ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀው የአፋር እና ኢሳ ጎሳዎች ግጭትን ለመቋጨት የተኩስ አቁም ስምምነት ተደረገ

በድንበርተኞቹ የአፋር ሕዝቦች እና ኢሳ በሚል መጠሪያ በሚታወቁት በሶማሌ ክልል የሚኖሩ ጎሳዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶች በውስን አርብቶአደሮች መካከል ከሚፈጠር ግብግብነ እስከ ተካረረ እና በትጥቅ ግጭት ድረስ በየጊዜው ይከሰታል። 

በዛሬው ዕለት ሚያዝያ 10 ቀን 2016 በተካሄደ ውይይት የሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ግጭት በዘላቂነት እንዲያበቃ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ መግባባት ላይ መድረስ መቻሉ ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከቀናት በፊት የካቲት 29 ቀን 2016 ባካሄደው የእርቀ ሠላም መድረክ ይኽን ለዘመናት የዘለቀ አለመግባባት በዘላቂነት ለመፍታት 25 አባላት ያሉት የእርቀ ሰላም ኮሚቴ መቋቋሙን አዲስ ማለዳ እንደዘገበች አይዘነጋም።

በወቅቱም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ “ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የተኩስ ድምፅ እንደማይሰማ እና ግጭት እንዳይኖር ሁለቱም ወንድማማቾች” መሳሪያቸውን እንዲያስቀምጡ ተማጽነው ነበር። የዕርቀ ሰላም ጥረቱ ከሁለቱም ክልሎች ገለልተኛ የሆኑ የአገር ሽማግሌዎች፣ ኡጋዞች፣ ሡልጣኖች፣ የክልል መጅሊስ አመራሮችና የጎሳ ተጠሪዎችን በማሳተፍ ተካሄዷል ተብሏል።

በዚህም  የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሁለቱም ወገኖች በተወከሉበት እንዲሁም የሰላም ሚኒስቴር ታዛቢዎች፣ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንትን እና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት በዕርቀ ሰላም ውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።

በአፋር እና ሶማሌ ክልል አጎራባች የሚገኙት ሁለቱም ሕዝቦች አርብቶ አደር እንደመሆናቸው መጠን ግጭቶቹ በግጦሽ መሬት ይገባኛል ጥያቄ እንዲሁም በአዋሽ እና ኤረር ወንዞችን አጠቃቀም መሰረት ያደረጉ ሽኩቻዎች ናቸው። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በኹለቱ ሕዝቦች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቀረት የኢሳ ጎሳ አባላት ወደ ኤረር ወንዝ ምዕራባዊ አቅጣጫ እንዳያልፉ ተከልክለው እንደነበር ታሪክ ይጠቁማል። 

ሆኖም በደረቃማ ወቅቶች የኢሳ ጎሳ አባላት ለከባድ የውሃ እና የሣር እጦት እንዳረጋለን በሚል የጦር መሣሪያ ሳይታጠቁ ወደ ተከለከሉባቸው ስፍራዎች በመግባት የውሃ እና የግጦሽ ሣር ችግራቸውን እንዲያስታግሱ ይደረግ እንደነበር የቀድሞ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በ1997 ያስጠናው የጥናት መዝገብ ያስረዳል።

በደርግ የሥልጣን ዘመንም የሁለቱ ተጎራባች ሕዝቦች ግጭትን ለመቆጣጠር ተመሳሳይ እርምጃዎች እየተወሰዱ ቢቆዩም የአዲስ አበባ–አሰብ መንገድን ተከትሎ አዳዲስ ከተሞች መቆርቆራቸው ግጭቶቹ መልካቸውን እየቀየሩ እንዲኼዱ አድርጓቸዋል።

በዚህ ምክንያት በኹለቱ አጎራባች ማኅበረሰቦች መካከል የሚነሳው የድንበር ውዝግብ በዋናነት አደይቱ፣ ገዳማይቱ እና ዑንድፎ በተባሉ አነስተኛ ከተሞች ይገባኛል ጥያቄ ላይ የሚያተኩር ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት እንደ መፍትሔ የሚቀርቡ ሃሳቦች ሳይተገበሩ በመቅረታቸው አሊያም ሃሳቦቹ ውጤታማ መሆን ባለመቻላቸው ግጭቱን ማስቆም ሳይቻል ቀርቷል።

ለአብነትም የቅርብ ጊዜ ትዝታ መጋቢት 30 ቀን 2013 የሰላም ሚኒስቴር በአዋሳኝ ድንበሮች ላይ የተፈጠሩትን ግጭቶች ለማስቆም የምክክር መድረክ ማካሄዱን ተከትሎ፤ ግጭቱ እየተባባሰ በመምጣቱ የበርካቶች ሕይወት መጥፋቱ፣ የአገር እና የግለሰቦች ንብረት መውደሙ አንዱ ማሳያ ነው።

ከዓመታት በፊት የወቅቱን የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለምን ጨምሮ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ባደረጉት ውይይት ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ያስችላል የተባለ ስምምነት ላይ ተደርሷል ተብሎም ነበር። ሆኖም ግን የአፋር እና የሱማሌ ክልል መንግሥት እና ርዕሰ መስተዳድሮች ችግሮቻቸውን በዘላቂነት ለመቅረፍ በየወቅቱ ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት ተገናኝተው ሲመክሩ ይስተዋላል። 

በአንጻሩ የአሁኑ ስምምነት መሬት ላይ ለማውረድ በሳምንት ጊዜ ውስጥ በጠቅላይ ምክር ቤቱ ሰብሳቢነት ዳግም በመገናኘት የትግበራ ሂደቱን እና ቀጣይ ሂደቱን አቅጣጫ ለማስቀመጥ መስማማታቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገልጿል።

ጠቅላይ ምክር ቤቱም እንደ ሐይማኖት ተቋም የሚጠበቅበትን ኃላፊነትን ለመወጣት የሁለቱን ሕዝቦች ግጭት በዘላቂነት ለማስቆም እና መፍትሄ ለማበጀት ሰፊ ሥራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝደንት ልዩ አማካሪ የሆኑት ኡስታዝ አቡበክር አህመድ አስታውቀዋል።

በአሁን ዘላቂ የተኩስ አቁም ለማድረግ የተደረሰው ስምምነት ለዘመናት የዘለቀውን ግጭት ለማስቆም ያስችል ይሆን?

Source: Link to the Post

Leave a Reply