“ከውድቀት ታሪክ ወደ ዕድገት የሚያሻግር ፍጻሜ በኢትዮጵያና ኤርትራ”

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ

(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና

የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

ኢትዮጰያና ኤርትራ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻና ከ20ኛው ክፍለ ዘመን የውድቀት ታሪካቸው ወደ ተሻለ የዕድገት ሂደት የሚያሻግር ጉዞ እነኾ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ሊነጣጠልና ተለይቶ በፍጹም ሊታይ የማይችል የጋራ ኹለንተናዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ – ታሪክ፣ አኗኗር፣ ዕሴት፣ ባሕልና የአኗኗር ዘይቤ የነበራቸውና ያላቸው ከህጋዊ ማዕቀፍ ውጪ በኾኑ በርካታ ነገሮች የሚመሳሰሉ ሀገራት መኾናቸው የሚታወቅ ነው፡፡

ይህም ኾኖ ለዘመናት በሀገራችን የነበረው የሥልጣን ፖለቲካ እምነት (አስተሳሰብና አመለካከት)፣ እውቀት (ስልት፣ ስትራቴጂና ፕሮግራም) እንዲሁም ድርጊት (ተግባር) በተለያዩ ኃይሎች ከገዢ እስከ ተገዢ፣ ከምሁር እስከ ተማሪ፣ ከግለሰብ እስከ ቡድን ድረስ የሚዘልቁና የዘለቁ – የፍላጎት ልዩነቶችና ይህን ተከትለው የተደረጉ ፍትጊያዎች፣ ትግሎችና ውሳኔዎች ዘመኑ እንደነበረውና እንደያዘው አማራጭ ተመርቶ፣ ተንቀሳቅሶ፣ ኹለንተናዊ መስዋዕትነትን የሕይወት፣ የአካል፣ የእውቀት፣ የስሜት፣ የገንዘብ፣ የጉልበት – – – ከፍሎና አስከፍሎ መለያየት በሚል ድንበር እንዲታጠር ኾኗል፡፡

አሁን ኤርትራን እያስተዳደረ ያለው ገዢ ኃይል (ህ.ግ.ደ.ፍ /ሻዕቢያ/) ትጥቃዊ ትግልን ከ30 ዓመታት በላይ በማድረግ እንደማንኛውም ትጥቃዊ ትግል እንደሚያደርግ ኃይል ዓላማውን “ነጻ ኤርትራ የምትባል ሀገር መመሥረትን አድርጎ” ለዚህ ይረዳው ዘንድ እንደዋነኛ የመታገያ ስልትና ስትራቴጂ ብሎም እንደዓላማ መነሻና መዳረሻ “የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው!” በማለት ተንቀሳቅሶ ከማዕከላዊ መንግሥት የሚነጥቃቸውን ቦታዎች በቁጥጥሩ ስር እያዋለና ባዋለውም ቦታ የራሱን አስተዳደር እያቋቋመ እንደታገለ ይታወቃል፡፡

ይህም የትጥቅ ትግል ሂደት እስከ ግንቦት 16 – 1983 ዓ.ም ድረስ ቀጥሎ አስመራን፡ የኤርትራ ዋና ከተማን እስከ ተቆጣጠረበት ድረስ ቀጥሏል፡፡ በአንጻሩ በ13 ዓመታት ዘግይቶ የተጀመረው የህ.ወ.ሓ.ት የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ሌሎች መሰል የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱና ለማካሄድ በጅምር ላይ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎችን በማካተት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ በመሰኘት በተመሳሳይ በቁጥጥር ስር ባዋሏቸው አካባቢዎች የራሳቸውን አስተዳደር እያቋቋሙ ግንቦት 20 – 1983 ዓ.ም አዲስ አበባን ተቆጣጥረዋል፡፡

በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች የጋራ በሚያደርጋቸው እና ዓላማቸውን ለማሳካት የሚያስችላቸውን ስልታዊና ታክቲካዊ ግንኙነት በማድረግ ለድል መብቃታቸው እንደተጠበቀ ኾኖ የ20ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ከአንድ ሀገርነት ወደ ሁለት የተለያዩ ሀገራትነት፤ ከአንድ ነን – የተለያየን ነን፤ ተመሳሳይ ከነበረ ዜግነት ወደ ሁለት ሀገራት ዜጋነት፤ ልዩነት ካልነበረበት ሀገራዊ ማዕቀፍ ወደ ጎረቤታምነት፤ ከመተሳሰብ ወደ መሳሳብ፤ ከአብሮነት ይልቅ ወደ ውድድር የገባንበትን ምዕራፍ ዕውን እንዲኾን አስችሏል፡፡

ይህም በሁለቱም ሀገራት ሕዝብ ላይ የራሱን ኹለንተናዊ አዎንታዊና አሉታዊ አሻራዎችን አሳርፏል፡፡ ይህ በንዲህ እንዳለ ምንም እንኳ ጉዳዩ ቀድሞ ያለቀና ማለቁም ለፖለቲካ ኃይሎቹ እንደግብ ያስቀመጡት መኾኑ ቢታወቅም ሕጋዊ ሰውነትን ለማላበስና በዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ሲባል ለፎርማሊቲ (Formality) ሪፈረንደም (Refurendom) እንዲካሄድ ተደርጎ መለያየታችን ተበሰረ፡፡ የመለያየትም ባሕሪያዊና ጠባያዊ ክስተቶች ኹሉ በሁለቱ ሀገራት ሕዝብ ላይ አረፈ፡፡

ይባስ ብሎ የተገለጹና ያልተገለጹ፤ የሚታወቁና የማይታወቁ ፍላጎቶች ወደ ከፍ ያለ አለመግባባትና አለመስማማት ከፍ ብለው በየትኛውም መለኪያ ሊኾን የማይገባው ግን የኾነ በአሰቃቂነቱና በጉዳቱ ስፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ አብነት መኾን የቻለ ጦርነት ተካሂዶ የሁለቱ ሀገራትን በከፍተኛ ደረጃ በኹለንተናዊ መንገድ ጎድቶ “ጦርነትም ኾነ ሰላም የሌለበትን“ ቀጠና አብነታዊነት ለሁለት አስርት ዓመታት አምጥቷል፡፡

ክስተቱ ከመጀመሩ በፊት፣ ከተጀመረ በኃላም ኾነ በቅርብ ጊዜያት መደበኛ (Formal) እና መደበኛ ባልኾኑ (Informal) መንገዶች በግለሰቦች፣ በቡድኖችና በተቋማት በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ፤ በሀገራት መንግሥታትም ኾነ በሃይማኖት አባቶችና በሀገር ሽማግሌዎች እጅግ በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ የቆየ ቢኾንም ከነበረበት ኹኔታ ትርጉም ባለው መንገድ ፈቅ ሳይል ቆይቶ እነኾ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የ20ኛው ክፍለ ዘመን የውድቀት ታሪካችንን የሚያድስ አዲስ ምዕራፍ በኹለቱ ሀገራት መንግሥታት ሲከናወን ተመልክተናል፡፡

ስለኾነም ቀድሞውንም በጉዳዩ ላይ የተወሰነበትን የመቀበል፤ የመገዛት እና የመመራት እንጂ የመወሰን፣ የመግዛትና የመምራት ሥልጣን የሌላቸው የሁለቱ ሀገራት ሕዝብ ደስታውን በተለያየ መንገድ እየገለጸ ይገኛል፡፡ ይህም ማንም ጤነኛ አዕምሮና ዕይታ ያለው ሰላም፣ ፍቅርና ሕብረትን የሚሻ ፍጡር ስሜት ነው፡፡ ኾኖም ግን እንቅስቃሴውንና ክስተቱን ከዘላቂነት፣ ከአስተማማኝነትና ከተጠቃሚነት አንጻር እንዴት ዘላቂ ማድረግ ይቻላል? የሚል ያልተመለሰ ዐቢይ ጥያቄ መኖሩ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡

1.1 ከድንቅ ጅማሬ ወደ ድንቅ ፍጻሜ ለመሻገር መልስ የሚሹ የኢትዮጵያና የኤርትራ የጋራ ጥያቄዎች

ኹለንተናዊ ሰላምን፣ ፍቅርንና ህብረትን ማንኛውም ፍጡር የሚሻው ጉዳይ ነው፡፡ በሰው ልጅ ሰፊ የታሪክም ኾነ ዛሬ – ኹለንተናዊ የትላንት፣ የዛሬና የነገ ፍላጎቶችን መሠረት ባደረጉ ኹለንተናዊ ግንኙነቶች የተነሣ – ባሕሪያዊና ጠባያዊ ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና ችግሮች ሲከሰቱ ቆይተዋል፡፡

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በሰፊው እንደተንጸባረቀው ኹሉ በኢትዮጵያና በኤርትራ መሐከል መፈጠር ነበረባቸው ወይስ አልነበረባቸው? ማን ነው አነሳሹ? መንሥኤውስ ምንድነው? የሚለውን ዐበይት ጥያቄዎች እንዳሉ ኾነው አሁን ባለው እንቅስቃሴ ሊታዩና ትርጉም ባለው መንገድ መልስ ሊያገኙ የሚገቡ ነጥቦች፡-

1ኛ. በተፈጠረው ችግር፣ ግጭትና አለመግባባት መንሥኤ የኾኑ ዕውነተኛ ጉዳዮች ተለይተው ተቀመጡ ወይ?

2ኛ. በተቀመጡት ዕውነተኛ ነጥቦች መነሻነት ማን ምን አይነት ድርሻ ወሰደ?

  • የማንኛውም ትግልና አለመግባባት መነሻ – ማን ምን አገኘ? መቼ? የት? ለምን? እንዴት? የሚሉ ጥያቄዎች ላይ ማዕከል የሚያደርግ ነው፡፡ (N.B:- Any struggle and controversy was/is over ‘who gets what, when, how.’)

3ኛ. ድርሻ በመውሰድ ሂደት ማን ምን ያገኛል? ማንስ ምን ያጣል?

4ኛ. ያገኘ ማግኘቱን እንዴት ያየዋል? የሚያጣውስ ማጣቱን እንዴት ይመለከታል?

5ኛ. በዚህ ሂደት ከወሳኞቹ አካላት በላይ የሚወሰንበትና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው፣ በታሪኩና በአኗኗሩ ከፍ ሲልም በማንነቱ ላይ ተጽዕኖ የሚያርፍበት ሕዝብ ነገሮችን እንዴት ይመለከታቸዋል?

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ እንደሕዝብ ሰላም፣ ፍቅርና ሕብረትን እንደትላንትና ከትላንት ወዲያ ኹሉ ዛሬም ኾነ ነገ እንደሚፈልግ ፍጹም አያጠራጥርም፡፡ ጥያቄው ፍላጎትና መኾን የሚገባው እየኾነ ካለው ጋር ከዘላቂነት፣ ከአስተማማኝነትና ከማያዳግም መፍትሔነት አንጻር ከላይ የተጠቀሱ ጥያቄዎች ተመልሰዋል ወይ? የሚል ይኾናል፡፡

ለዚህም የማንኛውም አይነት ኹለንተናዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ትርጉም ያለው ፋይዳ የሚያመጣው ከተጠቃሚነት ጋር ሲያያዝ ብቻ ነው፡፡ ተጠቃሚነት የኹሉ አይነት ለውጥ መነሣሻ፣ መታገያ፣ ሕብረት የመፍጠሪያ፣ የማታገያ፣ የመትጊያና ተስፋ የማድረጊያ ትልቅ መሣሪያ ነው፡፡ ያለ ተጠቃሚነት የነገሮችን ዑደትና ሂደት በነጠላ፣ በቡድንም ኾነ በተuም ደረጃ ትርጉም ባለው መንገድ ከለውጥ ጋር አያይዞ ማስቀጠልና ማንቀሳቀስ አዳጋች ነው፡፡

በመኾኑም የኢትዮጵያና ኤርትራ ኹለንተናዊ ግንኙነትም የጋራ ለጋራ ስለጋራ በጋራ ተጠቃሚነት – ተጠቃሚነትን መነሻውና መዳረሻው ብሎም የእንቅስቃሴው ማዕከል ኹሉ እርሱ ከኾነ – ዘላቂ፣ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ይችላል፡፡ በዚህም አዲሱ ሂደት ከውድቀት ታሪክ ወደ ዕድገት የሚያሻግር ጅማሮ ብቻ ሳይኾን ዘላቂ መንገድ ይኾናል፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

Leave a Reply