ከደቡብ ሱዳን ድንበር ጥሰው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች አሁንም ጥቃት እየፈፀሙ ይገኛል ተባለ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 2 ቀን 2015 ዓ/ም…

ከደቡብ ሱዳን ድንበር ጥሰው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች አሁንም ጥቃት እየፈፀሙ ይገኛል ተባለ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 2 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ መነሻቸውን ከደቡብ ሱዳን በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ጥሰው የሚገቡት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የአርብቶ አደሮችን እንስሳት መዝረፍን ጨምሮ ህፃናትን አፍኖ እስከመውሰድ የሚደርስ ጥቃት እየፈፀሙ እንደሆነ ተነግሯል። ታጣቂዎቹ የሚያደርሱት ጥቃት ከ2008 እስከ 2011 ድረስ በነበረው ጊዜ ውስጥ ሀይል አደራጅተው ድንበር ጥሰው በመግባት ከፍተኛ ጥቃት ይፈፅሙ ነበር ሲሉ የጋምቤላ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሀላፊው አቶ ኡገቱ አዲንግ ተናግረዋል። ከ2011 ወዲህ ያለው እንቅስቃሴ አስቀድሞ ከነበረው አንፃር በከፍተኛ ሁኔታ ቢቀንስም አልፎ አልፎ ግን በሀይል ድንበር ጥሰው በመግባት ህፃናትን አፍኖ የመውሰድ እና ሌሎች የዝርፍያ ተግባራትን እንደሚፈፅሙ ሀላፊው አንስተዋል። እነዚሁ ታጣቂዎች በ2013 አንዳንድ ጥቃቶችን ሲፈፅሙ ነበር ያሉት አቶ ኡገቱ በ2014 ዓ.ም መላው የክልሉ ፀጥታ መዋቅር ከፌደራሉ ጋር ባደረገው እንቅስቅሴ በጠንካራ መከላከል ጥቃቶቹ የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ እንዲከሽፉ መደረጋቸውን አስታውቀዋል። በቀጣይም ከአካባቢ ሚሊሻ አንስቶ ያለውን የፀጥታ መዋቅር በማቀናጀት ታጣቂዎቹ ጥቃት እንዳያደርሱ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል። ታጣቂዎቹ አሁንም አልፎ አልፎ ይህንኑ ጥቃት እየፈፀሙ እንደሚገኙ ያነሱት ሀላፊው በጥቅምት ወር ላይ በፈፀሙት ድንገተኛ ጥቃት የአኝዋ ዞን ፖሊስ አዛዥን ገድለው እንደነበር አስታውቀዋል። የክልሉን የፀጥታ ሀይል በማጠንከር ጥቃቱን ከመከላከል ባለፈ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ኡገቱ አዲንግ ጨምረው ስለመግለጻቸው ብስራት ሬድዮ ነው የዘገበው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply