You are currently viewing ከዳኖ ወረዳ የተፈናቀሉ አማራዎች መንግስት እና የሰብአዊነት ጉዳይ የሚገዳቸው ወገኖች ሁሉ እንዲደግፏቸው ጥሪ አቀረቡ፤በ አሜሪካ የምትኖር ኢትዮጵያዊ በጎ ፈቃደኛ ያደረገችውን ድጋፍ ተቀብለው…

ከዳኖ ወረዳ የተፈናቀሉ አማራዎች መንግስት እና የሰብአዊነት ጉዳይ የሚገዳቸው ወገኖች ሁሉ እንዲደግፏቸው ጥሪ አቀረቡ፤በ አሜሪካ የምትኖር ኢትዮጵያዊ በጎ ፈቃደኛ ያደረገችውን ድጋፍ ተቀብለው…

ከዳኖ ወረዳ የተፈናቀሉ አማራዎች መንግስት እና የሰብአዊነት ጉዳይ የሚገዳቸው ወገኖች ሁሉ እንዲደግፏቸው ጥሪ አቀረቡ፤በ አሜሪካ የምትኖር ኢትዮጵያዊ በጎ ፈቃደኛ ያደረገችውን ድጋፍ ተቀብለው በማመስገን ለሚያጠቡ እናቶችና ለአቅመ ደካሞች አከፋፍለዋል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 18 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ከምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ የተፈናቀሉ አማራዎች መንግስት እና የሰብአዊ ጉዳይ የሚገዳቸው ወገኖች ሁሉ እንዲደግፏቸው ጥሪ አቅርበዋል፤ አሜሪካ የምትኖር ኢትዮጵያዊ በጎ ፈቃደኛ ያደረገችውን ድጋፍ ተቀብለው በማመስገን ለሚያጠቡ እናቶችና ለአቅመ ደካሞች አከፋፍለዋል። ወ/ሮ የሸዋዘውድ ረታ የአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ)ን በተፈናቃዮች ላይ የሰራውን ዘገባ ተመልክተው የላኩላቸውን የ75 ሽህ ብር ድጋፍ በመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው በኩል ብርድ ልብሶችን በመግዛት 60 ለሚሆኑ የሚያጠቡ እናቶችና ለአቅመ ደካሞች አድርሰዋል። በተጨማሪም ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ሊትር ዘይት እንዲደርሳቸው አድርገዋል። ታህሳስ 17 ቀን 2014 ድጋፉን ያከፋፈሉትም በለሚኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክር ተገኝተው መሆኑን አማራ ሚዲያ ማዕከል በስፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል። ወ/ሮ የሸዋዘውድ ረታን ወክሎ የተገኘው ቤተሰቧ ወጣት ዘመኑ ያየህ በአማራዊ ማንነታቸው በግፍ የተፈናቀሉ ወገኖችን አጽናንቷል፤ ልክ እንደ ወ/ሮ የሸዋዘውድ ረታ ሁሉ ሌሎች በጎ ፈቃደኛ ወገኖችም ከተጎጅዎች እንዲደግፉ ጥሪ አቅርቧል። በተመሳሳይ የዳኖ ተፈናቃዮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አስተባባሪዎችም አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ችግራችን ተረድቶ ለህዝብ በማሳወቅ ረገድ ከጎናችን በመሆኑ ከልብ እናመሰግናለን ብለዋል፤ ሌሎች የሚዲያ ተቋማትና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም ከጎናቸው በመሆን እንዲረዷቸው ጠይቀዋል። በዋናነት ግን በሀገረ አሜሪካ የምትኖረው እህታችን ወ/ሮ የሸዋዘውድ ረታ ላደረገችው ሰብአዊ እርዳታ ከፍ ያለ ምስጋና ይድረሳት ብለዋል። መንግስት እና ሌሎች የሰብአዊ ጉዳይ ያገባናል የምትሉ ወገኖች ሁሉ በወራት እድሜ ብቻ ከ1,500 በላይ አባዎራዎች፣ በድምሩ ከ9,542 ቤተሰቦች በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ እና በጥፋት ተባባሪዎቹ በኃይል ተፈናቅለው የደረሰባቸውን የጭካኔ በትር ተመልክታችሁ እንድትደግፉ ጥሪ ቀርቦላችኋል። በተያያዘ በእለቱ የተገኙ የሚያጠቡ እናቶች እና አቅመ ደካማ አዛውንቶች ለተደረገላቸው ወገናዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፤ የደረሰባቸውን ድርብርብ በደል በመግለጽም የሁሉንም ትኩረትና ትብብር የሚሹ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ሙሉ ዝግጅቱን በአሚማ የዩቱብ አድራሻ ይጠብቁ።

Source: Link to the Post

Leave a Reply