ከጤፍ ዱቄት ጋር የተለያዩ ባዕድ ነገሮችንና የእንጨት ፍቅፋቂ (ሰጋቱራ) በመቀላቀል ለሕብረተሰቡ ሊያከፋፍሉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ሐሙስ ግንቦት 3 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ከጤፍ ዱቄት ጋር የተለያዩ ባዕድ ነገሮችንና የእንጨት ፍቅፋቂ (ሰጋቱራ) በመቀላቀል ለህብረተሰቡ ሊያከፋፍሉ የነበሩ ግለሰቦችን በሕብረተሰቡ ትብብር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

ሕገ-ወጥ ተግባሩ ሲፈፀም የነበረው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በተለምዶ አጠራሩ ቆሼ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ መጋዘን ውስጥ መሆኑ ተገልጿል።

በመጋዘኑ ውስጥ 47 ኩንታል ምንነታቸው ያልታወቀ ስራ ስርና የእንጨት ፍቅፋቂ ሰጋ ቱራ 167 ኩንታል የጤፍ ዱቄት ተከማችቶ የተገኘ ሲሆን፤ ባዕድ ነገሩን ከዱቄቱ ጋር የሚደባልቅ መጋዘኑ ውስጥ እንዳይወጣ የተቆለፈበት ሠራተኛ በፍተሻ መገኘቱን ፖሊስ አስታውቋል።ከአካባቢው ማህበረሰብ በደረሰው ጥቆማ መሰረት የጅማ በር አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በህግ አግባብ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ በሥራ ላይ የነበረውን ተጠርጣሪ እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር አውሎ ባደረግው ተጨማሪ ምርመራ፤ የንብረቱን ባለቤትን አፈላልጎ በመያዝ ተገቢው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚሞክሩትን ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን ሕብረተሰቡ ሲመለከት ለፖሊስ አጋልጦ በመስጠት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪውን አቅርቧል።

The post ከጤፍ ዱቄት ጋር የተለያዩ ባዕድ ነገሮችንና የእንጨት ፍቅፋቂ (ሰጋቱራ) በመቀላቀል ለሕብረተሰቡ ሊያከፋፍሉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply