ከወጪ ንግድ 4 ነጥብ 12 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱ ተገለጸ

የተመዘገበው የወጪ ንግድ ገቢ በታሪክ የመጀመሪያ መሆኑም ተነግሯል

ሐምሌ 14 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በ2014 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 4 ነጥብ 12 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሰታወቀ።

ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ ባለፉት አመታት የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡

በተለይም ባለፉት 3 የበጀት ዓመታት የአገር በቀል ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት፣ የወጨ ንግድን በመጠን፣ በአይነትና በጥራት ለማሳደግ የፖሊሲ፣ የስትራቴጂና የመዋቅራዊ ለውጥ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡

በተወሰዱት እርምጃዎችም በ2014 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 4 ነጥብ 12 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድ ትስስርና ወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ ገልጸዋል፡፡

ገቢው የእቅዱን 90 ነጥብ 3 በመቶ ሲሆን፤ ከባለፉት ዓመታት ዓፈፃጸም አንፃር ለታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበ የወጪ ንግድ ገቢ መሆኑንም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል፡፡

አገራችን በውስጣዊና በውጫዊ ፈተና ውስጥ ሆና የተገኘው ይህ ገቢ ከባለፈው በጀት ዓመት ገቢ በ13 ነጥብ 81 በመቶ እድገት ያሳየ ነው።

የተገኘው ስኬት ከገቢም በዘለለ ለአገራችን ብዙ ትርጉም ይሰጣል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የወጪ ንግድ ገቢ እያደገ መምጣት የሀገሪቱን ዓለምአቀፋዊ ተቀባይነት፣ የመበደርና ብድርን የመመለስ አቅምን ያሻሽላልም ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የግብርናው ዘርፍ የእቅዱን 105 በመቶ የአጠቃላይ እቀዱን 72 በመቶ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የእቅዱን 80 በመቶ የጠቅላላ እቅዱን 12 በመቶ ገቢ ያስገኙ ሲሆን፤ የማእድን ዘርፍ የእቅዱን 53 በመቶ የአጠቃላይ ወጪ ንግድ እቅዱን ደግሞ 14 በመቶ ነው ገቢ ያስገኘው፡፡

የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛውን ገቢ በማስገኘት አሁንም የኢኮኖሚው የመሪነት ደረጃውን የያዝ ሲሆን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማድረግ የተያዘውን ውጥን ለማሳካት ብዙ መስራት እንደሚጠይቅ ካሳሁን ጠቁመዋል፡፡

የጎንዮሽ ግንኙነት አለመዳበር፣ የኮንትሮባንድ ንግድ እና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር አዝጋሚነት የወጪ ንግዱን እየፈተኑት ያሉ ችግሮች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply