ከየመን የባሕር ዳርቻ አካባቢ አንድ የአሜሪካ ዕቃ ጫኝ መርከብ በሚሳይል ተመታ።

መርከቡ ከአናት ቢመታም የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን እና በባሕር ላይ መቅዘፍ እንደሚችል አምብሬ የተባለ የብሪታኒያ ኩባንያ አስታውቋል።

እስራኤል በጋዛ ሕዝብ ላይ የምትፈፅመዉን ግፍ ካላቆመች ቀይ ባሕርን አቋርጠዉ ከና ወደ እስራኤል የሚቀዝፉ መርከቦችን እንደሚያጠቁ በተደጋጋሚ ያስጠነቀቁት የየመን ሁቲዎች ካለፈዉ ሕዳር አጋማሽ ጀምሮ በቀይ ባሕር ላይ የሚቀዝፉ መርከቦችን ማጥቃት ጀምረዋል።

አሜሪካ የምትመራና የምታስተባብራቸዉ 10 መንግስታት የሁቲዎችን ጥቃት ለመከላከል ዘመቻ-ብልፅግና ያሉትን የጋራ ግንባር መሥርተዋል።

ዋና ማዘዢያዉን ባሕሬን ላደረገዉ ጦር መርከብና ወታደር ካዋጡት ሐገራት አንዳዶቹ ዘመቻዉ ጥቃትን ከመከላከል እንዳያላፍ ሲያስጠነቅቁ ነበር።

የኢጣሊያዉ መከላከያ ሚንስትር ጉይዶ ክሮሴቶ ባለፈዉ ሳምንት አጋማሽ ላይ የሁቲዎች ጥቃት «ሶስተኛ ግንባር» ያሉትን ጦርነት ሳይጭር መቆም አለበት ብለዉ ነበር።

የሁቲ የጦር ኃይል ቃል አቀባይ ጄኔራል ያሕያ ሳራኢ ባለፈዉ አርብ እንዳሉት ቡድናቸዉ የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ ጦር ኃይላት በየመን ላይ ያደረሱትን ጥቃት ይበቀላል።

የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ ጦር ኃይላት የመንን መደብደባቸዉን የሁለቱ ሐገራት የቅርብ ታማኞች የሚባሉት ሳዑዲ አረቢያና ግብፅ አሳሳቢ ሲሉት፣ ኦማን አዉግዛዋለች።

ኢራንም አጥብቃ አዉግዛዋለች የኢራን ወዳጅ የምዕራባዉያን ጠላት የምትባለዉ ሩሲያ ደግሞ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ እንዲነጋገር ጠይቃለች።ቻይና ሁሉም ወገኖች ጠቡን ከማባባስ እንዲታቀቡ መክራለች።

ይሁንና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ባለፈዉ ቅዳሜም የመንን መደብደቡ ተዘግቧል።የሁቲ ታጣቂዎች ባለፈዉ ዕሁድ በዩናይትድ ስቴትስ የጦር መርከቦች ላይ የተኮሱትን ሚሳዬል የአሜሪካ ጦር ማክሸፉን አስታዉቋልም።

የአዉሮጳ ሕብረት በበኩሉ በቀይ ባሕር ላይ የሚቀዝፉ መርከቦችን ደህንነት የሚጠብቅ ጦር ኃይል ለማዝመት መምከር ጀምሯል።

የሕብረቱ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች በሚቀጥለዉ ሳምንት በጉዳዩ ላይ ለመወሰን ቀጠሮ አላቸዉ።ጀርመን ጦር የማዝመቱን ሐሳብ እንደምትደግፈዉ የሐገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር አስታዉቋል።

ዘገቦች እንደሚጠቁሙት ኢጣሊያ፣ ፈረንሳይና አየርላንድን የመሳሰሉ የሕብረቱ አባል ሐገራትም ሐሳቡን ለመደገፍና ለመቃወም እያቅማሙ ነዉ።

ጥር 07 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply