You are currently viewing ከኪረሞ ወደ አማራ ክልል ጎጃም በአባይ በርሃ በኩል ሲጓዙ ከነበሩ ከ16 አማራዎች መካከል አስሩ በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ በግፍ መገደላቸውን ከጥቃቱ የተረፈ የዐይን እማኝ ተናገረ። አማራ ሚዲያ…

ከኪረሞ ወደ አማራ ክልል ጎጃም በአባይ በርሃ በኩል ሲጓዙ ከነበሩ ከ16 አማራዎች መካከል አስሩ በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ በግፍ መገደላቸውን ከጥቃቱ የተረፈ የዐይን እማኝ ተናገረ። አማራ ሚዲያ…

ከኪረሞ ወደ አማራ ክልል ጎጃም በአባይ በርሃ በኩል ሲጓዙ ከነበሩ ከ16 አማራዎች መካከል አስሩ በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ በግፍ መገደላቸውን ከጥቃቱ የተረፈ የዐይን እማኝ ተናገረ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 14 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ኪረሙ ወረዳ ንጹኃን ለግድያ እና ለእንግልት ከተጋለጡባቸው የወለጋ ወረዳዎች አንዱ ነው። ወረዳው ለወትሮው የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦች በአንድነት እና በፍቅር የሚኖሩበት እና የሚያለሙበት ነበር። ከሦስት ዓመታት ወዲህ ግን በኪረሙ ውስጥ እንደወትሮው ተዘዋውሮ ማልማት ቀርቶ በሰላም ወጥቶ ለመግባትም አዳጋች ኾኗል። አሸባሪው ሸኔ በሚፈጽመው ዘር ተኮር ጥቃት በርካቶች ሃብት እና ንብረታቸውን ተዘርፈዋል፣ ጥለው ሸሽተዋል፣ በግፍ ተገድለዋል። አሁንም ድረስ እየተገደሉ ነው። ወጣት ይበልጣል መኮንን የኪረሙ ወረዳ ነዋሪ ነው። በወረዳው መብራት ባለመኖሩ ወፍጮ እና የመሳሰሉት መሠረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል፤ ዜጎችም በስቃይ ውስጥ ናቸው ብሏል። በወረዳው ምንም አይነት የሕክምና አማራጭ ባለመኖሩ ነዋሪዎች በበሽታ ጭምር እየተሰቃዩ ስለመኾኑም የዓይን ምስክርነቱን ሰጥቷል። ከነቀምት ወደ ቡሬ የሚወስደው መንገድ ዝግ በመኾኑ ወደ አማራ ክልል ዘልቆ ለመታከም እንኳን አዳጋች ስለመኾኑ ጠቁሟል። የጠናበት ታማሚን በቃሬዛ ተሸክሞ፣ የሁለት ቀን የእግር ጉዞ እንደሚጠይቅ ይናገራል። በጉዞ ላይ ከሸኔ አባላት እይታ ለመሰወር ሕመምተኛ በቃሬዛ ተሸክሞ ጫካ ለጫካ መሹለክለክ የነዋሪዎች የዕለት ከዕለት ስቃይ ኾኗል። ይበልጣል ሕመም የጠናባቸውን አያቱን ለማሳከም ቤተሰብና ወዳጆቹን አስተባብሮ በቃሬዛ በመሸከም ይኽንን ፈታኝ ጉዞ የጀመረው ታኅሳሥ 7/2015 ዓ.ም ነበር። ታላቅ ወንድሙን ጨምሮ በአጠቃላይ 16 ሰዎች ነበሩ ወደ ፈታኙ ጉዞ የወጡት። ከሁለት ቀን የጫካ ጉዞ በኃላ እሑድ ታኅሳስ 9/2015 ዓ.ም ጠዋት ላይ ነቀምት እና ቡሬን በሚያገናኘው የዓባይ ወንዝ ድልድይ አካባቢ ደረሱ። ይበልጣል እና አጋሮቹ አንድም በፀና ታመው በቃሬዛ ላይ ያሉትን እናት ይዘው ወደ አማራ ክልል ለሕክምና ስለተዳረሱ፣ ሁለትም የንጹኃንን ሕይወት በግፍ ከሚቀጥፉት የሸኔ አባላት ዓይን ተከልለው መንገዳቸውን በማገባደዳቸው ተደሰቱ። ይበልጣል እንደሚለው ከድልድዩ በግምት በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ደርሰው ነበር። ይኹን እንጅ በዚኽ ቦታ ላይ ቀድመው ያደፈጡ የሸኔ አባላት በከፈቱት ተኩስ በጉዞ የዛሉት እግሮች በዚያው ቀሩ። ለመዳን ተስፋን የያዘችው እናትም እኩይ ዓላማን ባነገቡ ግፈኞች ጥይት ተመትታ በዚያው አሸለበች። ይበልጣል እንደሚለው ከ16ቱ መንገደኞች ውስጥ የተረፉት እሱን ጨምሮ ስድስቱ ብቻ ናቸው። የጉዟቸው ምክንያት የኾኑት አያቱን እና ታላቅ ወንድሙን ጨምሮ አስሩ በግፍ ተገድለዋል። ይበልጣል ግን በአስከሬን መካከል ወድቆ ከሞቱት ጋር ተመሳስሎ ከቆየ በኋላ በደረቱ ተስቦ ወደ ጫካ በመግባት ከግፈኞች ጥይት ተርፎ ለምስክርነት ሊበቃ ችሏል። ከግፍ ግድያ የተረፈው ይበልጣል ዓባይ ድልድይ ኬላ ላይ የሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ አባላት እና በዙሪያው ያሉ የቁጭ ንዑስ ወረዳ የፖሊስ አባላትን በማግኘት ጉዳዩን ነግሮ የወንድሙ እና የወዳጆቹ አስከሬን እንዲነሳ አድርጓል። ሌሎች አምስት ጓደኞቹ ደግሞ ሩጠው በማምለጥ በጫካ ውስጥ ጉዞ ላይ እንደሚገኙ ነግሮናል። ካመለጡት መካከል የቆሰለ ስለመኖሩ ስልካቸው በሠራለት ወቅት ማረጋገጡን ገልጿል። ይሄንን ሁሉ ግፍ በአስከሬን መካከል ኾኖ የተመለከተው ወጣት ይበልጣል ወደ ቁጭ ከተማ ገብቶ በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ተጠልሎ ነው ያገኘነው። ይበልጣል በግፍ የተገደለውን ወንድሙን ጨምሮ የሌሎች ወዳጆቹ የእጅ ስልክ በሸኔ አባላት ስለመወሰዱ ነግሮናል። ወደወንድሙ ስልክ ደውሎ ነበር። የሰማው የወንድሙን ሳይኾን ሌላ የጭካኔ ድምጽ ነበር። “መንግሥት ወዴት አለ፤ በፀሐይ የሚገድልን ቡድን እንዴት መጠየቅ ተሳነው፤ ገዳይ በላይ ኾኖ በበደለኛ ላይ በስልክ ሲዝት ጠያቂ ለምንስ ጠፋ?” የወጣት ይበልጣል ጥያቄዎች ናቸው። መንግሥት በአስቸኳይ ይህን የጭካኔ ጥግ ሊያስቆም እንደሚገባ ተማጽኗል። መውጫ መንገድ እንኳን ተዘግቶባቸው ባዶ ቤት ውስጥ በርሃብ እና በበሽታ የሚሰቃዩ ዜጎች መኖራቸው ታውቆ ሀገር እየመራ ያለው መንግሥት አስቸኳይ የጸጥታ ኃይል ስምሪት በማድረግ ንጹሃንን ሊታደግ እንደሚገባ ጠይቋል። ዘገባው የአሚኮ ነው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply