በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
#Ethiopia | በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ምልዓተ ጉባኤ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሶዶ ደሙ ወረዳ ሀሮ በዓለወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጸመውን ኢ-ሲኖዶሳዊ የሆነ የሃይማኖት፣ የቀኖናና የአስተዳደር ጥሰት አስመልክቶ በሰፊው ተወያይቶ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የሃይማኖት ልዩ ልዩ ሕግጋት ውጭ ጳጳስ ሾመናል ባሉ አካላት እና ተሹመናል በሚሉት አካላት ላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግጋት በሚፈቅድለት መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸው ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት በመሻር አውግዞ የለያቸው ሲሆን፣ በዕለቱ ይኸው ውግዘት በመላው ዓለም ለሚገኙ የዕምነቱ ተከታዮች ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምዕመናን ውግዘቱን እንዲያውቁት መንግሥትም በዚህ ጉዳይ የሚፈጠር ችግር እንዳይኖር ሰላም እንዲያስከብር ዓለም በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ መረጃ ኖሮት ቤተ ክርስቲያን ለወሰነችውም ውሳኔ ግንዛቤ እንዲወስድ በመግለጫ ማሳወቃችን ይታወሳል፡፡
በዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታይ የሆኑ አገልጋይ ካህናት እና ምዕመናን በመላው ዓለም የሚገኙት ደስታቸውን በመግለጥ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ሳይሸራረፍ እንደሚያስፈጽመ በልዩ ልዩ መንገድ እየገለጹ ይገኛል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚገኙ የልዩ ልዩ ሃይማኖት ተቋማትና ሲቪክ ማኅበራት የተፈጸመውን ድርጊት በመቃወም እና ቤተ ክርስቲያኒቱ የወሰነችውን ውሳኔ በመደገፍ ከጎናችን እንደሆነ እና አብረውን እንደሚሰሩ በልዩ ልዩ መንገድ እየገለጹልን ይገኛል፡፡ በዚህ ቤተ ክርስቲያናችን ከጎናችን ለቆሙትና ድጋፋቸውን ለገለፁልን ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የሃይማኖት እና የሲቪክ ተቋማት ምስጋናዋን አቅርባለች።
እነዚህ በሕገ ወጥ መንገድ ተሹመናል የሚሉት አካላትም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከማዕከላዊ መዋቅር ውጭ ተወግዘው ተለይተው እያለ በሌላቸው ሥልጣን ወዳልተፈቀደላቸው የአገልግሎት በታዎች በመግባት በሚያደርጉት ግብ ግብ በዕምነቱ ተከታዮች፣ በማህበረ ካህናትና ምዕመናን ላይ ሁከት እየተፈጠረ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ቤተ ክርስቲያናችን ለመንግሥት ያቀረበችው ሕግን የማስከበር እና የዜጎችን ሰላም የማስፈን ሥራ ጥሪ ተቀብሎ በሕገወጦች ላይ የወሰደው ምንም ዓይነት እርምጃ እየታየ አለመሆኑም ታውቋል፡፡
ይህ ሁሉ ድርጊት ሲፈፀም መንግሥት ሰምቶ እንዳልሰማ በዝምታያለፈውን ጉዳይ በጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሚኒስትሮችና ለካቢኔዎቻቸው በሰጡት የወቅታዊ ጉዳይ ማብራሪያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰተውን ወቅታዊ ችግር በማንሳት ልዩ ልዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡
ይኸውም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅዱስ ሲኖዶሱ እና ውጭ ባሉ አባቶች መካከል ሲካሄድ የነበረውን የዕርቅ ሒደት እልባት እንዲያገኝ ማድረጋቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችና ሕንጻዎች መካከል 4ኪሎ የሚገኙትን ሁለቱን ቀደምት ሕንጻዎች ለቤተ ክርስቲያን መመለሳቸው፣ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ሀገረ ስብከት ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ መሥሪያ ቦታ ማድረጋቸው! የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሀገር መሆኗን መግለጻቸው፣ የቤተ ክርስቲያኗ መዳከም ጉዳቱ ለቤተ ክርስቲያኗ ብቻ ሳይሆን ለሀገረ መንግሥቱም ጭምር መሆኑን መግለጻቸው፣ አግባብነት ያለውና ለዚህም : አድራጎታቸው ቤተ ክርስቲያናችን በወቅቱ በእውቅና ሽልማት አጅባ አመሰግናለች፡፡
ሆኖም ግን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም በተለያዩ የመንግሥት ሚዲያዎች በተላለፈው 36 ደቂቃ በሚፈጀው በሰላምና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚኒስትሮች ካቢኔ አባላት የሰጡትን ማብራሪያ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ተመልክታዋለች፡፡
በመሆኑም በቀረበው ማብራሪያ ላይ ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን አቋም እንደሚከተለው በዝርዝር እንገልጻለን፡፡
1. መንግስት በቤተ ክርስተያናችን የተፈጠረውን ሃይማኖታዊ እና ቀኖናው ጥሰትን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን ሲኖዶሳዊ ውሳኔ ሊያመጣ የሚችለውን ውጤት አቅልለው በአሁኑ ወቅት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረው ጉዳይ በጣም ቀላል ነው” በማለት ያዩበት መንገድ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ጉዳዩ ቀላል እና በንግግር የሚፈታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ይህ አገላለጽ በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውስጥ ጣልቃ እንደመግባት እና ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፋቸውን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ውሳኔዎች ያላቸውን ውጤት ወደ ጎን የተወ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ታምናለች፡፡ ከዚህም አልፎ ሁለቱም ወገን ውስጥ እውነት አለ፣ ሁለቱም አባቶቻችን ናቸው፣ ለማንም አንወግንም፤ ማንም የካቢኔ አባል እዚህ ውስጥ እጁን እንዳያስገባ፣ የሚሉት አገላለጾች በሕግ እውቅና የተሰጣትን ቤተ ክርስቲያን እና በሕጋዊቷ ቤተ ክርስቲያን ላይ በሕገ ወጥ መንገድ የተነሱትን ሕገ ወጥ ቡድኖች በአቻ እይታ ተመልክተው ሊወያዩ ይገባል በማለት የስጡት ማብራሪያ ሕገ ወጥነትን የሚያበረታታ፣ ለሕጋዊ ተቋማት መንግሥት ያለበትን የመጠበቅና ዋስትና የመስጠት ኃላፊነቱን ወደ ጎን ያደረገ፣ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ተቋማት በሕገ ወጥ ቡድኖች እንዲታመሱና እንዲተራመሱ ይሁንታ የሚሰጥ፣ ሕግንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንታዊ ታሪክና የሀገር ባለውለታነትዋን ያላገናዘበ፣ ማብራሪያ በመሆኑ ሊታረም የሚገባ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያሳስባል።
ከዚህም በተጨማሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትኛውም ካቢኔ በዚህ ጉዳይ እጁን እንዳያስገባ በማለት የሰጡት የሥራ መመሪያ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጋዊ ሰውነት አክብረው እና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ያሉትን በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ የሚያደርግና በሕገመንግሥቱ ለአስፈጻሚው አካል የተሰጠውን ሥልጣን የሚሽር፤ ሥርዓተ አልበኝነትን የሚያበረታታ፤ የሕግ የበላይነትን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል አድራጎት በመሆኑ ይህ አድራጎት እንዲታረምና መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን የሕግ የበላይነትና የተቋማትን ደህንነት የማረጋገጥ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያሳስባል፡፡
በሕገ መንግሥቱ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸው በግልጽ የተደነገገ እንደመሆኑ መጠን መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ላይ እጁን ማስገባት እንደሌለበት የምናምንበት ሐቅ ሲሆን ከዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ውጭ በሆነ መንገድ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የተፈጸመውን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ ጥሰትን እንደተራ ግጭት እና የግለሰቦች አለመግባባት በመቁጠር ትንታኔ ለመስጠት የተሄደበት ርቀት ሲታይ በአሁኑ ሰዓት ሕጋውያን የሆኑትን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ተልዕኳቸውን ከኤርፖርት ታግተውና ለሃይማኖታዊ አምልኮ የተሰበሰበውን ሕዝበ ክርስቲያን አዝኖ እንዲበተን በማድረግ ለአንድ አንጋፋና የሀገር ባለውለታ ሊቀጳጳስ የማይመጥን እንግልትና ማዋከብ መደረጉ ሳያንስ ይባስ ብሎ ለሕገወጡ የቡድን አባላት
Source: Link to the Post