You are currently viewing ከአሥራት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

ከአሥራት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

የአስራት ሚዲያ የአማራን ህዝብና ኢትዮጵያን በተመለከቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ታሪካዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ለድምፅ አልባዎች ድምፅ በመሆን ባለፈው አንድ ዓመት መተኪያ የሌለው አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል።

የአሥራት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ መጋቢት ፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓመተ ምህረት ሙሉ አባላቱ(፲፭ቱ) በተገኙበት ባካሄደው ስብሰባ በአሥራት ሚድያ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል። ቦርዱ በሚዲያው ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ላይ ጥልቅ ውይይት አድርጓል።

ቦርዱ በውይይቱ ላይ በሚድያው የፋይናንስ፣ የሰው ኃይል፣ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ፣ የአቀራረብ ይዘት፣ የፕሮግራም ጥራት፣ የተቋም ፖሊሲዎችና መመሪያዎች እንዲሁም በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ችግሮችና ክፍተቶች መኖራቸውን ተገንዝቧል።

በተጨማሪም ቦርዱ ከአሥራት ቤተሰቦችና ደጋፊዎች በቅጥርና በሰው ሀይል አስተዳደር፣ በፋይናንስና በኦዲት፣ በሽግግርና ርክክብ፣ በሚዲያው ፍቃድና ምዝገባ ባለቤትነት እንዲሁም በመሰል ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎች መኖራቸውን በተለያዩ መንገዶች ለመገንዘብ ችሏል።

ከዚህም በመነሳት ቦርዱ የሚከተሉትን ውሳኔዎች እና ህዝባዊ ጥሪ አሳልፏል።

፩) ነባሩ መሥራች ኮሚቴ የሚዲያውን ፍቃድና ምዝገባ ባለቤትነት፣ የሚዲያ ንብረቶች፣ ሕጋዊ ሰነዶች፣ የፋይናንስ ሰነዶች፣ ውሎች አና ሌሎች አስፈላጊ ንብረቶች ወደ አዲሱ ቦርድ
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሽግግሩን ለመጨረስ እየሰራ እንደሚገኝ ይገልጻል።

፪) የአሥራት ጠቅላላ ጉባዔ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚቴ አዋቅሮ የተቋሙን ፋይናንስ በገለልተኛ ኦዲተሮች በአጭር ቀናት ኦዲት እንዲያስጀምርና ኦዲቱ እንደተጠናቀቀ ጠቅላላ የፋይናንስ መረጃ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ ተወስኗል።

፫) የተቋሙ ኃላፊዎችም ይሁኑ ሰራተኞች ከተቋሙ ፖሊሲና አሠራር ውጭ በሕዝብ መካከል ልዩነት የሚፈጥር አስተያየት መስጠትም ሆነ ማስተላለፍ የተከለከለ ሲሆን፤ ይህንን ተላልፎ በተገኘ አካል ላይ በተቋሙ መመሪያ መሠረት አስተዳደራዊ የእርምት ዕርምጃ እንደሚወስድ ይገልፃል።

፬) አሥራት የሕዝብ ተቋም በመሆኑ ማናቸውም የሃሳብ ልዩነት ወይም ቅሬታ ያላቸው አካላትን አቅርቦ ለማወያየትና ሃሳቦችን ለማድመጥ ቦርዱ አወያይ ኮሚቴ ያቋቋመ ሲሆን፤ ኮሚቴውም ስራውን የጀመረ መሆኑን ይገልጻል።

፭) ለተቋሙ ቀጣይነት ያልተቋረጠ የሕዝብ ድጋፍና አስተያየት ወሳኝ በመሆኑ፤ ከአማራ ሕዝብና ከአማራ ሕዝብ ወዳጆች ጋር በተቻለ ፍጥነት በተለያዩ መንገዶች ሕዝባዊ ውይይቶች እንዲካሄዱ ተወስኗል።

፮) ቦርዱ የተቋሙን ወቅታዊ የፋይናንስ ይዞታ ከገመገመ በኋላ፤ የፋይናንስ እጥረቱን ለመቋቋም፤ የተለያዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያና የወጭ ቁጠባ መፍትሔዎችን የወጠነ ሲሆን፤ የዚህም አንድ አካል የሆነውን የአጭር ጊዜ የፋይናንስ አሰባሳቢ ኮሚቴ አዋቅሮ ወደሥራ እንዲገባ አድርጓል። በተጨማሪም የተቋሙን ወጭ ለመቀነስ በሚቀጥለው አንድ ሳምንት የምክር ሃሳቦችን አጥንቶ የሚያቀርብ ፮ (ስድስት) የቦርድ አባላት የሚሳተፉበት ኮሚቴ አዋቅሯል።

፯) በቀጣይ ጊዜያት ቦርዱ የተቋሙን አጠቃላይ ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎችን እየገመገመ፤ ለሚለያቸው ተግዳሮቶችና ክፍተቶች የመፍትሔ ሃሳቦችን እንደሚያስቀምጥ ይገልጻል።

በመሆኑም የአሥራት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ለመላው ሕዝባችንና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የሚከተሉትን ጥሪዎች ማቅረብ ይፈልጋል።

፩) አሁን ባለው ሁኔታ ይህ ሕዝባዊ ተቋም ጊዜያዊ የፋይናንስ እጥረት ስላለበት፤ የሚድያውን ጥቅምና ተጽዕኖ በመገንዘብ፤ እንዲሁም መጪውን ሀገራዊ ምርጫ ጨምሮ የሕዝባችንንና የሀገራችንን መጻዒ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት አሥራት ሚድያን በገንዘብ፣ በሃሳብና በሌሎች ሚድያውን ሊጠቅሙና ሊያሳድጉ በሚችሉ አማራጮች ሁሉ ድጋፍና ዕርዳታ እንድታደርጉ ጥሪ ያቀርባል።

፪) ይህንን ሚድያ በዘላቂነት ለማስቀጠል በቦርዱ በኩል የታቀዱ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው፤ ሁሉንም የማኅበረስብ አካል ለማሳተፍ ይቻል ዘንድ መዋቅር የተዘረጋ በመሆኑ፤ ማንኛውም አማራና የአማራ ሕዝብ ወዳጆች በአሥራት ሚድያ ጉዳዮች ተሳትፎ በማድረግ እንዲያግዙ በሕዝባችን ስም ጥሪ ያቀርባል።

፫) አሥራት ሚድያን አስመልክቶ የሚሰጡ አስተያየቶች በአመዛኙ መነሻቸው ከቀናነትና ደጋፊዎቹ ለተቋሙ ካላቸው የባለቤትነት ስሜት የሚመነጩ ጠቃሚ ግብአቶች እንደሆኑ የስራ አመራር ቦርዱ ይገነዘባል። ሆኖም፤ ቦርዱ የተቋሙን ሁለንተናዊ ይዘት ለማስተካከል በሚጣጣርበት በዚህ ወቅት በቦርዱ አባላት ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አላስፈላጊ ተፅዕኖ ለማሳረፍ መሞከር ተገቢ እንዳልሆነ ቦርዱ ይገነዘባል። ለተቋሙ ግንባታ የሚዉሉ አዎንታዊ ሀሳቦችና አስተያየቶች በአስራት ቤተሰቦች የሚገለፁበት መንገድ በፍጥነት እንደሚመቻች ቦርዱ ይገልጻል። በውስጥ መስመር የሚደረጉ የውይይት ጥሪዎችና የሚሰጡ አስተያየቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ከዚያ ባለፈ ግን በማኅበራዊ ሚድያም ሆነ በሌላ መንገድ የሚሰጡ አሉታዊ አስተያየቶችና አላስፈላጊ አስተዳደራዊ ጫናዎች ከልማታቸው ጥፋታቸው፣ ከገንቢነታቸውም አፍራሽነታቸው ስለሚያመዝን ከመሰል ተግባራት በመታቀብ፤ ችግሩን የሁላችን አድርጎ በማየትና ራሳችንንም የመፍትሄው አካል በማድረግ ቦርዱ የተሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ ይወጣ ዘንድ እገዛ እንዲደረግለት ጥሪ ያቀርባል።

እናመሰግናለን፤
የአሥራት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ፤
ማክሰኞ መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓመተ ምህረት።

Leave a Reply