ከየካቲት 29 ጀምሮ የሚሰጠዉ የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ወረቀት በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እስከ መጪዉ አርብ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ/ም ድረስ ተጓጉዞ እንደሚጠናቀቅ የብሄራዊ ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የፈተናዎች ኤጀንሲ ከኢትዮጲያ አየር መንገድ ጋር ባደረገዉ ስምምነት መሰረት ፈተናዎቹ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እየተጓጓዙ መሆናቸዉን የኤጀንሲዉ ዋና ዳይሬክተር ዶክትር ዲላሞ ቱሬ ለአሀዱ ተናግረዋል፡፡

በጥብቅ ቁጥጥር በመከላከያ ሰራዊት እና በፌደራል ፖሊስ አጃቢነትም በተቀመጠዉ አቅጣጫ እና የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተጓጓዘ ነዉ ብለዋል፡፡አያይዘዉም ፈተናዎቹ ወደ ክልል ከተሞች ሲደርሱ የየክልሎቹ ፖሊስ እና ልዩ ሀይል ጥብቅ ቁጥጥር እና እጀባ አድርገዉ ወደ ዞኖች እንደሚያደርሱም ተናግረዋል፡፡

እስካሁን እየተደረገ ያለዉ የማጓጓዝ ሂደትም ሰላማዊ ነዉ፤ ምንም አይነት ችግር አልገጠመውም ሲሉም ተናግረዋል፡፡የጸጥታ ስጋት አለባቸዉ የተባሉ ቦታዎች ላይም ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ በመከላካያ ሰራዊት እና በፌደራል ፖሊስ ታጅቦ እንደሚጓጓዝም ገልጸዋል፡፡ በመላዉ ሀገሪቱ ፈተናዉ እስከ መጪዉ አርብ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ/ም ተጓጉዞ እንደሚጠናቀቅ ዶክትር ዲላሞ ለአሀዱ አረጋግጠዋል፡፡

ፈተና በሚወሰድባቸዉ ቀናት የጸጥታ እና ሌሎች ችግሮች እንዳይከሰቱ ከ400 በላይ የፖሊስ አባላት ፈተናዉ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ስምሪት እንደተሰጣቸዉም ይታወሳል፡፡

ቀን 24/06/2013

አሐዱ ራዲዮ 94.3

Source: Link to the Post

Leave a Reply