ከአዲስ አበባ በተወሰዱ አካባቢዎች በተለይም በሸገር ከተማ አስተዳደር ኩራ ጊዳ ክ/ከተማ በተለምዶ አበባ ልማት ለገኦላ አካባቢ አሁንም የዜጎችን ቤት ማፍረሱ ተባብሶ ቀጥሏል ተባለ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መጋቢት 8 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በሸገር ከተማ አስተዳደር ኩራ ጊዳ ክ/ከተማ በተለምዶ አበባ ልማት ለገኦላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አሁንም የዜጎችን ቤት ማፍረሱ ተባብሶ ቀጥሏል። ቤት ፈረሳ ከጀመረ ሁለት ወራት ማስቆጠሩን ነዋሪዎች ለአሚማ ገልጸዋል። የዜጎች ቤት ማንነት እየተለዬ ከፈረሰባቸው አካባቢዎች ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ዳሌ፣ ድሬ፣ ቀርሳ፣ሚካኤል፣ገዋሳ፣ አርባ አራት፣ሚሽን፣ ጀሞ ተራራ መድኃኒያለም፣ ፋኑኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ለቡ ባቡር ጣቢያ አካባቢ፣ኤርቱ ሞጆ፣ በጨሪ መድኃኒያለም፣ ቡራዩ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ። በዚህም በአብዛኛው ተጎጅዎች የአማራ ተወላጆች መሆናቸው ተገልጧል። አሁንም ቤት ማፍረሱ በብዙ አካባቢዎች እንደቀጠለ ነው። ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች በአብዛኛው በቀን ስራ ተሰማርተው ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ህይወት ይመሩ ስለነበር ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ የከፋ ስለመሆኑ ተጎጅዎች ተናግረዋል። መንግስት እየሄደበት ያለው መንገድ ህግ ማስከበር ሳይሆን ዜጎችን በማንነት እየለዬ ቤታቸውን በማፍረስ እና ማሰቃዬት በመሆኑ ይህ አካሄድ ለምንም ለማንም በዘላቂነት የሚጠቅም ባለመሆኑ ሊቆም ይገባዋል ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።
Source: Link to the Post