
ከኦሮሞ ታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት ሁለት እግሮቿን ተመታ ክፉኛ በመቁሰሏ በምኒልክ ሆስፒታል የምትገኘው እናት “አሳክሙኝ” ስትል የትብብር ጥያቄ አቀረበች። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በአዲስ አበባ ዙሪያ አርባ አራት ማዞሪያ አካባቢ የዜጎች ቤት በማንነት እየተለዬ ለወራት ሲፈርስ መክረሙ እና አሁንም ድረስ እየፈረሰ መሆኑ ይታወቃል። በኦሮሚያ ልዩ ዞን በሰንዳፋ በኬ በረክ ወረዳ ለገኦላ ገበሬ ማህበር ይኖሩ የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ግን ሸገር ከተማ አስተዳደር በሚል እንዳካተቷቸው የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች በአርባ አራት ማዞሪያ አበባ ልማት አካበቢ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። በግብረ ኃይል እና በእስካቫተር በሚያፈርሱበት ወቅትም ቤታችን ለምን ይፈርሳል ብለው የጠየቁ ዜጎች ላይ አልሞ ተኳሽ የሽመልስ አብዲሳ ታጣቂዎች ጥይት በመተኮስ እስከማቁሰል የደረሰ እርምጃ ወስደዋል። አቶ ሽመልስ አብዲሳ በሚመራው ክልል በኦሮሞ ታጣቂ ሁለት እግሮቿን ታፋዋ ላይ የካቲት 14/2015 በጥይት የተመታችው እናት በምኒልክ ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላት ትገኛለች። በከፍተኛ ህመም እየተሰቃዬች የምትገኘው ወ/ሮ ንጋት ተሾመ መኮንን “አሳክሙኝ” ስትል የወገንን ትብብር ጠይቃለች። በእለቱ ጭሆት ሰምታ ከቤቷ ከመውጣቷ ያላሰበችው ነገር ገጠማት፤ አልሞ ተኳሹ የኦሮሞ ታጣቂ የካቲት 14/2015 ከቀኑ 5 ሰዓት ገደማ ሁለት እግሮቿን በጥይት መትቶ ጣላት። ጥይቱም በግራ እግሯ አድርጎ ቀኟንም አግንቷል፤ ከሰውነቷ አልፎም ቆርቆሮውን ቀዶ ጥይቱ ተገኝቷል። “ወደ ህክምና አትውሰዷት፤ ተዋት ትሙት” እያሉ የሚከለክሉ እና ተሸካሚዎችን የሚደበድቡ ታጣቂዎች ነበሩ ስትል ተናግራለች። ወ/ሮ ንጋት በጥይት ተመታ በወደቀችበት ወቅት በቅድሚያ ወደ ጤና ጣቢያ፣ከዛም ወደ በኬ ሆስፒታል ከተወሰደች በኋላ ከአቅማችን በላይ ነው በመባሏ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ገብታለች። የቁስለኛዋ ባለቤት አቶ የሱፍ አባተ ኃይሌ በበኩሉ የቀን ስራ ሰርተው ከዛሬ 12 ዓመት በፊት በመግዛት የኖሩበት ቤት እንዲፈርስ መደረጉን፣ ባለቤቱም በጥይት መመታቷን ተናግሯል። አቶ የሱፍ እንዳለው ከአምስት ሜትር በማይርቅ አካባቢ ባደፈጠ ታጣቂ ነው ባለቤቱ ወ/ሮ ንጋት የተመታችው። ቤት ያከራዬ እና እቃ በአደራ መልክ ያስቀመጠ የ3 ዓመት እስር እና የ15 ሽህ ብር ቅጣት አለበት በመባሉ በአካባቢው ያሉ የኦሮሞ ተወላጆችም ለመተባበር እየቸገራቸው እንደሆነ ተናግሯል። ከ6 ጓደኞቹ ጋር ሆኖ ቁስለኛ በተሸከመበት ከፍተኛ ድብደባ የተፈጸመበት አቶ የሱፍ በአካባቢው ከሚያውቁት የገንዘብ እርዳታ እንኳ እንዳይሰበሰብለት ተከልክሏል ሲል ገልጧል። የ6 እና የ10 ዓመት ሴት ልጆች ያሏቸው ሲሆን ለተገቢ ህክምና፣ ለመድኃኒት መግዣ፣ ለቤት ኪራይ እና ለሌሎች አስፈላጊ ወጭዎች መሸፈኛ አንድም ገንዘብ እጃቸው ላይ እንደሌ ተናግረዋል። ወ/ሮ ንጋት አሁን ላይ ሁለቱ እግሮቿ መንቀሳቀስ አይችሉም፤ ሽንት እና ሰገራ ቱቦ በመጠቀም ነው የምታስወግደው ሲልም አክሏል። አቶ የሱፍ አባተ በቤቱ ዙሪያ የተከለው ባህር ዛፍ ሌላ አንድ ቤት የሚያሰራ ቢሆንም ሁሉም ነገር ቀርቷል ይለናል። የምትችሉ በሚከተለው አካውንት ድጋፍ እንድታደርጉ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቁጥር 1000050647475 የሱፍ አባተ ኃይሌ
Source: Link to the Post