ከአዲስ አበባ – ደሴ የሚገኘው መንገድ “ላልተወሰነ ጊዜ” ተዘገቷል

ከአዲስ አበባ – ደሴ በሚገኘው አውራ ጎዳና ከዛሬ የካቲት 16 ቀን 2016 ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የሰውና የንብረት እንቅስቃሴ እገዳ እንደተጣለ አዲስ ማለዳ ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

በተጨማሪም ከደሴ – ሸዋሮቢት_ ደብረ ብርሃን እንዲሁም ከደብረ ብርሃን -ሸዋሮቢት – ደሴ የሚደረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለጊዜው እንዲቆም ተወስኗል።

እገዳው የተጣለው ከሰሞኑን ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ በሚወስደው የአስፋልት መንገድ ላይ “በንፁሀን መንገደኞች ላይ ግድያ፣ እገታ፣ ዘረፋና መሰል አሰቃቂ ወንጀሎች በታጣቂዎች እየተፈጸመ በመሆኑና ጠንካራ የህግ ማስከበር ኦፕሬሽን ስራ እየተሰራ” በመሆኑ ነው ሲል ኮማንድ ፖስቱ አስታውቋል።

ይኼውም ከቀጣናው የመንግስት አስተዳደር፣ ህዝብ፣ የአካባቢ የፀጥታ አካላት እና የፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር የአገር መከላከላያ ሠራዊት ወንጀለኞችን በአጭር ጊዜ ለህግ የሚያቀርብ ይሆናል ብሏል።

በተመሳሳይ አዲስ ማለዳ ከአዲስ አበባ ወደ ወሎ እንዲሁም ወደ ደሴ የሚጓዙ ሰዎች መንገድ ላይ በታጣቂዎች ጥቃት እየተፈጸመባቸው መሆኑን የደረሷት ጥቆማዎች ያመላክታሉ።

“ሁሉም የመንግስት የፀጥታ ሀይሎችና የመንግስት ተቋማት እገዳውን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ”፣ ዜጓች መንገድ ላይ እንዳይጉላሉ ከመነሻ መረጃ እንዲሰጣቸው፣ የትራፊክና የመንገድ ትራንስፖርት ተቋማት መነኀሪያዎች፣ የብዙኀን መገናኛዎች ትብብር እንዲያደርጉ የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አሳስቧል።

ይህንን ክልከላም ይሁን ሌሎች ቀደም ብለው በኮማንድ ፖስቱ የተላለፉ እገዳዎችን ወይንም ክልከላዎችን ጥሶ የተገኘ ግለሰብ፣ ቡድን፣ ተቋም ወይም ማንኛውም አካል በአሰቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት ተጠያቂ ይሆናል መባሉንም አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

በአማራ ክልል ለተለያዩ ጥያቄዎች እየታገልኩ ነው የሚለው “ፋኖ” በመንግስት “ጽንፈኛ ኃይል” ተብሎ የትጥቅ ውጊያ ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል። በክልሉ ሁኔታ ሳቢያ ለስድስት ወራት ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘሙን አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይዘነጋም።

Source: Link to the Post

Leave a Reply