
ከአማራ ተማሪዎች ማህበር (አተማ) በድሬድዋና ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲዎች በአማራ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ! መጋቢት 02 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ የአማራ ሕዝብ ለዘመናት በጠላቶቹ የተሴሩበት ሴራዎች እና የጥላቻ ትርክቶች ጊዜያትን እየጠበቁ ሲፈነዱና ሕዝቡን እንደ ሕዝብ ከየአቅጣጫው ለሠቆቃ እና ለጥፋት ሲዳርገው ማየት የተለመደ ነው።በዚህም የአማራው ተማሪ እንደ አንድ የአማራ ሕዝብ የማህበረሰብ ክፍል ለዘመናት በጠላቶቹ ተዘርቶ፣ተኮትኩቶና አድጎ እዚህ የከፋ ደረጃ ላይ የደረሰው ፀረ-አማራ ትርክት ገፈት ቀማሽ ከሆነ ዋል አደር ብሏል።ከሰሞኑ በድሬድዋ እና ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ በሚገኙ የአማራ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው ብሔርን ትኩረት ያደረገ ድብደባ ፣እስር እና ማዋከብ የዚህ ፀረ-አማራ ትርክት ማሳያ ነው። በድሬድዋ ዩኒቨርስቲ በቀን 23 /06/15 ዓ.ም የጀመረው የአማራ ተማሪዎችን ላይ በፀጥታ አካላት የተደገፈ ድብደባ ፣ እስር እና ማዋከብ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ ከ 400 በላይ የአማራ ተማሪዎች ተደብድበው እንዲሁም የመታወቂያ ካርዳቸውን እና የመመገቢያ ተቀምተው ከግቢ ውጭ እንዲወጡ ተደርገዋል። በተጨማሪም ከ 20 በላይ የአማራ ተማሪዎች ታስረው ይገኛሉ ።ከታሰሩ ተማሪዎች መካከልም አብዛኞቹ የት እደታሰሩ የሚታወቅ ነገር የለም ። ሆኖም እነዚህ ከ 400 በላይ የሚሆኑ የአማራ ተማሪዎች በቤተ-ክርስቲያን እና መስጊድ ተጠግተው እንደሚገኙ እና በችግር ላይ እንዳሉ ማወቅ ተችሏል። ሌላው በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ከ 15 ቀን በላይ ያስቆጠረው ግጨት በመጀመሪያ ሃይማኖቶታዊ መነሻ ምክንያት ያለው መስሎ ግን ብዙም ሳይቆይ መልኩን እና ቅርፁን ቀይሮ የአማራ ተማሪዎች ላይ ባነጣጠረ መልኩ አሰቃቂ ድብደባ እና ማዋከብ እየተደረገ እንዳለና ይህም በአካባቢው ተወላጆች እና ነዋሪዎች የተደገፈ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። በዚህም ምንም እንኳን ዩኒቨርስቲው የማጠቃለያ ፈተና እያስፈተነ ቢሆንም ተማሪዎች ፈተናውን እየጣሉ ወደቤታቸው እየተመለሱ ይገኛሉ። ስለሆም ማህበራችን የአማራ ተማሪዎች ማህበር (አተማ) በድሬድዋ እና በዋቻሞ ዩኒቨርስቲ በሚገኙ የአማራ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ድብደባ፣እስር እና ማዋከብ አስመልክቶ የሚከተሉት ተግባራት እንዲፈጸሙ ለሚመለከተው አካል ሁሉ ያሳስባል። 1ኛ በድሬድዋ ዩኒቨርሲቲ በመማር ላይ እያሉ የታሰሩ የአማራ ተማሪዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እና ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ። 2ኛ በቤተ-ክርስቲያን እና መስጊድ ተጠግተው የሚገኙ ከ400 በላይ የሚሆኑ የአማራ ተማሪዎች በአስቸኳይ ወደ ትምህርት ገበታቸው እዲመለሱ ። 3ኛ በዋቻሞ ዩኒቨርስቲ የአማራ ተማሪዎች ላይ እሚደረገው ድብደባ እና ማዋከብ እንዲቆም እና ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እንዲሁም በዚህ ምክንያት ፈተና ያለፋቸው ተማሪዎች እንዲፈተኑ እንጠይቃለን። የሚመለከተው አካል ሁሉ በአስቸኳይ ተረባርቦ ከላይ የጠየቅናቸውን ጥያቄዎች መፍትሔ የማይሰጣቸው ከሆነ ማህበራችን የአማራ ተማሪዎች ማህበር (አተማ) ጉዳዩን ከክልል ትምህርት ቢሮ አንስቶ እስከ ፌደራል ትምህርት ሚንስቴር ድረስ ይዞ እንደሚቀርብ ልናሳስብ እንወዳለን። በተጨማሪም ወደ ሚመለከተው የፍትሕ ተቋም በተዋረድ ጉዳዩን ይዘን የምንቀርብ ይሆናል። ሆኖም ይህ ሳይሳካ ቀርቶ የአማራ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው በደል እና ግፍ ካላቆመና ተባብሶ ከቀጠለ በቀጣይ በምናደርገው ሁለንተናዊ ትግል ለሚፈጠረው ችግር ሃላፊነቱን የሚወስዱት የድሬድዋ እና የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም መንግሥት መሆናቸውን ለማሳወቅ እንወዳለን። መጋቢት ፩/፳፻፲፭ ዓ.ም “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24
Source: Link to the Post