ከዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን ተፈናቅለው በእብናት ወረዳ ለሚገኙ ተፈናቃዮች በሰሜን አሜሪካ የአርማጭሆ ሰላምና ልማት መረዳጃ ማህበር ግማሽ ሚሊዮን ብር ወጭ ያደረገበትን ድጋፍ አበረከተ። ጥቅም…

ከዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን ተፈናቅለው በእብናት ወረዳ ለሚገኙ ተፈናቃዮች በሰሜን አሜሪካ የአርማጭሆ ሰላምና ልማት መረዳጃ ማህበር ግማሽ ሚሊዮን ብር ወጭ ያደረገበትን ድጋፍ አበረከተ። ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓ. ም (አሻራ ሚዲያ ) … የትህነግ አሸባሪ ቡድን በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በከፈተው ጦርነት በሰው ህይዎትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማስከተሉ በተጨማሪ በርካቶች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም የወሎ፣ የሰሜን ጎንደርና የዋግኽምራ አካባቢዎችን ለመጥቀስ ይቻላል፡፡ እሄን ተከትሎም ለወገን ደራሽ ወገን ነው በማለት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች እጃቸውን እየዘረጉ ይገኛሉ፡፡ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የአርማጭሆ ሰላምና ልማት መረዳጃ ማህበርም ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ 100 ኩንታል የፊኖ ዱቄትና 40 ኩንታል ስኳር በጠገዴ አርማጭሆና አካባቢው የበጎ አድራጎት ማህበር አማካኝነት ድጋፍ መደረጉን የማህበሩ መስራችና ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ገብረ መስቀል ሙሉ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ገ/መስቀል ሙሉ ገለጻ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የአርማጭሆ ሰላምና ልማት መረዳጃ ማህበር ከዚህ በፊትም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ እንዲሁም ለተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ጭምር የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ያለ መረዳጃ ማህበር መሆኑን አብራርተዋል፡፡ አሁን ላይ ያለውን ችግር የመንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የሚመለከተው አካል ተፈናቃይ ወገኖቻችን አካባቢያቸው ሰላም ሆና እስኪመለሱ ድረስ በምንችለው ሁሉ ልንደርስላቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ የጠገዴ አርማጭሆና አካባቢው በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና የቦርድ አባል የሆኑት አቶ አብተው አሻግሬ በበኩላቸው በሰሜን አሜሪካ በሚኖሩ የአርማጭሆና አካባቢው ተወላጆች የተደረገውን ድጋፍ ለተፈናቃይ ህፃናቶችና ሴቶች እንዲሁም አቅመ ደካሞችን ላይ እንዲደርስ አሳስበዋል፡፡ ችግሩ በዘላቂነት እስካልተፈታ ድረስ መረዳጃ ማህበሩ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት፡፡ ድጋፉን የተረከቡት የእብናት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉጌታ ይማም በበኩላቸው ከመስከረም 12/2014 ዓ.ም ጀምሮ የትህነግ አሸባሪ ቡድን በከፈተው ጦርነት አማካኝነት ከዋግኽምራ ብሔረሰብ ልዩ ዞን ከ18ሽ 600 በላይ ተፈናቃዮች በእብናት ከተማ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ የወረዳውና የከተማው ማህበረሰብም ለእነዚህ ተፈናቃዮች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝና የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦችም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡ አሁን ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይል፣ የአማራ ሚሊሻና ፋኖ በዋግኽምራ ግንባር ጠላትን እየለበለበ እንደሚገኝ ገልፀው በቀጣይ ነፃ የወጡ አካባቢዎችን በመለየት ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው የመመለስ ስራ እንደሚሰራም አብራርተዋል፡፡ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የአርማጭሆ ሰላምና ልማት መረዳጃ ማህበር ላደረገላቸው ድጋፍም ተፈናቃይ ወገኖች ምስጋናቸውን አቅርበዋል ሲል የዘገበው የማዕከላዊ ጎንደር ኮሚዩኒኬሽን ነው። ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም :- https://t.me/asharamedia24 ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- https://t.me/asharamedia24 Facebook :- https://www.facebook.com/asharamedia24 ዩትዩብ:- https://bit.ly/33XmKro

Source: Link to the Post

Leave a Reply