ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠቅላላ ጉባዔ ተወካይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ፤ ሕዳር 7 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ ባህርዳር የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠቅላላ ጉባዔ አባላት ተ…

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠቅላላ ጉባዔ ተወካይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ፤ ሕዳር 7 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ ባህርዳር የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠቅላላ ጉባዔ አባላት ተወካይ ኮሚቴ በኢፌዴሪ መንግስት እና በሕወሃት መካከል የተደረገውና እየተተገበረ ያለው ድርድር የአማራን፣ የአፋርን፣ የትግራይንና የሌሎችን ወንድም ሕዝቦች እንዲሁም በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሠላም በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲሆን የሁሉም ፍላጎትና መብት ግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ እንዲተገበር በአፅንኦት እያሳሰበ ባልተጠናቀቀው 3ኛው ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ዙሪያ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቷል፡፡ **** የአማራ ሕዝብ በዚህ ወቅት ለጦርነትና ለዘር ፍጅት ተዳርጎ የበረታ ጉዳት እያስተናገደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቀጣይም ተጋላጭነቱ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን የአማራ ሕዝብን የህልውና አደጋ ለመቀልበስና የተዛነፈውን የሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር በማስተካከል በኢትዮጵያ እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሕ እንዲሰፍን ለማስቻል ታልሞ የተመሰረተው አብን ዓላማውን ስቶ ከትግል መስመሩ ከወጣ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ የተሟላ የብሔራዊ ስራ አስፈፃሚ እና የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አባላት ካለመኖርም ባሻገር የማዕከላዊ ኮሚቴና የሌሎች የተለያዩ የድርጅቱ አካላት ስብሰባዎችን ማካሔድና ውሳኔ መስጠት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ከተደረሰ ቆይቷል፡፡ ይህም በመሆኑ የድርጅቱን አሰራርና ህግን በተከተለ መልኩ ውሳኔ ያልተሰጠባቸው እንዲሁም የትግሉን ዓላማና ስትራቴጅ የሚፃረሩ መግለጫዎች በተደጋጋሚ በድርጅቱ ስም ለሕዝብ ሲተላለፉ ተስተውሏል፡፡ የበርካታ የዞን ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችን የባንክ አካውንት በማገድ እንዲሁም ቋሚ የጽ/ቤት ሰራተኞችን ደመወዝ በማቋረጥ ቢሮዎች እንዲዘጉ በመደረጉ ትግሉ እንዲንኮላሽ እየተደረገ ነው፡፡ ይህና መሰል ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ አስቀድሞ በማወቅ የአብን ጠቅላላ ጉባዔ አባላት ከመጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ድርጅታዊ አሰራርንና ህግን ተከትለን ለተለያዩ የድርጅቱ አካላት እና ለምርጫ ቦርዱ በጽሑፍና በአካል ያቀረብን መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ተወካይ ኮሚቴው ከተቋቋመበት ቀን ጀምሮ ጉዳዮችን ለሚመለከታቸው የድረርጅቱ አካላትና አመራሮች እንዲሁም ለምርጫ ቦርድ ግለሰባዊ፣ ድርጅታዊና ሀገራዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ በጥንቃቄና በትግስት በማቅረብ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት እጅግ በጣም ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ሆኖም ግን የተወሰኑ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ባለመወጣትም ሆነ ያላግባብ በመጠቀም ተገቢው ድርጅታዊ መፍትሔ እንዳይተገበር አድርገዋል፡፡ የምርጫ ቦርዱ የጠየቃቸው ከኦዲትና ከጠቅላላ ጉባዔ ጋር የተያያዙ ሰነዶች በወቅቱ ቀርበው የተቋረጠው 3ኛው ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔ መጠናቀቅ አልቻለም፡፡ የምርጫ ቦርዱም ጉባዔውን በተመለከተ በቁጥር አ1162/11/586 በሚያዚያ 18/2014 ዓ.ም የወሰነውን እንዲሁም የቀረበለትን የጉባዔ ማራዘሚያ ጥያቄ ውድቅ አድርጎ በቁጥር አ1162/11/640 በግንቦት 26/2014 ዓ.ም በድጋሜ ያፀናውን ውሳኔ እስከ ዛሬ ድረስ ማስፈፀም አለመቻሉ ይታወቃል። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ 1162/2011 የሚቃረን ነው፡፡ በመሆኑም በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉባዔ አድርጎ የተቋረጠው የሪፎርምና ሌሎች አጀንዳዎችን ለማጠናቀቅ አብንን ከተደቀነበት አደጋ ታድጎ የአማራ ሕዝብን እንዲሁም የኢትዮጵያን አሁናዊ ችግር ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ ከድርጅቱ የሚጠበቀውን አይተኬ ሚና እንዲጫወት ለማስቻል በየደረጃው ያላችሁ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ደጋፊዎች የሚጠበቅባችሁን ዝርዝር ኃላፊነት በጋራ መክረን በቅርብ ጊዜ የምናሳውቅ መሆኑን ተረድታችሁ በያላችሁበት በንቃት ትጠባበቁን ዘንድ ጥሪያችንን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡ 1ኛ) ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፦ የሪፎርምና ሌሎች ያልተቋጩ አጀንዳዎች ላይ ውሳኔዎችን በማስወሰንና ተፈፃሚ በማድረግ የተቋረጠውን ጉባዔ ለማጠናቀቅ በጠቅላላ ጉባዔው ኃላፊነት የተሰጠውና ለምርጫ ቦርዱ ጥያቄ ያቀረበ አካል እያለ የተቋረጠው የአብን 3ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ በቦርዱ ውሳኔ መሰረት በድጋሚ ተጠርቶ ሳይጠናቀቅ ስምንት (8) ወራትን አስቆጥሯል፡፡ ከተወካይ ኮሚቴው በተጨማሪ ምላሹ በመዘግየቱ የተነሳ የዞን ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችና አመራሮችም ለቦርዱ ጥያቄውን በደብዳቤ እስከማስገባት ደርሰዋል። ይህ ሁኔታ አሁን ላይ በቦርዱ ገለልተኛነትና ሀቀኝነት ላይ ጥርጣሬና ስጋት እንዲያድርብን እያደረገን ነው። በተጨማሪም ሁኔታው ትክክልና ፍትሐዊ ካለመሆኑም በላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ለሠላማዊ ትግልና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ያለው ሚና አሉታዊ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ በመሆኑም ሁኔታው ድርጅታችንና ሕዝባችን ለባሰ አደጋ እያጋለጠ ስለሆነ የማዕከላዊ ኮሚቴውም ሆነ ሌሎች አካላት ጉዳዩን ማስፈፀም የማይችሉ መሆኑን በመገንዘብ ለጠቅላላ ጉባዔው አባላት ተወካይ ኮሚቴው ኃላፊነቱን በመስጠት ምርጫ ቦርዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቋረጠው ጉባዔ እንዲጠናቀቅ በማስቻል የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲወጣ ስንል ጥብቅ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ 2ኛ) በየደረጃው ለምትገኙ የአብን አመራሮችና አባላት እንዲሁም ደጋፊዎች፦ በየደረጃው የምትገኙ የአብን አመራሮችና አባላት እስከዛሬ ድረስ እያደረጋችሁት ያለው ህግንና መርህን የተከተለ ጠንካራ ውስጣዊ ትግልና በአግባቡ እየተወጣችሁት ያለው ትልቅ አደራ/ኃላፊነት እንዲሁም በደጋፊዎች ዘንድ የታየው ትግስት በታሪክም ሆነ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ሒደት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው። የሪፎርምና ሌሎች አጀንዳዎችን በማስወሰንና በማስፈፀም የተቋረጠውን ጉባዔ ህጋዊ በሆነ መንገድ በስኬት በማጠናቀቅ ድርጅታችን አብንን የመታደግ ኃላፊነታችን በምርጫ ቦርዱ እጅ ላይ በመሆኑ እስካሁን የቦርዱን ውሳኔ መጠበቅ የግድ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ሁኔታው ያልተገባ ረዥም ጊዜ በመውሰዱ የእስካሁኑን ሁኔታዎች መሰረት በማድረግ አዲስ ትግል መጀመር እንዳለበት ተወካይ ኮሚቴው ያምናል፡፡ በመሆኑም ድርጅታችን ለመታደግና የአማራ ሕዝብን ትግል ለማጠናከር የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን በጋራ መክረን በቀጣይ አጭር ጊዜ ውስጥ የምናሳውቅ መሆኑን በመረዳት ዝግጁ ሆናችሁ እንድትጠብቁ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡ አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፣ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ! የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠቅላላ ጉባዔ አባላት ተወካይ ኮሚቴ አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ ህዳር 7 ቀን 2015 ዓ.ም ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24

Source: Link to the Post

Leave a Reply