ከጦርነት የተረፉ ፈንጂዎች እና ያልፈነዱ ተተኳሾች መጠንን የሚለይ የዳሰሳ ጥናት ሊካሄድ ነው 

በመላው ኢትዮጵያ ከጦርነት የተረፉ ፈንጂዎችን እና ያልፈነዱ የከባድ መሳሪያ ተተኳሾች መጠን ምን ያህል  መሆኑን የሚለይ የዳሰሳ ጥናት ሊካሄድ ነው። ከኢትዮጵያ ፈንጂ አምካኝ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ጥናቱን የሚያካሄደው ከአሜሪካ መንግስት የተላከ የባለሙያዎች ቡድን ነው ተብሏል።

የቡድኑ አባላት ከአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር የሰብዓዊ ፈንጂ ማምከን ማሰልጠኛ ማዕከል እና ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የጦር መሳሪያ ማስወገድ እና ቅነሳ ፕሮግራም የተውጣጡ መሆናቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ  ኤምባሲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የዳሰሳ ጥናቱን እና ቀጣይ ድጋፎችን በተመለከተ፤ የኤምባሲው ተወካዮች እና የባለሙያዎች ቡድኑ አባላት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኃላፊዎች ጋር ትላንት ሰኞ ጥር 6፤ 2016 ዓ.ም. መወያየታቸውን ኤምባሲው ገልጿል።

በኢትዮጵያ የአምስት ቀናት ቆይታ የሚኖራቸው የቡድኑ አባላት፤ በትላንቱ ውሏቸው የኢትዮጵያ ፈንጂ አምካኝ ጽህፈት ቤትን ጎብኝተዋል። የባለሙያዎች ቡድኑ ከጽህፈት ቤቱ ጋር በመተባበር የሚያደርገው የዳሰሳ ጥናት፤ ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያሉ ሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት እና የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል ያለመ መሆኑን የአሜሪካ ኤምባሲ መግለጫ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ ጊዜ የተቀበሩ ፈንጂዎች፣ የከባድ መሳሪያ ተተኳሾች እና ውጊያ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያሉ የጦርነት ቅሪቶች፤ የሰላማዊ ሰዎች ህይወትን ከመቅጠፉ ባሻገር አርሶ አደሮች ወደ ማሳቸው ተመልሰው የእርሻ ስራቸውን እንዳያከናውኑ እንዳደረጋቸው በመግለጫው ተጠቅሷል። ይህ ሁኔታ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ የመበተን እና ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራ ላይም እንቅፋት መፍጠሩን ኤምባሲው ገልጿል። 

ይህንን ችግር ለመቅረፍ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በጀመረችው ትብብር፤ የዳሰሳ ጥናት ከማድረግ በተጨማሪ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ተግባራዊ የሚደረግ የቁሳቁስ፣ የስልጠና እና ተጨማሪ ድጋፎች ለመስጠት አቅዳለች። የዳሰሳ ጥናቱ የትኛዎቹን የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደሚሸፍን በመግለጫው አልተብራራም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

Source: Link to the Post

Leave a Reply