በቀደሙ መግለጫዎቻችን ላይ ተቋማችን በሽግግር ላይ እንደሚገኝና ጊዜያዊ ትየፋይናንስ ችግር እንደገጠመው ቦርዱ ገልጿል። ሽግግርን በተመለከተ የተወሰኑ ውሳኔዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ እየተተገበሩ መሆናቸውን እያሳወቅን፤ የተቋሙን ጊዜያዊ የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ ቦርዱ ብዙ አማራጮችን ያየና የሞከረ፣ እየሞከረም ያለ ሲሆን በሁኔታው አስገዳጅነት ምክንያት፤ የሥራ ማስኬጃ ወጮችን በተመለከተ አንዳንድ ለውጦችን በማድረግ ላይ ይገኛል። ከለውጦቹም መካከል በሀገር ቤትና በውጭ የሚገኙ ቅርንጫፎችን የሰው ኃይል፣ የሕንጻ ኪራይንና የሳተላይት ወርኃዊ ወጮችን በመገምገም አንዳንድ ጊዜያዊ የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ወስኗል። በዚህ ውሳኔ የመጀመሪያ ምዕራፍም የተቋሙን ሕልውና በሚያስቀጥል መልኩ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን ቅርንጫፍ የሠራተኞች ደመወዝና የሕንጻ ኪራይ የተመለከቱ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
የሕንጻ ኪራይን በተመለከተ፤ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን ስቱዲዮ አነስ ያለ ወጭ ወደሚያስወጣ የኪራይ ሕንጻ ወይም ሌሎች አማራጮች እንዲፈለጉ የተወሰነ ሲሆን፤ የነባሩ ቢሮ የኪራይ ውል፡ አማራጮች እንደተገኙ በአጭር ጊዜ እንዲቋረጥ መወሰኑን ቦርዱ ሊያሳውቅ ይወዳል።
የሰው ኃይልን በተመለከተ፤ እስካሁን የረጂም ጊዜ የቅጥር ውል ከነበራቸው የሙሉ ጊዜ ባለሙያዎች መካከል፤ ግማሹን የሰው ሀይል በመቀነስ የባለሙያዎች የቅጥር ውል እንዲቋረጥ የተወሰነ ሲሆን ባለሙያዎቹ ከነሱና ከቦርዱ ቁጥጥር ውጭ ተቋሙ በከፍተኛ ገንዘብ ችግር ምክንያት አገልግሎት ሊያቋርጥ ጫፍ ላይ በመድረሱና ብዙ ጥረቶችን ቢያደርግም መፍትሔ በማጣቱ ቦርዱ ይህን ውሳኔ እንዲያሳልፍ ተገዷል። ባለሞያዎችም እስካሁን በተቋሙ ውስጥ ለነበራቸው ፍሬያማ ቆይታና ላደረጉት ጥረት ትልቅ ክብርና ምስጋና እንዳለው ቦርዱ መግለፅ ይወዳል።
በዚህ አጋጣሚ፤ የሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ ለአሥራት ደጋፊዎችና ቤተሰቦች እንዲሁም ታዳሚዎች ይህ የማስተካከያ ዕርምጃ በመደረጉ ምክንያት ከአሥራት ዲሲ በየሳምንቱ ረቡዕና አርብ ይተላለፍ የነበረው የዜና ዝግጅት ላልተወሰነ የጊዜ ገደብ የተቋረጠ መሆኑንና ሌሎቹ ሁለት ዝግጅቶች (የአሥራት እንግዳና የጋዜጠኞች ምልከታ) አቅም እንደፈቀደ የሚቀርቡ መሆናቸውን እያሳወቀ፤ ሌሎች ፕሮግራሞች ባሉበት የሚቀጥሉ ሲሆን፤ ሁኔታዎች ሲመቻቹ አሥራት በሕዝባችን ፍላጎት ልክ በይዘትና በጥራት ተጠናክሮ እንደሚመጣ ተስፋ እንዳለው ሊገልጽ ይወዳል።
በተጨማሪም፤ የአሥራት የሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ የወጭ ቅነሳ ብቻውን ተቋሙን ሊታደገው እንደማይችልና፤ የሚድያውን አስፈላጊነትና ቀጣይነት የምታምኑ ሁሉ ተቋሙን በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በሃሳብ ለማጠናከር በተዘረጉት የገንዘብ ማሰባሰቢያ አማራጮች እና አድራሻዎች ያልተቆጠበ ድጋፋችሁን በማበርከት አሥራትን እንድትደግፉ በጽኑ እናሳስባለን።
ለጊዜያዊ ዕርዳታ በጎፈንድሚ “https://www.gofundme.com/f/gofundmecomfASRAT“ን፣ እንዲሁም ለወርኃዊ ድጋፍ “https://charity.gofundme.com/o/en/donate-widget/7297“ን በመጠቀም ድጋፋችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ እያሳሰብን፤ በምናባችሁ “አሥራት ባይኖር…” ብላችሁ ላንድ አፍታ አስባችሁ፤ በሕዝባችንና በሀገራችን ሊፈጠር የሚችለውን የመረጃ ክፍተት እንዲሁም የድምፅ መታፈን ለአፍታም ቢሆን በዓይነ-ኅሊናችሁ እንድታዩት በትህትና እንጠይቃለን።
ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም፤ ተቋሙን ከዚህ ለማድረስ በብዙው ለደከማችሁ የተለያዩ ግለሰባዊ እና ቤተሰባዊ ዋጋ ለከፈላችሁ እና ሚዲያው ለድምፅ አልባዎች ድምፅ ሆኖ እንዲቀጥል ለጣራችሁ ባለሙያዎቻችን እና የአማራ ህዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች በህዝባችን እና በሀገራችን ስም ልባዊ ምስጋና እናቀርባለን። በተጨማሪም፤ አሥራትን ወደተሻለ ተቋምነት ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት ድጋፋችሁ፣ አገልግሎታችሁና ክትትላችሁ እንዳይቋረጥ እየጠየቅንና በሙያችሁ ሚዲያውን ለመርዳት እና ለማገልገል ለምታሳዩት ፈቃደኝነት ከጎናችሁ እንደማንለይ እየገለጽን፤ እናንተም በሙያችሁ ለመቀጠል በምታደርጉት ጥረት በምንችለው ሁሉ ከጎናችሁ እንደማንለይ ለማሳወቅ እንወዳለን።
ድር ቢያብር፤
አንበሳ ያስር።
እናመሰግናለን።
የአሥራት ሚድያ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ፤
https://www.gofundme.com/f/gofundmecomfASRAT
ዐርብ መጋቢት ፲፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓመተ ምህረት።