
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመውሰድ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረሃል በሚል በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ሲመላለስ የሰነበተው ተማሪ ጆን ተሻገር በ50 ሽህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ ትዕዛዝ ተሰጠ። የአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ግንቦት 16/2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ግቢ በመውሰድ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረዋል በሚል ከከሰሳቸው የአማራ ተማሪዎች መካከል ጆን ተሻገር በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ግንቦት 16/2015 በነበረው ችሎት በ50 ሽህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ ተወስኖለታል። የአሁኑ የዋስትና ገንዘብ ደጋፊ ከሌላቸው ተማሪዎች አንጻር የተጋነነ መሆኑን የገለጸው ጠበቃ ሀብተ ማርያም ጸጋዬ ቀደም ሲል በሁከትና ብጥብጥ ተጠርጥሯል በተባለው ወንጀል ተመጣጣኝ የሆነ በ6 ሽህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ በሚል የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት መወሰኑን አውስቶ ይህም ክፍያ በጓደኞቹ በኩል መፈጸሙን ጠቁሟል። በመሆኑም በዋስትናው ጉዳይ ይግባኝ ሊጠይቁ እንደሚችሉ ጠቁሟል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተወስዶ ለአንድ ወር ገደማ በእስር ላይ በሚገኘው የ3ተኛ ዓመት የህግ ተማሪ ላይ በፍ/ቤት የተወሰነው የዋስትና ገንዘብ ፍትሃዊ አይደለም ሲል ችሎቱን የታደመ ቤተሰቡም ለአሚማ ተናግሯል። በተያያዘ ተማሪ እዘዝ ሞላ ተሻለ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ አመት የህዝብ አስተዳደሪ ልማት ተማሪ ግንቦት 2/2015 ምሽት የታፈነ መሆኑ ይታወቃል።
Source: Link to the Post