ከአውራ፡ መንደር፥ አውራ፡ አባውራ።” የምስራቅ አማራ ፋኖ ምርቃን በወልድያ። እነሸዋ ረገድ ገድሌ፣ እነ አብዲሳ አጋ፣ እነ ራስ አሉላ አባ ነጋ፣ እነ ገብርዬ፣ እነ ንጉሥ ጦና፣ እነ መይሳ…

ከአውራ፡ መንደር፥ አውራ፡ አባውራ።” የምስራቅ አማራ ፋኖ ምርቃን በወልድያ። እነሸዋ ረገድ ገድሌ፣ እነ አብዲሳ አጋ፣ እነ ራስ አሉላ አባ ነጋ፣ እነ ገብርዬ፣ እነ ንጉሥ ጦና፣ እነ መይሳው ካሳ፥ እነ እምዬ ሚኒልክ፣ በአጠቃላይ የአፋሩ፣ የጅማው፣ የወሎው፣ የወላይታው፣ የጅግጅጋው፣ የጎንደሩ፣ የጉራጌው፣ የጎጃሙ፣ የሸዋዉ፣ የትግሬው፣ የጋምቤላው፣ … የጥንቱ ሀገራዊ አርበኛ ሁሉ የሚጠራበት ነው “ፋኖነት” እና “ነፍጠኛነት።” ከቃሉ ባለፈ ጥበባዊ ቅኝቱ በጥንታዊዉ የአባቶቻችን ወታደራዊ ሳይንስ ስያሜና አደረጃጀት ከ”ልጅ” እስከ “ንጉሠ ነገሥት (አፄ)”፤ ዛሬ ላይም ከወታደር እስከ ማርሽያል ፊልድ ባለው መዋቅርና ስያሜ ለወገንና ለሀገር ደሙን ሳይሆን ሕይወቱን የሚሰጠው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከጠላት ጋር ፍልሚያ ሲያደርግ ያጅባል፤ ኪናዊ ጥበቡ…ን እንደያዘ፣ የመልእክቱን ዓይነ ውሃ እንደጠበቀ ዘመናትን ዘልቋል። “ፋኖ” እና “ቸበለው” “ወዳጅህን፡ በምን፡ ቀበርከው? በሻሽ፤ የኋለኛው፥ እንዳይሸሽ።” እንዲሉ በ”ፋኖ” እና በ”ቸበለው” የሀገር ፍቅር ኪናዊ ድርሰቶች እና የበገና ድምፆች አእምሮው በሀገር ፍቅር ተነድፎ፤ ለወገኑ ቀናዒ ሆኖ ህይወቱን ለሌሎች አሳልፎ በመስጠት፣ በባህሪው የዕድሜና የማዕረግ ፆታን አጣምሮ በያዘ የተባ የቋንቋ አገላለጽ “የልፍኝ አሽከር” እና “ጋሻ ጃግሬ” እያሉ ፍቅራቸውን ይገልፁለታል፣ ያከብሩታል፣ ያወድሱታል። ፈሪውን፣ ሆድ አደር ባንዳውን፣ ዘራፊውን፣ ቀማኛውን፣ ይወቅሩበታል፣ አበያውን ያቀኑበታል፣ የማይቀናም ከሆነ ያወግዙበታል ጎሳዊ ሳይሆኑ ሕዝባዊ ከያንያን፣ የጎጥ ሳይሆኑ ዜጋዊ ጥበበኞች፦ “ቸ፡ በለው፡ የልፍኝ፡ አሽከሮች፥ ቸ፡ በለው፡ ሲተኳኩሱ፤ ቸ፡ በለው፡ ጋሻ፡ ጃግሬዎች፥ ቸ፡ በለው፡ ሲተኳኩሱ፤ ቸ፡ በለው፡ ሞሰብ፡ ቀዳጆች፥ ቸ፡ በለው፡ ወዴት፡ ደረሱ? ቸ፡ በለው፡ ባይወለድስ፥ ቸ፡ በለው፡ የሰው፡ ምራጩ፤ ቸ፡ በለው፡ ሲራብ፡ ወገኑ፥ ቸ፡ በለው፡ ክብሩን፡ ለዋጩ፤ ይሉታል በ”ቸ፡ በለው።” የጥበብ ቅኝት። “ተኩሶ፡ ሲነጉድ፥ የፈሪ፡ ልምደኛ፤ ፊት፡ ለፊት፡ ተጋዳይ፥ ፋኖ፡ እንደ፡ መጋኛ። እረ፡ ተው፡ በሉት፥ ያን፡ ባለ፡ ቡሎ፤ ሰጠው፡ ለነፋስ፥ አንጓሎ፡ አንጓሎ፡ አንጓሎ፡ አንጓሎ።” ይሉታል “ፋኖ” በሚለው ድርሰታቸው ስሜተኞቹ ሳይሆኑ ጥበበኞቹ፤ ነጋዴዎቹ ሳይሆኑ የሀገር ፍቅር በልብ ሰሌዳቸው የተቀረፀው፤ በአእምሯቸው የሰረጸው ከያንያን እንደ ዓድዋ ዓይነቱን በሜካናይዝድ፣ በባህር እና በአየር ኃይል ተደራጅቶ የመጣውን የውጭ ወራሪ በባህላዊ የጦር አሰላለፍ እና ትጥቅ ጭምር በማነጻጸር ከእኛ ኢትዮጵያውያን አልፎ የመላ አፍሪካውያንን በአጠቃላይ በከለሩ ብቻ እንደበታች ይቆጠር የነበረውን ጥቁር ሁሉ አንገት ቀጥ እንዲል ያስቻለውን ጠላት ዶጋ አመድ የሆነበትን ታሪክ ቀጥተኛ የውጊያው ተሳታፊዎችን በጥበብ የዘከሩበት ጥበብ ዛሬም ላይ የእውነተኛው አርበኛ ምንጭ እንዳይደርቅ አድርጓል። ዳሩ ግን “የበሽታ፡ ክፉ፥ ቁርጥማት፤ የኃጢአት፡ ክፉ፥ ቅናት።” ሆኖ የኢትዮጵያውያን የጀግንነት የክብር ስያሜ ለአንድ ወገን ብቻ በመለጠፍ ለፖለቲካ ፍጆታ እንዲመች ተደርጎ ተስሏል። በወቅቱ የዘመነ መሳፍንት ርዕዮተ ዓለም እሳቤ አራማጆች። ምስጢሩ ክብር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” በሚለው የጥበብ ስጦታቸው የ”ፊት አውራሪ መሸሻ” እና “የአበጀ በለው” ጉዳይ ነው የሚሆነው። በ2013 ዓ.ም መገባደጃ ቀደም ብሎ ክልላዊ፤ በመቀጠልም ሀገራዊ የክተት አዋጅ ሲጠራ መንግሥታዊ ጥሪውን ተቀብለው ኢትዮጵያውያን ወገኖች በሀብታቸው፣ በእውቀታቸው፣ የውጩን ፕሮፓጋንዳ እና የማዕቀብ ተጽዕኖ ከመመከት እስከ ምሽግ መውረድ የባንዳነት መንፈስ ከሰፈረባቸው ውሱኖች በስተቀር ያልተሳተፈ የለም። ላይ ላዩን ሲያዩት የእርስ በእርስ በሚመስል ውስጡ ግን የምዕራባውያን የውክል ጦርነት በግልጽ ጎልቶ በታየበት እና ዛሬም ላይ ባልተቋጨው ጦርነት ከሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ጎን በመሰለፍ ሀገርን ከመፍረስ ለመታደግ ከተፋለሙት ኢትዮጵያውያን ፋኖ አንዱ ነው። መንግሥት የክተት ጥሪ ያወጀውን የህልውና ዘመቻ ባለበት እንዲቆም ማድረጉ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም ምንም እንኳ ሀገራችን በዘመነ ኢህአደግ እንዳይኖር የተደረገውን የባህር ኃይል ጭምር አስተማማኝ ደረጃ የመገንባቱ እና ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጅ የታጠቀ መከላከያ ሰራዊት መገንባቷ ቢታወቅም፤ የተለያዬ የግፍ በትር እስከ ሞት ፅዋ በወገኑ ላይ የተፈጸመበት ሕዝብ ግን ወታደራዊ ስልጠና ይሰጠን ቀዳሚው ጥያቄ ነበር። የስልጠና ጥያቄው ዓላማ ባለመደራጀቱ ፣ ባለመሰልጠኑ ያስከፈለውን መስዋዕትነት በማሰብ ለሚመጣበት ጥቃት መከላከል፣ መመከት እንዲችል እና መንግሥት ነገም ላይ ለሌላ የክተት አዋጅ ቢጠራ ሙያ መያዙ ለመንግሥትም ጥሩ አቅም እንዲሆን “ከአውራ መንደር፣ አውራ አባውራ፤” እንደሚሻል ከግፍ ፈጻሚዎቹን የወረራ ሁኔታ በመነሳትና በማሰብ የዙር ስልጠናው ተጠናክሮ ቀጥሏል። ወልድያ ከተማ ላይ የምስራቅ አማራ ፋኖ የወልድያና አካባቢዋ ሰልጣኝ ከሦስት ወራት በላይ ያሰለጠናቸውን እጩ ፋኖዎች ዛሬ ሚያዝያ 17 ቀን 2014 ዓ.ም በማስመረቅ ላይ ይገኛል። ነገሩ “ጥቃት ከጥንብ ይገማል።” ሆኖበት ምክንያቱም ደግሞ የትግራይ ወራሪ ቡድን ከ12 ዓመት እስከ 60 ዓመትና በላይ በሆነ የሰው ኃይል አሰማርቶ ጥቃት ስለተፈጸመበት አርፎ ለመቀመጥ ኅሊናው ሊያስተኛው አልቻለም። የህልውናው ዘመቻ መቼ ተጠናቆ የስጋት ቀጠናዎች ሳይሆን፤ የስጋት እንቁላል አስፈልፋዮች ሀሳባቸው መክኖ፤ የውጭ ጠላቶችም ከኢትዮጵያ ላይ የሴራ ሀሳባቸው ከሽፎ፤ በምትኩ የሰላም፣ የልማት፣ የእኩልነት፣ የአብሮነት፣ የአንድነት የሀሳብ ልዕልና ነግሦ ሁሉም በአንድ ልቡ ወደ መደበኛ ሥራው የሚመለስበት በሁሉም ዘንድ የሚናፈቅ እና የሚጠበቅ ቀዳሚው ጉዳይ ነው። በከተማዋ ከአሁን በፊት በሁለት ዙር ሕዝባዊ ሰራዊት የተመረቀ ሲሆን፣ የዛሬው በፋኖ አደረጃጀት የተመረቀው በከተማዋ የመጀመሪያው ዙር ነው። ሁለቱም በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊታችን እዝ የሚመሩ፣ የሚሰማሩ እንጂ እጃቸውን በማስረዘም ዕኩይ ተልዕኮ በሚሸከሙ ኃላፊነት በተለየው መልኩ የማኅበራዊ ድረ ገጽ አሳዳጅና ተሳዳጅ በማድረግ በሚያንጸባረቁ፣ እንዲሁም በትክከለኛው ፋኖ ስም በመነገድ ሕወሓት በቀደደው የጎጠኝነት ቦይ በሚፈሱ መንደርተኞች ሳይሆን፣ እንደሌሎች አካባቢዎች ለመንግሥትና ለሕዝብ አጋዥ እንጅ እዳ ላለመሆን በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ይታወቃል። ሚያዝያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም ወልድያ ከተማ ኮሙኒኬሽን

Source: Link to the Post

Leave a Reply