅና የሰነድ ዝግጅት ኮሚቴዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተውና ከፍተኛ ፋይናንስ ወጪ በማድረግ ግለሰባዊ ፍላጎቶችና አቋሞች ላይ በተመሰረቱ የተለያዩ ድርጅት አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ተጠምደው ቆይተዋል፡፡ በመጨረሻም አመቻች ኮሚቴው ፋይናንስን እንደምክንያት ጠቅሶ ስልጣኑን ያላግባብ በመጠቀም ጉባዔውን በተቀመጠው ቀነ ገደብ እንዳይካሄድና እንዲራዘም አድርጓል፡፡ በጉባዔው የተያዘው የሪፎርም አጀንዳ በውስጣቸው ያሉ ከፍተኛ አመራሮችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከት በመሆኑ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን እና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይሄንን እንዲሁም በተወካይ ኮሚቴው በተደጋጋሚ አቤቱታ የቀረበባቸውን ሌሎች መሰል የመርህ ጥሰቶችና ችግሮች እንዲታረሙ አድርጎ ጉባዔውን በማሳካት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ አልቻሉም፡፡ በመሆኑም የአብን የጠቅላላ ጉባዔ ተወካይ ኮሚቴ ከዚህ በኋላ ጉባዔውንና ሪፎርሙን በማሳካት ድርጅቱን የመታደግ ብቸኛው ኃላፊነት በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ያረፈ መሆኑን ሁሉም የድርጅታችን፣ የሕዝባችንና የሀገራችን ጉዳይ የሚያሳስባቸው ተቆርቋሪዎች እንዲገነዘቡት ይፈልጋል። ከዚህ በመነሳት የጉባዔውንና የሪፎርሙን ሂደትን በተመለከተ ተወካይ ኮሚቴው የሚከተሉትን መልዕክቶች ማስተላለፍ ተገቢ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ 1ኛ) ለአብን የማዕከላዊ ኮሚቴ፣ የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን እና የብሔራዊ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፡- ባለፉት ጊዜያት በድርጅታችን ውስጥ እንደግለሰብም ሆነ እንደኮሚቴ ያበረከታችሁት መልካም አስተዋጽኦ እንዳለና ታሪክም የሚመዘግበው መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ አስቀድሞ ተገቢ ተግባራትን አከናውኖ መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም ሲካሄድ በነበረው ጠቅላላ ጉባዔ ሪፎርም መደረግ የነበረበት ቢሆንም ሰብሳቢዎች የጉባዔተኛውን ጥያቄ በአግባቡ ባለማስተናገድና ረግጠው በመውጣታቸው ምክንያት ጉባዔው በመቋረጡ ቦርዱ የቀረበለትን አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ ቢሰጥበትም እስካሁን የድጋሚ ጉባዔውንና ሪፎርሙ ያልተካሄደው በእናንተ ኃላፊነትን አለመወጣት፣ የፍላጎት አለመኖር እና ከሕዝብ ይልቅ የግለሰቦችን ፍላጎት ተከትሎ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ድርጅት አፍራሽና የአማራን ሕዝብ አንድነት የሚያናጋ አቋምና እንቅስቃሴ ላይ መገኘት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ከድርጅቱ አልፎ የአማራ ሕዝብን ትግል ተፅዕኖ ውስጥ የሚከት በመሆኑ በድክመት ብቻ የሚታይ ሳይሆን ሁሉንም አበርክቶ በዜሮ አባዝቶ ከታሪክ አልባነት ባለፈ ዘለዓለማዊ ተወቃሽነትን የሚያወርስ ሁኔታን የሚያስከትል ነው፡፡ በመሆኑም ከጠቅላላ ጉባዔው በተፃራሪ ያልቆማችሁትን አመራሮች ተወካይ ኮሚቴው እያመሰገነ ለተሻለ በጎ ተግባር ሳትጠቀሙበት የሚያልፈው ሁኔታና ጊዜ ሁሉ ድርጅታችንና ትግላችን ከጉዳት የሚታደግ አለመሆኑን በጥብቅ ማስገንዘብ ይፈልጋል። በፊርማቸው አረጋግጠው ለቦርዱ አቤቱታ አቅርበው ያስወሰኑትን የጠቅላላ ጉባዔ አባላትና ተወካይ ኮሚቴውን በጠላትነት ከማየት ይልቅ ከጠቅላላ ጉባዔው ጎን በመሰለፍ ጉባዔውና ሪፎርሙ ስኬታማ ሆኖ አውደ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለለትን ድርጅታችንና የአማራን ትግል በመታደግ የእስካሁኑን መዘግየት የሚክስ ተግባር ላይ ተገኝታችሁ በዚህ ወቅትም ሆነ በታሪክ ደምቆ የሚታይ መልካም አበርክቶ ይኖራችሁ ዘንድ በድርጅታችንና ቃል ገብታችሁ በስሙ በምትታገሉለት በአማራ ሕዝብ ስም ጠቅላላ ጉባዔው ጥሪውን ያቀርባል፡፡ 2ኛ) ለአብን የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም አባላት፡- ድርጅታዊ ሪፎርም አድርጎ የተቋረጠውን ጠቅላላ ጉባዔ ለማጠናቀቅ በጉባዔ አባላትና በተወካይ ኮሚቴው የተጀመረው ትግል በሀሳብ አለመግባባት፣ በፋይናንስ ችግር፣ በተስፋ መቁረጥና በተለያዩ ጫናዎች ከጅምሩ ይከስማል ብለው አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮችም ሆኑ ሌሎች አካላት ቢጠብቁም ይህ የሚቻል እንዳልሆነ ታይቷል፡፡ ወደፊትም ጉባዔውና ሪፎርሙ ተሳክቶ ድርጅታችን ወደሚገባው ቁመና እስኪመለስ ድረስ በየደረጃው ያላችሁ አመራሮችና አባላት የአብን ህልውና፣ የአማራ ሕዝብ ትግል ቀጣይ እጣፋንታና የትውልዱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተስፋ በእኛ ላይ እንደወደቀ አምነንና ለግባችን ታምነን በተለመደው ቁርጠኝነትና ፅናት መርህን መሰረት ያደረገው ትግላችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተወካይ ኮሚቴው ያሳስባል። 3ኛ) በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ለምትገኙ የአብን ደጋፊዎችና ለሕዝባችን በሙሉ፡- አብን ከቅድመ ምስረታ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ባለው ሂደት መልካም ቁመና ላይ እንዲገኝ፣ ከችግሩም እንዲወጣና ወደፊትም ጠንካራ ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል ከአባላቱ ባልተናነሰ ደረጃ የደጋፊዎቹ ዘርፈ ብዙ አበርክቶ የገዘፈ እንደሆነ የሚታመን ነው። በድርጅታችንና በሕዝባችን ስም ከፍ ያለ ምስጋና እያቀረብን እስካሁን ለድርጅታችን ያደረጋችሁት ድጋፍ ለአባላት የሞራል ልዕልናን በመስጠት በዚህ በችግር ወቅትም የትግል ፅናትንና አይበገሬነትን ማጎናፀፍ የቻለ እንደሆነ ኮሚቴው መግለፅ ይፈልጋል። ይህን የጠቅላላ ጉባዔና ሪፎርም በተሳካ ሁኔታ አከናውኖ ድርጅቱን ለመታደግም ሆነ ወደፊትም በሚኖረው የሕዝባችን ትግል ሁሉ የተለመደው መልከ ብዙ ተሳትፏችሁና ድጋፋችሁ አሁንም ጠንክሮ እንዲቀጥል ተወካይ ኮሚቴው በአፅንኦት ያሳስባል። 4ኛ) ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፡- የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን እና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያሉ አመራሮችን ጉባዔው እንዲካሄድ ፍላጎት የሌላቸው መሆኑና በተግባርም ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ላይ መገኘታቸውን፣ ጉዳዩ በቦርዱ ውሳኔ ከተሰጠበት የቆየ መሆኑንና ውሳኔው ተፈፃሚ ሊሆን አለመቻሉን፣ ጉባዔው የተቋረጠ ወይም ተጠርቶ ያደረ እንጅ አዲስ አለመሆኑን፣ የድርጅቱ የበላይ የስልጣን አካል በሆነው የጠቅላላ ጉባዔ አባላት የድጋሚ ጉባዔና የሪፎርም ዝግጅቱን ጉዳይ ለተወካይ ኮሚቴው በፊርማቸው አረጋግጠው ኃላፊነት መስጠታቸውንና ለቦርዱ ገቢ መደረጉን እንዲሁም ሐምሌ 27 እና ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ተወካይ ኮሚቴው ለቦርዱ ያቀረባቸውን ማብራሪያዎች መሰረት በማድረግ ጉባዔውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አካሂዶ ድርጅቱን ለመታደግ ተወካይ ኮሚቴው የተሰጠውን ጉባዔውን የማጠናቀቅ ኃላፊነት በአፋጣኝ እውቅና እንዲሰጥ በአክብሮት ያሳስባል፡፡ ምንም እንኳ ቦርዱ ጉዳዩን ሲያስተናግድ የቆየበት ሁኔታ መልካም ቢሆንም ጉዳዩን በመመርመር ትክክለኛ ውሳኔ በተገቢው ጊዜ ውስጥ ካልሰጠና ጉባዔው ከዚህ በላይ ከተራዘመ ግን ሁኔታው የቦርዱን ተዓማኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባና ለወደፊትም የሠላማዊ ትግልና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ ትውልዱ ያለውን ተስፋ የሚሸረሽር መሆኑን ተወካይ ኮሚቴው ማሳሰብ ይፈልጋል። አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፣ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ! የአብን የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ተወካይ ኮሚቴ አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ ነሐሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply